ኩዊር እህቷን ከምትደግፍ ኢትዮጲያዊት ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ
ይህ ኩዊሮችን (LGBTQIA+) የሚደግፉ ሰዎች ታሪካችውን እንዲያካፍሉ የጀመርነው የመጀመሪያው ቃለምልልስ ነው:: ቃለ ምልልሱ የተካሄደው በአዲስ አበባ ከጥቂት ቀናት በፊት ነው:: ቃለምልልሱን የሰጠችን በአዲስ አበባ ተወልዳ ያደገች ስትሆን ስለእህቷ ሌዝቢያንነት ስታውቅ ከ15 አመት በላይ ሆኗታል:: ይህ ቃለ-መጠይቅ ከጊዜ አንፃር እንዳንድ ጥያቄና መልሶች ተቆርጠው እንዲያጥሩ ተደርገዋል።
ጥያቄ: አንድ የቤተሰብሽ አባል ሌዝቢያን መሆኗን ስታውቂ ምን ተሰማሽ?
በጣም አዝኜ ነበረ ምክንያቱም ኢትዮጲያ ውስጥ ምን ያህል ከባድ እንደሆነና ለሷም እንደሚከብዳት ስለተረዳሁኝ በጣም አዝኜ ነበር::
ጥያቄ: ጌይ ሌዝቢያን ትራንስ ኩዊር መሆንን ባጠቃላይ እንዴት ታይዋለሽ?
ሰው የመረጠውን መሆን ይችላል፣ ስለዚህ እዛ ላይ ምንም ቅሬታ የለኝም::
ጥያቄ: አብዛኛውን ጊዜ ነገሮችን ባህልና ሃይማኖትን መሰረት በማድረግ የመፈረጅ ነገር አለ እና አንቺ መጀመሪያ ላይ እንዴት ነበር ያየሽው?
ለኔ ይህንን የሚሉ ሰዎች መፅሃፍ ቅዱስን በደንብ አያውቁትም ብዬ ነው የማስበው ምክንያቱም እግዚአብሄር ሁሉንም አንድ አድርጎ ፈጥሮ፤ አንዱን ወዳጅ አንዱን ጠላት አያደርግም:: በኔ እምነት አምላካችን ሁላችንንም እኩል ይወደናል ብዬ ነው የማስበው፤ ቤተእምነት የሚያስተዳድሩ ሰዎች ግን ሰውን እንደፈለጋቸው ለማድርግ ለነሱ የሚያስኬዳቸውን መንገድ ይመርጣሉ:: [እኔ ግን] ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ እግዚአብሄር ያዳላል ብዬ አላምንም::
ጥያቄ: ስለ ጌይ ሌዝቢያን ትራንስ ባጠቃላይ ስለኩዊር ሰዎች ያለሽ አመለካከት እህትሽ ሌዝቢያን መሆኗን ካወቅሽ በፊት እና በኋላ ለውጥ አለው?
እኔ እህቴ ከመንገሯ በፊት ምን እንደሆነ ብዙ ነገርም አይገባኝም እውነት ለመናገር፣ ምክንያቱም ያላቸው ፈተና ምንድነውም አላውቅም:: እህቴ መሆኗን ሳውቅ ግን ምንድነው የሚለውን ነገር ስጠይቅ ፣ ራሴ ለማወቅ በተቻለኝ ስሞክር ብዙ የተለየ ነገር የለውም::
ጥያቄ: እስኪ አብራሪልን
የእኛ ሃገር ህብረተሰብ ጥራዝ ነጠቅ አመለካከት አለው ብዬ ነው የማምነው ምክንያቱም ሃይማኖት ይላል ግን ከሃይማኖቱ ጋር ደግሞ የሚመቸውን መርጦ የማይመቸውን የሚተው ህብረተሰብ ነው:: ስለዚህ ማንም ሰው ተነስቶ ምንድነው የሚለውንም ነገር ሳይጠይቅ ቶሎ ብሎ ሰዎችን ወደመናገር፣ አስተያየት ወደመስጠት፣ ወደመብት መጋፋት ነው የሚሄደው ግን እዚኛው ጉዳይ ላይ ብቻ አይደለም:: ህብረተሰቡ ከሚያምንበት ነገር ውጪ የሚያደርግን ሰው መቀበል በጣም ይከብደዋል፣ ይሄ ደግሞ ሁሉም ሰው ጠላነው ብሎ የሚለው ነገር ስለሆነ ይሄ ነገር ከታወቀ — የእኛ ማህበረሰብ ሰውን መግደል ከባድ ነው ብሎ ስለያማስብም ምንም ነገር ሊያደርግ ይችላል:: እሱ ላይ ስጋት አለኝ ምክንያቱም ሰው ወጥቶ እንደልቡ ራሱን መሆን አለመቻሉ፣ ራሱን አለማሳወቁ፣ ራሱ የሚፈልገውን አለመሆኑ [አግባብ አይደለም]::
በዛ ላይ እኛ ሃገር ሰው በራሱ መብት እንዳለውም ህብረተሰቡ አያውቅም:: ይሄ ለሌላ ሰው ብቻም ሳይሆን የራሱንም መብትና ግዴታውንም አያውቅም፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ ብዙ ችግሮች የደረሱብን ይመስለኛል፤ እንደ ሃገር እና እንደ ህብረተሰብ::

ጥያቄ: ስለ እህትሽ ስታስቢ ፍርሃት አለሽ?
አዎ! አንደኛ እህቴ ራሷን ሆና አለመኖሯ፣ ሁለተኛ የምትፈልጋቸውን ነገሮች አለማድረጓ፣ ሶስተኛ ደግሞ ወጥታ በምትናገራቸው ነገሮች ውስጥ የሷን ምንነት ለማወቅ ብዙ ሰዎች ጥረት ሲያደርጉ እና ከዚያ ወዲያ ቢያውቁ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ስገምት ከማውራት ጀምሮ እንኳን ነፃነት እንደሌላት ይገባኛል:: ይሄ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ያለውን ነገር ደግሞ ቢያውቁ ምንም ነገር ከማድረግ አይመለሱም፣ ከመግደልም ሊሆን ይችላል፣ መግደል የማይደርሱት ደግ የምንላቸውም የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ ብዙ ጫና ያደርሱባታል ብዬ አስባለሁ:: ምክንያቱም እኔ አብሬያት በምሆንባቸው ጊዜዎች ብዙውን ተግዳሮቷን አያለሁ፣ እንደውም ለሷ በጣም አጠነቀቃለሁ::
ጥያቄ: ኩዊር ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ይቀበላሉ ወይም ይደግፋሉ ብለሽ ታስቢያለሽ?
አላስብም! አንዳንዴ በነሱም ላይ አልፈርድም ምክንያቱም ምን እንደሆነም አይገባቸውም.. ህብረተሰባችን ውስጥ ሴት እንኳን መብት የላትም የምትፈልገውን ሰው የማግባት፣እስከምትፈልገው ድረስ መቆየት፣ አለማግባት፣ የምትመርጠውን ስራ መስራት፣ መውለድ አለመፈለግ ህብረተሰባችን አይገባውም — እንኳንስ ኩዊር ነኝ ብላ አንድ ሴት ብትመጣ — አይገባቸውም:: አንዱን አግቢና ውለጂ አለቀ:: የእኛ ማህበረሰብ ግቡ እኮ አግብቶ መውለድ ነው እንጂ ሌላ ህይወት ያለ አይመስለውም:: ስለዚህ በነሱ በኩል መቶ በመቶ መፍረድም ይከብዳል:: ስለማያውቁትና ስለማይገባቸው ነው፤ ቢገባቸው መቼም ሁሉም ሰው የራሴ የሚለውን ሰው ለመረዳት የሚፈልግ ይመስለኛል::

ጥያቄ: ኢትዮጲያ ውስጥ እንዳንቺ ኩዊር የቤተሰብ አባል ያላቸው ሰዎች እንዴት ኩዊር የቤተሰብ አባሎቻቸውን መደገፍ ይችላሉ ብለሽ ታስቢያለሽ?
ያንን ሰው በማዳመጥ፣ ህመሙን በመረዳት፣ ሰው የመረጠውን መሆን አለመቻሉ ትልቅ ዋጋ ስለሚያስከፍል ያ ሰው የሚፈልገውን እንዲሆን ማድረግ አለባቸው ብዬ አምናለሁ::
በኔ እምነት ማንም ሰው ራሱን የመሆን መብት አለው ስለዚህ እውነት የራሳቸውን ሰው የሚወዱ ከሆነ ያ ሰው የሚፈልገውን እንዲሆን መፍቀድ ነው:: ያለንበት ማህበረሰብ አስቸጋሪ ስለሆነ ለምሳሌ አደባባይ ላይ ወጥቶ ግልፅ የሆነ ነገር አለማድረግ ዋጋው ከፍተኛ ስለሆነ .. ከዛ ውጪ ግን ቤተሰብ አመቺ እና የማያጋልጥ በሆነ መንገድ ከማንኛውም ጥቃት ጥበቃ ቢያደርግላቸው ጥሩ ነው:: ሌላው ነገር ግን ይሄ እኮ በሽታ አይደለም፣ አንድ ሰው መረጠ፤ እኔም እመርጣለሁ — በወንድ ውስጥ የተለያየ ምርጫ አለኝ — ያም ሰው እንዲሁ ምርጫ አለው:: እንደሰው ምርጫን መጋፋት የለብንም::
ጥያቄ: ኩዊር ለሆኑ ኢትዮጲያውያን ምን ትመኝላቸዋለሽ?
እንደሌላው አለም ነፃ ሆነው ከሚፈልጉት ሰው ጋር እንዲኖሩ፣ የሚፈልጉትን መንገድ እንዲመርጡ — ሴትና ወንድ እንደፈለጉት እንደሚመርጡት ሁሉ ሰዎች ናቸው የመረጡትን መንገድ ደግሞ እንደማንኛውም ሰው በነፃነት መኖር አለባቸው:: ሌላ ሰው የሚገባው ሁሉ ይገባቸዋል:: ማንም ሰው የእነሱን ምርጫ ተጋፍቶ በሌላ መንገድ እንዲሄዱ ማድረግ የለበትም፤ ማድረግ መፈለግም የለበትም::
What a lucky soul she is to have a supportive sibling. It was a good reading too!
Thank you for reading, Dinbushea. She is indeed lucky and we hope more of our family members will continue to become our allies. And also that our allies will be more vocal about their support for us.
Hey. This is excellent! Awesome to have such a supportive sister. Can I borrow her for a week 😀? Loved the part where she says “Let’s understand being queer is a lifestyle choice, not an illness!”
Yes, it is awesome to have sibilings who are supportive. We will ask if she is willing to be borrowed:)
Thank you for reading, Rebecca.