“በሌዝቢያን ግንኙነት ውስጥ ጥቃት ምን ይመስላል?”

በማህበራዊ ሚዲያ ፃታዊ ጥቃትን የያዙ ዜናዎችን ማየት በጣም የተለመደ ነው:: አሁን ደግሞ ከኮሮና ጋር በተገናኘ በዚህ ዙሪያ ላይ የተለያዩ ዘገባዎች ይወጣሉ::  በአብዛኛው ፃታዊ ጥቃት የሚባለው አሲድ የተደፋባት ሴት ወይም የተለያየ አካላዊ ጥቃት የደረሰባት ሴት ብቻ ተደርጎ ይወሰዳል፣ ነገር ግን አንድ ሴት አካላዊም እና ስነ ልቦናዊም ጥቃት ሊደርስባት ይችላል:

ፆታዊ ጥቃት በተቃራኒ ፃታ አፍቃሪያን መካከል እንደሚፈጠረው ሁሉ ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪያን ሰዎች መሃልም ይፈጠራል:: በአብዛኛው ሌዝቢያን ሴቶች ግንኙነት ውስጥ ሲገቡ ምንም አይነት ጥቃት እንደማይደርስባቸው ተደርጎ ይታሰባል:: 

በሌዝቢያን ግንኙነት ውስጥ ጥቃት ምን ይመስላል?

• በግንኙነት ውስጥ በገንዘብ መቆጣጠር (ለመግዛት መሞከር)፥ እንዲህ አይነቱ ጥቃት አንደኛዋ የተሻለ ገቢ ያላት ከሆነች፣ ሌላኛዋ ለምትወስናቸው ውሳኔዎች አዛዥ ሆና መገኘት ማለት ነው:: የሆነ ጊዜ አንድ ጓደኛዬ የነገረችኝ ታሪክ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል፥

“ትንሽዬ ቤት ተከራይቼ ነበር የምኖረው እና ከሷ ጋር በግንኙነት ትንሽ እንደቆየን የተሻለ ቤት አብረን እንኑር ብላኝ አብረን መኖር ጀመርን:: ከኔ የተሻለ ስራ ስለምትሰራ ብዙውን የቤታችንን ወጪ እሷ ነበረች የምትሸፍነው ነገር ግን አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በተደጋጋሚ እሷ ባትኖር ደህና ኑሮ እንደማልኖር ትነግረኝ ነበር፣ ችግሩ እየባሰ የመጣው ቤት ውስጥ የምንወስናቸው ውሳኔዎች ሁሉ በሷ ሆነ:: ያለሷ ፍቃድ ምንም ነገር መግዛትም ሆነ ማድረግ አልቻልኩም፣ የበታችነት ስሜት ተሰማኝ::” 

እንዲህ አይነት ብዙ ታሪኮች አሉ:: የተሻለ ገቢ የሌላቸው ሴቶች በእንዲህ አይነቱ ግንኙነት ውስጥ ለብዙ ጊዜ ይቆያሉ:: ሌዝቢያን ጓደኞቻችንን በትምህርት እና በስራ በመደገፍ ራሳቸውን እንዲችሉ መፍትሄ ለመሆን ብንሞክርስ?

• በእድሜ የምትበልጥ ሴት ከ18 ዓመት በታች ያለችን ልጅ ወደ ወሲብ መገፋፋት(ማማለል)

ከ18 ዓመት በታች ካለች ልጅ ጋር ግንኙነት መፈፀም ወይም ለወሲብ መገፋፋት ጥቃት ነው:: ከ18 ዓመት በታች ያለች ሴት ስለራሷ በራሷ መወሰን የምትችልበት እድሜ ላይ ስላልደረሰች ግንኙነት ለመፈፀም መጎንተል ጥቃት ነው::

 • በመጠጥ ወይም በአደንዛዥ ዕፅ ቁጥጥር ስር ያለችን ሴት ወሲብ መፈፀም

በስካር ላይ ያለች ሴት ፈቃዷን ለመግለፅ በትክክለኛው አዕምሮ ላይ ስላልሆነች ዝምታዋ እንደ “እሺ” መወሰድ የለበትም::

በእያንዳንዱ አካሄዳችን የሰውን ፈቃድ ማረጋገጥ ተገቢ ነው:: አንድ ሰው ስልክ ስለሰጠን ለወሲብ ዝግጁ ነው ማለት አይደለም:: ገላጣ ቦታ ከተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ አጋር ጋር መታየት ስለሚያስፈራ ሆቴል ሄደን እንዝናና ማለት ለsex መጋበዝ ማለት አይደለም:: በተጨማሪም አንድ ሴት አብራን ለመኖር ስለወሰነች እኛ በፈለግንበት ጊዜ ሁሉ ለsex ፈቃደኛ ናት የሚለው አስተሳሰብ ልክ አይደለም::

ስነልቦናዊ ጥቃቶች ደግሞ አፀያፊ ንግግሮችና ስድቦችን የሚያካትቱ፣ ስሜት ጎጂ ጥቃቶች ናቸው:: እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ከብዙ በጥቂቱ ለመግለፅና የተለያዩ ገፆችን ለማሳየት እንጂ፤ እነዚህ ብቻ ሆነው አይደለም::

ብዙ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን በሚዲያ ብናይም ፍትህ ሲሰጣቸው አናይም:: ኩዊር ሰዎች ደግሞ ፃታዊ ጥቃት ሲደርስባቸው የህግ/ህክምና ከለላ ስለሌለ ችግራችንን ይበልጥ የከፋ ያደርገዋል:: ይህም ማለት አንድ ሌዝቢያን ሴት የፍቅር አጋሬ ጥቃት አድርሳብኛለች ብላ ፖሊስ ጋር መቅረብ ስለማትችል ሚስጥር ሆኖ ይቀራል:: ከህግ እና ህክምና ድጋፍ አለማግኘት በተጨማሪ አብዛኞቻችን  የተቃራኒ ፃታ አፍቃሪ ጓደኞቻችንም ሆኑ ቤተሰቦቻችን ሌዝቢያን መሆናችንን ስለማያውቁ፥ የእነሱን ምክርና ድጋፍ ማግኘት የማይታሰብ ነው:: 

እነዚህን ጥቃቶች ለማስቀረት በጓደኝነታችን ውስጥ ግልፅ ውይይት ማድረግ ይኖርብናል፣ ሁልጊዜ ማንነታችንን ልንፈትሽም ይገባል:: ሰውን በሰውነቱ በማክበር፣ አለመግባባቶችን በሃይል ሳይሆን በውይይት ለመፍታት በመሞከር፣ ከሰው ፈቃድ ውጪ የሆነን ነገር በማስወገድ ጤናማ ግንኙነትን መፍጠር ይቻላል::

2 thoughts on ““በሌዝቢያን ግንኙነት ውስጥ ጥቃት ምን ይመስላል?””

  1. በውነት ይህ ጥሩ ጠቃሚ ፅሑፍ ነው። ከዚህ በፊት በብዙም አስቤበት የማላውቀው ግን የኖረ እና የሚከሰት የግንኙነት ነጥቦች አንስታችሁ አብሮ መሆን ማለት ምን እንደሆነ ለማስረዳት ጥራችኅል። ግን በተለይ ይህ ኮሚውኒቲ አነስተኛ ስለሆነ ብዙ ነገሮች አንደኖርማል ይወሰዳሉ ለምሳሌ butch የሆነች ሴት ፍቅረኛዋን ልክ typical የሀበሻ ባል የሚያሳየውን አይነት መጫን ስታከናውን ይታያል ምንአልባት የአስተዳደጋችን ተፅዕኖ ይሆናል ግን አኛ በፆታ ምርጫችን አንለያይ አንጂ ግንኙነት መፍጠር ተመሳሳይ process ነው የምንከተለው ስለዚህ እኛ ለእኛ ካልተሳስበን በውነት ብዙ ነገር ይብድናል። በዚህ ላይ ምንም አይነት support systems የለንም። ምስጋና ለፅሑፍ አቅራቢዎች ቻው።

    1. ፅሁፉን ጊዜ ወስደሽ ስላነበብሽው እናመሰግናለን:: እንዳልሽው ግንኙነቶች ሁሉ በተቃራኒ ፃታ አፍቃሪያን የተቃኘ ስለሆነ የራሳችን የሆነ መማማሪያ መፍጠር ይኖርብናል:: በጓደኞቻችን መሃል ግልፅ ውይይትን ማዳበር እና ችግሮችን መወያየትን ልማድ ማድረግ ከብዙ በጥቂቱ መፍትሄ ሊሆኑ ይችላሉ::

Leave a Reply