ራስን ፍለጋ #2

ከባለፈው የቀጠለ

ጉግል ላይ ያየሁትን ነገር ማመን አቃተኝ:: መፅሃፎቻቸውን የማነባቸው የተለያዩ የሃይማኖቴ አስተማሪዎች በተለያዩ መድረኮች ሲያወግዙና ሲፀየፉ አየሁኝ:: ብዙተፈጥሮአዊ ነውየሚሉ ፅሁፎች ቢኖሩም እኔ ግን ሃጢያት ነው የሚለውን ተቀበልኩኝ:: ድብልቅልቅ ብሎብኝ ወደዶርሜ ተመለስኩኝ! ዶርም ገብቼ ራሴን መቆጣት ጀመርኩኝሁለተኛ እንዲህ አይነት ነውር! ንስሃ ገብቼ ወደ ቤተክርስቲያን ይበልጥ መቅረብ አለብኝ!” ለዶርም ጓደኞች እንኳን መንገር የማልችለውን ትልቅ ሸክም እነሱ እንዳይሰሙኝ በትራስ ራሴን አፍኜ ምርር ብዬ አለቀስኩኝ:: 

ትጉ ፀላይ እና ቤተክርስቲያን ታዳሚነቴ ጨመረ:: በአጋጣሚ የሴትን ውበት ሳደንቅ ራሴን ካገኝሁት ማታ ላይ ተንበርክኬ ንስሃ እገባ ነበር:: እፀልያለሁ፣ ራሴን እቆጣዋለሁ ከዛ ደግሞ አለቅሳለሁ፥ ለውጥ ግን የለም:: የወደድኳቸው ሴቶች የወንድ ጓደኛ ያላቸው ይሆናሉ ወይም ስሜቱ የኔ ብቻ ይሆናል  ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደኔ ግራ የገባትን እንጂ ማንነቷን በነፃነት ያመነች፥ ነገን ከሴት አጋር ጋር የምታስብ ሴት ዩዮኒቨቭርስቲ ቆይታዬ አልተዋወኩም:: ይሄም ይመስለኛል ሽክሜን ያከበደው፥ ኢንተርኔት ላይ እኔን የመሰለች (ጥቁር እና ኢትዮጲያዊ) ሴት አምለማየቴ ፈተናዬን ከባድ አድርጎታል:: ከራስ ሽሽት ብዙ ወንዶችን ተዋውቄያለሁ አብሬው የምሆነው ወንድ ጋር ሁሌም የሆነ ነገር ይጎድልብኛል ከሴት ጋር ስሆን ያለው ስሜት ጭራሽ አይሰማኝም፣ ከወንድ ጋር sex ማድረግ ስራ ይሆንብኛል ሲቀርም አይከፋኝም:: 

ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ ዮኒቨርስቲ እስከምመረቅ የነበሩኝ አመታት በቤተሰብ ፍርሃት፣ ራስን በመጥላት ከምንም በላይ ደግሞ ያመኝ የነበረውአምላክ እንዴት ያፍርብኝ!” የሚለው ስሜት ነው:: ሁሌም ፀፀት

ዩዮኒቨርስቲ ተመርቄ ስመለስ አዲስ ህይወት የምጀምር መስሎኝ ነበር ከአደረኳቸው ነገሮች ሁሉ ርቄ አዲስ ህይወት:: ብዙም ሳልቆይ የወንድ ጓደኛ ያዝኩኝ:: ከጊዜ በኋላ ምንም አዲስ ነገር የለም ሳላስበው ይደብረኛል፣ ከቤት ወጥቶ ማግኘት ስራ ይሆንብኛል:: ሁለታችንም አንድ እምነት ተከታዮች ስለነበርን ብዙ ጊዜ በቤተክርስቲያን እናሳልፍ ነበር:: ግንኙነታችን ለትዳር ይመስል ነበር:: አንድ አመት እንደቆየን በአጋጣሚ ከፂሆን ጋር በስራ ምክንያት ተዋወቅን በጣም መደዋወል ጀመርን.. መጀመሪያ የተሳሳምንበትን ቀን አልረሳውም፥ አንድ ቃል ሳልተነፍስ ቤቴ ሄጄ ፈጣሪዬንለምን አትገድለኝምአልኩት:: ጭንቅላቴን ይዤ ብዙ አለቀስኩ፥ ጓደኛዬን መበደሌ፣ ማንነቴን መረዳት አለመቻሌ እናሃጢያትተከትሎኝ መምጣቱ፥ አልጋችሁ ውስጥ እያለቀሳችሁ እንቅልፍ ወስዷችሁ ያውቃል? ብዙ ቀናቶቼ እንደዛ ሆነው ያልፉ ነበር:: አይኔ አብጦ እና ከባድ ራስ ምታት ይዞኝ እነቃለሁ:: 

ፂሆንን ሳውቃት ይበልጥ ኢንተርኔት ላይ በማንበብ የተሻለ እውቀት ቢኖረኝም እራስን ማመን ላይ ግን አልደረስኩም:: ከፂሆን ጋር ያለኝን ግንኙነት ለማቆም ብዙ ፀለይኩ፥ አንዳንዴም አብረን እንፀልይ ነበር:: ፀልየን ለአለመደዋወል እንወስናለን ግን እርሱም የእኔ እና የፂሆንን ግንኙነት አላስቆመውም:: 

ህይወት ምንም ያህል ብትሸሿት ጥያቄዋን አታቆምም፥ እኔም ሰላም የሌለውን ህይወቴን መምራት ሲደክመኝ ይመስለኛል ተረጋግቼ ስለማንነቴ ለማወቅ የፈለኩት:: ጥያቄዬ ስላላቆመ እንዲሁም ብዙ አመት የከደንኩት የህይወት ምዕራፍ ምንም ያህል ጊዜ ቢወስድክፈችኝማለቱ አይቀርም፥ በተለይ ማንነት ላይ ያለ ጥያቄ

ዛሬ ላይ ሆኜ እንዴት እራሴን ወደመቀበል እንደደረስኩ ሳስበው ይገርመኛል እንዲህ ነው ብዬ የምገልፀው አይደለም:: ቀስ በቀስ ማህበራዊ ድህረገፆች (social media) ላይ እንደኔ ያሉ ሰዎች በመተዋወቅ ብዙ ነገር ተማርኩ:: ይበልጥ ደግሞ በእምነት ውስጥ ሆነው ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ የሆኑ የእምነት አስተማሪዎች፣ ዘማሪዎች እንዲሁም ቤተክርስቲያናትን ማየቴ የማንነቴን እይታ ቀየረው:: እንደኔ ራሳቸውን ለመቀበል የታገሉ ብዙ የቤተ ክርስቲያን ሰዎችን ታሪክ አነበብኩኝ፥ ታሪካችን ከመመሳሰሉ የተነሳ ስለኔ ህይወት የተፃፈ ሁሉ ይመስለኝ ነበር:: 

ከፂሆንም ከወንድ ጓደኛዬ ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቁሜ ስለራሴ ለማወቅ ወሰንኩ:: ብዙ አመት የፈጀብኝን ፈተና ልጋፈጠው እና የምፈልገውን ላዳምጥ..ለጥቂት ጊዜ ከወንድም ከሴትም ጓደኛ ራሴን አገለልኩ:: 

ፀፀት የሞላበት ህይወቴን እኔን ስለሚመስሉ ሰዎች የተለያዩ ፅሁፎችን በማንበብ እና በማስተማር አደስኩት:: የመጣሁበትን መንገድ በእኔ አቅም ብቻ እንዳልተወጣሁት አምናለሁ፥ እራስን እንደማወቅ ትልቅ ደስታ የለም! ሁሉ አመት የፈጀብኝ ያደኩበት ማህበረሰብ መፈናፈኛ ስለማይሰጠኝ እንደሆነ አስባለሁ:: 

በእራሴ ብዙ ጥረት ካደረግኩ በኃላእንዴ ይሄ ነገር ልክ ነው እንዴ?” “የማልቀየረው ተፈጥሮአዊ ማንነት ስላለኝ ነው እንዴ?” አልኩኝ:: 

የእኔ የማንነትን መቀበል ታሪክ ይሄው ነው፥ ብዙ አመት እራስን ለመቀየር መጣር ከዛም የማነበው መፅሃፍ ቅዱስ ስለ ሰዶምና ጎመራ ሲያወራ ስለ ወሲባዊ ትንኮሳ እንጂ በፈቃደኝነት ላይ ስለተመሰረተ ተመሳሳይ ፃታ ፍቅር እንደማያወራ አወቅሁ:: የመፅሃፍ ቅዱስ ታሪክ በተፃፈበት ዘመን እንደነበሩበት ባህል እንደተፃፈም አምናለሁ:: እዚህ ላይ ለመድረስ ብዙ ፈተናዎችን ባልፍም ለሌላው ዛሬ ላይ ሆኜ መፃፍ መቻሌ እና ለሌሎች እራሳቸውን መቀበል እንዲችሉ ትንሽ አስተዋፆ ሊያደርግ መቻሉን ሳስብ ደስ ይለኛል::

እራስን የማወቅ ሂደት አያልቅም ነገር ግን በማንነቴ ለደቂቃ እንኳን የማልጠራጠር ሌዝቢያን (lesbian) ነኝ:: ከአራቱ እህቶቼ መካከል በጣም የምቀርባት እህቴን ስለማንነቴ ነገርኳት:: እኔን ብቻ ሳይሆን ከልብ የምወዳትን የፍቅር ጓደኛዬን በጣም ትወዳታለች:: 

ነገዬ ምን እንደሚመስል እና ማን ሰምቶ ምን እንደሚለኝ ሳልጨነቅ ዛሬዬን በደስታ እያሳለፍኩ ነው:: ይህ ማለት ምንም አይከፋኝም ማለት አይደለም፥ ኢትዮጲያ ውስጥ መኖር ሁሌም ፈተና ነው፥ ነገር ግን ራሴን ስጠላ ካሳለፍኳቸው አመታት ጋር ስለማይወዳደር እኔን ከሚመስሉ ጓደኞቼ ጋር እየተረዳዳን ህይወትን ለማጣጣም እንሞክራለን:: 

ስለነገ ደግሞ የፈጠረኝ ይጨነቅበት:: ራሴን ከነበርኩበት ጭንቀት አውጥቼ ሌዝቢያንነቴን ተቀብያለሁ::

ይሄ የአብዛኞቻችን ታሪክ ነው:: በዚህ ታሪክ ውስጥ እራሳችሁን ያገኛችሁ ወይም እንዳለፍኩበት ጭንቀት ውስጥ ያላችሁ የሚወዳችሁ፣ የሚቀበላችሁ እና የምታማክሩት ጓደኛ እንዲኖራችሁ ምኞቴ ነው::

Leave a Reply