ራስን ፍለጋ

ተወልጄ ያደኩት አዲስ አበባ ውስጥ ነው። ልጅነቴ እንደአብዛኛው ኢትዮጲያዊ ነበር የተማርኩ በአንድ የህዝብ ት/ቤት ውስጥ ነው፡ ከትምህርት ውጪ ያለ ሰዓታችንን ሰፈር ውስጥ በመጫወት እና እሁድ እሁድ አባባ ተስፋዬን ተሰብስበን በማየት እናሳልፋለን። የእኔ ቤተሰቦች አክራሪ ክርስቲያኖች ስለነበሩ ቤተ ክርስቲያን በጣም እንሄዳለን የሰንበት ትምህርትም እማራለሁ በዛም ብዙ ጓደኞች ነበሩኝ እና ከነሱም ጋር ጊዜ አሳልፋለሁ።

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደገባሁኝ ከ“ዮሃና” ጋር አብረን መቀመጥ ጀመርን በዛም ተግባብተን ጓደኛ ሆንን። የእኔና የዮሃና ጓደኝነት በጣም የጠበቀ ነው ከተግባባን  ጥቂት  ሳምንት  እንዳለፈ ደብዳቤ  መጻጻፍ  ጀመርን።  የደብዳቤውን  ይዘት አላስታውስም፤ የማስታውሰው  ከትምህርት ቤት ቤት እስከምደርስ እና ደብዳቤውን እስከማነብ ያለኝን ችኮላ እና ጉጉት ነው። ዮሃና እና እኔ  ደብዳቤ  ከመጻጻፍ  ባለፈ  በዛን  ወቅት  ይወጡ  የነበሩ  የፍቅር  ሙዚቃዎችን ስንገባበዝ አስታውሳለሁ። አንዳችን ከትምህርት ቤት  ከቀረን  እንኮራረፋለን፤  እንደባበራለን። “ናፍቀሽኛል” የምንባባላቸውን የሰኞ ደብዳቤዎች ቅዳሜና ዕሁድ ላይ አስባቸዋለሁ። ዮሃና የምትኖረው ትምህርት ቤት አካባቢ ስለነበር ከትምህርት ቤት  ስንለቀቅ  እቤቷ  ድረስ  እሸኛት ነበር።

ከዮሃና ጋር ያለኝ ግንኙነት ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር ካለኝ ግንኙነት እንደሚለይ አውቅ ነበር። አይን ለአይን ስንተያይ ልቤ ይደነግጣል፤ ደብዳቤዋን ሳነብ ልዩ ስሜት ይሰማኛል፤ ደብዳቤዎቹን ለማንም አላስነብብም፤ ደብዳቤዎቹን ስንለዋወጥ ሰው ፊት አይደለም… ለየት ያለ ግንኙነት ነበር። ነገር ግን አንድም ቀን ከዮሃና ጋር ስላለን የተለየ ጓደኝነት አውርተን አናውቅም። ለአንድ አመት ያህል ጀርባቸው ላይ የአበባ ምስልና የፍቅር አባባሎች ባላቸው ወረቀቶች ላይ ደብዳቤዎችን ተለዋወጥን፣ በ Walkman MP3 የፍቅር ዘፈን ያለባቸውን ሙዚቃዎች አስተማሪ በማይገባባቸው ክፍለ ጊዜያት ተገባበዝን። አንዳንድ ጊዜ ስንኮራረፍ ሌላ ቀን ደግሞ  ትምህርት ቤት  ግቢ  ውስጥ  ለብዙ ሰዓት ብቻችንን ተቀምጠን እናሳልፋለን። ትምህርት ቤት ውስጥ ስለሚያጋጥሙኝ ጓደኞች ለሰፈር ጓደኞቼ ሳወራ ስለዮሃና አንድም ቀን አውርቼላቸው አላውቅም። ዮሃናንም ለሰፈር ጓደኞቿ ስለኔ አውርታላቸው እንደምታውቅ ጠይቄያት አላውቅም። የኔና የዮሃና ጓደኝነት ሚስጥር እንደሆነብኝ በተለያየ ቦታ ተመድበን በዛው ተራራቅን ተለያየን…

በተመደብኩበት ቦታ  የመጀመሪያ  አመት  እያለሁ  ከ“ቤቲ”  ጋር  የዶርማችን  ኮሪደር  ላይ ተዋወቅን፤ ያኔ ከዮሃና ጋር ስተዋወቅ ልቤ የደነገጠው ስሜት ተሰማኝ። እኛ ዶርም ስትመጣ እየተሽኮረመምኩ ስታየኝ እየደነገጥኩ ለሳምንታት ተወዛገብኩ። የሚሆነውን ሁሉ ከህሊናዬ መልስ በሌለኝ ጥያቄ ላለመፋጠጥ ተደበቅኩኝ። ቤቲ እኔ የሚሰማኝን ስሜት እንደሚሰማት ከአይኗ ተረድቻለሁ ግን ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም። አንድ ምሽት ለምን እንደሆነ ባላስታውስም ቤቲ እኔ ዶርም መጥታ ማውራት ጀመርን፤ የዶርም ጓደኞቼ space እና ዙረት ሄደው ነበር ከወሬያችን መሃል ራሴን ከቤቲ ጋር ስሳሳም አገኘሁት ድንጋጤ ጥያቄ ደስታ ሃፍረት አንድ ላይ ተፈራረቁብኝ። ምንም ሳናወራ ቤቲ ከዶርሜ ሮጣ ወጣች…

ስሙን ምክንያቱን ሳላውቀው የሃጢያተኝነት᎒ ራስን የመጥላት እና የተወሳሰበው ጥያቄዬ ከዛ ቀን ጀመረ። በዛን ወቅት የነበረኝን የፍቅር ጓደኛዬ “መክብብ”ን ማዋራት አስጠላኝም አሳፈረኝም። ከቤቲ ጋር ለጥቂት ቀናት ብንዘጋጋም በድብቅ መገናኘት ጀመርን። ሰው ፊት ብዙም እንደማይግባባ ብቻችንን ስንሆን ደግሞ ጨቅጫቆች ሆንን። በጣም የቀረብኳቸው ጓደኞቼ ሚስጥራቸውን ሲያካፍሉኝ እኔ ከመክብብ ጋር ያለኝን ግንኙነት ራሱ ማውራት ያስደብተኝ ነበር። ምን ላውራ?ለምን  ከቤቲ  ጋር  ያለኝ  ስሜት  እሱ  ጋር  እንደማይሰማኝ  መልስ  የለኝም።  ከሰኞ  እስከ ቅዳሜ ከቤቲ ጋር ስላለኝ ነገር በመጨነቅ አሳልፍና እሁድ ጠዋትን ቤተ ክርስቲያን ሄጄ “የዝሙት መንፈስ በዚህ መሃል አለ” ሲባል አልቆም የሚል የሲቃ እምባዬን አልቅሼ “ሁለተኛ አይለመደኝም፤ ይቅር በለኝ” ብዬ እመለሳለሁ። ለቤቲ የሚሰማኝን ስሜት የዶርም ጓደኞቼ በማይኖሩበት ሰዓት ድምጼን ከፍ አድርጌ በመጸለይ: ከቤቲ ጋር ያለንን ነገር ለማቆም ደግሞ በሃይል በመጨቃጨቅ እናሳልፍ ነበር። ለእረፍት ወደቤቴ ስመለስ የሚሰማኝ ስሜት፣ ይሄንን ስጽፍ እንኳን እምባዬን ማቆም አቅቶኛል እግዚአብሄርን የሚፈሩ ቤተሰቦቼን እንዳዋረድኳቸው፡  እድሜዬን  ሙሉ  ስለኔ  መልካም ሲመኙ የነበሩ ቤተሰቦቼን ያሳፈርኳቸው ይመስለኝ ነበር። የቤተሰብ የጋራ ጸሎት ሰዓት ላይ ላለመገኘት አምሽቼ እገባ ነበር፡ ከቤተሰብ  ጋር  አብሮ  መቀመጥ  ይጨንቀኝ  ነበር።  አብዛኛውን እረፍቴን እዛው ግቢ ውስጥ ሁሉ አሳልፌያለሁ። ከሴት ጋር እንዲህ አይነት ስሜት እንዴት ሊሰማኝ ይችላል አመቱን ሙሉ ከራሴ ጋር ተሟገትኩኝ… ከቤቲ ጋር ያለኝ ጓደኝነት በመሃል  ትምህርት ስታቋርጥ አቆመ ለምን እንዳቋረጠች በወቅቱ ስላልነገረችኝ “በኔ ምክንያት እኮ ይሆናል” በሚል ያሉብኝ ጭንቀቶች ላይ ሌላ ምክንያት ሆኖ ተደረበ።

አንድ ቀን ምሽት space ሄጄ ከኋላዬ ማንም እንዳይቀመጥ ግድግዳውን ተደግፌ ጉግል (Google) ላይ “I have a different feeling to my friend”, “women loving women”, “Is a woman loving a woman natural?” እና የመሳሰሉትን ጠየኩኝ።  እጃችሁን አልቧችሁ ያውቃል?በኮምፕዪተር ውስጥ ከመንግስተ ሰማያት የሚያዩኝ ሁሉ ነበር የመሰለኝ።

የሚቀጥል

 

Leave a Reply