ኩዊር ኢትዮጵያ: አዳዲስ እንቅስቃሴዎች

ውድ LBTQ ኢትዮጵያውያን

እንኳን ወደ ኩዊር ኢትዮጵያ መጣችሁ!

ኩዊር ኢትዮጵያን ከአንድ አመት እና ጥቂት ወራት በፊት የጀመርነው LBTQ የሆኑ ሴቶች ጋር ለመተዋወቅ፣ ለመወያየት እና በኢትዮጵያ ላሉ LBTQ ሴቶች የኦንላይን ማህበራዊ አብሮነት መንፈስን ለመፍጠር ነው:: ከተለያዩ ኩዊር ኢትዮጵያውያን ጋር ለመወያየት ትልቅ ተስፋ የነበረን ቢሆንም ያገኘነው ምላሽ ከጠበቅነው በላይ ነው:: በኢሜል፣ በፌስቡክ መልዕክትና ብሎጋችን ላይ ስላካፈላችሁን ሃሳቦች፣ እንዴት እንደረዳችሁ ስለገለፃችሁልን እና መልካም ምኞቶች ሁሉ እናመሰግናለን:: 

በነበረን አበረታች ቆይታ ላይ ይህ የማህበራዊ አብሮነት መንፈስ በኢትዮጵያና ዳያስፖራ ላሉ LBTQ ሴቶች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተረድተናል:: በትብብር ያደረግነው የኦንላይን ግምገማ ቅኝት (Assessment survey) የሚያሳየው በእምነትና ፆታዊ ተማርኮ፣ ከሌሎች ኩዊር ሰዎች ጋር መተዋወቅ፣ ራስን መቀበል፣ አዎንታዊ ኩዊር ታሪኮች እና የአዕምሮ ጤና ዙሪያ ጥልቅ ግንዛቤ ማስጨበጫ እና ውይይት እንደሚያስፈልግ ነው:: 

ከተሰጡን አስተያየቶች በመነሳት ተጨማሪ ስራዎችን ይዘን እንደመጣን ስንነግራችሁ ደስታችን ወደር የለውም – ፖድካስት፣ የኦንላይን መፅሄት፣ የኦንላይን አርት ምሽት፣ ውይይቶች እና የኦንላይን የባለሙያ ምክር አገልግሎቶች በሚቀጥሉት ወራት እንጀምራለን:: 

ኢትዮኩዊር የተሰኘው ወርሃዊ ፖድካስታችን በአውሮፓውያን አቆጣጠር የጃንዋሪ ወር መጨረሻ የምንጀምር ሲሆን በኢትዮጵያና ዳያስፖራ የሚገኙ LBTQ ሴቶች ህይወት ላይ የሚያተኩር ነው:: በሶስት ወር አንዴ የምናሳትመው መፅሄታችን የተለያዩ ኩዊር ጉዳዮችን በጥልቅ ያስሳል:: ወርሃዊው የአርት ምሽታችን የተለያዩ ኩዊር አርቲስቶች በግጥም በሙዚቃና ዳንስ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበትና የምንዝናናበት ምሽት ይሆናል:: በተጨማሪም ኩዊር የሆኑ ኢትዮጵያውያን በአዕምሮ ጤና ላይ የባለሙያ ምክር ለሚፈልጉ በኩዊር ጉዳዮች ላይ ራሳቸውን ብቁ ካደረጉ የሃገር ውስጥ የአዕምሮ ባለሙያዎች በአማርኛ እና እንግሊኛ ቋንቋ መወያየት እንዲያስችል ነፃ መንገዶችን አመቻችተናል::

በተለያዩ የማህበሪያ ሚዲያ ላይ መጥተናል ፤ ይከታተሉን

በእነዚህ አስፍተን ልንጀምር ባቀድናቸው ስራዎች ትልቅ፣ ሁሉንም ያካተተ እና ብቁ LBTQ ማህበረሰብን አብረን መፍጠር እንደምንችል ተስፋ እናደርጋለን::

እስካሁን ለነበራችሁ እገዛ እያመሰገንን በቀጣይም ከእኛ ጋር እንድትሆኑ እንመኛለን

መልካም ጊዜ

ኩዊር ኢትዮጵያ

Leave a Reply