የፍቅር አርበኛ: የሌዝቢያን ፍቅረኛሞች ህይወት በአዲስ አበባ

የሁለት ሌዝቢያኖች ፍቅር በእሳት ውስጥ እንኳን ጠንክሮ ሊቆም እንደሚችል ተማርን

“ለእራታችን የያዝኩትን ቦታ ሰርዥዋለሁ” አለችኝ ፍቅረኛዬ ለፍቅረኛሞች ቀን በምወደው ሬስቶራንት ልትጋብዘኝ የነበረው እቅዷ ስላልተሳካ እየተበሳጨች:: ለእራት ቦታ ለመያዝ ስትደውል የሬስቶራንቱ መሃል ላይ ያለው ወንበር ብቻ ነፃ እንደሆነ ነገሯት:: የሁለት ሴቶች የፍቅረኛሞች ቀንን በሚያከብሩ የተቃራኒ ፃታ አፍቃሪያን ጥንዶች ተከቦ መቀመጥ ሃሳቡ ከበዳት:: ጥርጣሬን የሚያመጣ ማንኛውንም ሁኔታ ማስወገድ ትልቁ ስራችን ነው:: ገብቶኛል:: ያንን ምሽት ጥርጣሬ እና ፍራቻ በሌለባት ትንሿ ቤታችን አሳለፍን፤ ሁሌም ካለውና በየጥጋጥጉ ከሚጮኸው የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪያን ጥላቻ ለጊዜው ተከልለን ጥሩ ጊዜን አሳለፍን::

በአዲስ አበባ ያለው የእኔ እና የፍቅረኛዬ ኑሮ እውነታው ይሄ ነው:: ከቤታችን ስንወጣ እያንዳንዱን እንቅስቃሴያችንን ሁለት ጊዜ ማሰብ፣ ሰዎች አብረን እንዳለን እንዳይጠረጥሩን መጠንቀቅ፣ በፍቅር አይን ላለመተያየት ራሳችንን መቆጠብ፣ ሰልፊ ፎቶ እንኳን ስንነሳ ምን ያህል እንደተቀራረብን ማመዛዘን:: ከሌሎች ተቃራኒ ፃታ አፍቃሪ ሴት ጓደኞቻችን ጋር በነፃነት የምንደንሰውን እርስ በእርስ ለመደነስ መፍራት ወይም ከነሱ ጋር ክንድ ለክንድ ተያይዘን የምንሄደውን እርስ በእርስ አለመያያዝ፣ ሌሎች ባሉበት ስልክ ከማውራት መልዕክት መላላክ፣ ወይም የቅርብ ጓደኛ እንደሆንን ለማስመሰል መሞከር አንዳንዴም የስልኩን ድምፅ መቀነስ ጥቂቶቹ ናቸው:: 

ይሄ ንፁህ እና ጥብቅ የሆነ የፍቅር ግንኙነት ነው፣ በዝምታ ውስጥ የሚያድግ እና የሚሰፋ ፍቅር፣ ከብዙ እይታዎች የራቀ፣ ነገር ግን በልቤ ውስጥ ግልፅ ሆኖ ካወኩዋቸው ፍቅሮች ሁሉ የተለየ ፍቅር ማፍቀር እንድችል አስተምሮኛል::

እኔ እና ፍቅረኛዬ ስንተዋወቅ አዲስ አበባ እየኖሩ ጤናማ እና ዘላቂነት ያለው የፍቅር ግንኙነትን ማሰብ አዳጋች ነበር:: በዙሪያችን ያለ ሁሉ ሊሰብረን እየሞከረ እንዴት የሚያድግ ግንኙነትን ማሰብ ይቻላል? ግፊቱን መቋቋም እንችላለን ብለን አላሰብንም ነበር:: ነገር ግን ጊዜ ትክክል እንዳልሆንን አስገነዘበን:: የሁለት ሌዝቢያኖች ፍቅር በእሳት ውስጥ እንኳን ጠንክሮ ሊቆም እንደሚችል ተማርን:: በምንገለልበትና ተቀባይነት በማናገኝበት ቦታ ላይ ለእርስ በእርሳችን ፍቅር መስጠትን መቀጠላችን ለራሳችን ያስደንቀናል::

ከእኛ ቆራጥነት ባሻገር እኛን የረዱን ተጨማሪ ነገሮች እንዳሉ አምናለሁ:: አብዛኛውን ጊዜ ትንንሽ ነገሮች ናቸው፤ ለእርስ በእርሳችን ጊዜ መሰጣጣት፣ የምንወዳቸውን ነገሮች አንድ ላይ ማድረግ ምንም እንኳን ይሄ ማለት ብዙ ጊዜ ቤት ውስጥ ማሳለፍ ማለት ቢሆንም:: ይሄ ደግሞ የተለያዩ ኩዊር ነክ የሆኑ መፅሃፎች፣ ፊልሞችና የአርት ስራዎች ከሰፊዊ የኩዊር ማህበረሰብ ጋር አስተዋውቆናል፤ ይሄም ጉዞአችን የእኔ እና የእሷ ብቻ እንዳልሆነ ያስታውሰናል:: በይበልጥ ግን በዙሪያችን ያሉ ጓደኞቻችን ሰላም፣ ጥንካሬ እና ብርታት ሆነውናል:: ለደህንነታችን ያሰጋል ያልናቸውን እና የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪያንን ጠል የሆኑ ጓደኝነቶችን ከራሳችን አርቀናል::  ስለእኛ የማያውቁ ጓደኞቻችን ጋር ይሄን ማንነታችንን ብንደብቅም ግን ደግሞ ሙሉ በሙሉ ራሳችንን ሆነን እንድንውል የሚያደርጉን በጣም የምንወዳቸው ጥቂት ኩዊር ጓደኞች አሉን:: እኛን የሚቀበሉ ተቃራኒ ፃታ አፍቃሪ ጓደኞቻችን በኩዊር ጥላቻ በተዘፈቀ ህብረተሰብ ውስጥ ለሰው ማንነት ዋጋ የሚሰጡ እንዳሉ ያስታውሱናል::

ራሳችንን ደብቀንና ራሳችንን እንዳንሆን በሚያደርጉ ብዙ ፈተናዎች እንዳለፍን አይጠረጠርም:: አልፎ አልፎ ራሳችንን መሆን የማንችላቸው ቦታ ላይ ስንሆን ፍቅረኛዬን “ምን ያህል እንደማፈቅርሽ ለሌሎች መናገር አለመቻሌ ያሳዝነኛል” እላታለሁ:: “በጣም! ግን ፍቅራችን እውነት ነው:: ይሄ ምኑንም ሊቀይርብን አይገባም” ትለኛለች፤ ፍቅራችን የማንንም ማረጋገጫ አይፈልግም ብላ ታፅናናኛለች:: ይሄ ንፁህ እና ጥብቅ የሆነ የፍቅር ግንኙነት ነው፣ በዝምታ ውስጥ የሚያድግ እና የሚሰፋ ፍቅር፣ ከብዙ እይታዎች የራቀ፣ ነገር ግን በልቤ ውስጥ ግልፅ ሆኖ ካወኩዋቸው ፍቅሮች ሁሉ የተለየ ፍቅር ማፍቀር እንድችል አስተምሮኛል:: ባልደብቀው ብዬ እመኛለሁ? በደንብ! ምንም እንኳን ዕለት ዕለት ከብዙ ተግዳሮቶች ጋር ብፋለምምና የተሻለ ቀን ይመጣል ብዬ ተስፋ ባደርግምና ጥልቅና ውብ በሆነ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ በፍፁም መሰጠት መሆን ምን ማለት እንደሆነ ያለኝን መረዳት እያሰፋው ያለውን የፍቅር ሙቀት አጣጥሜ አልጠገብኩም።

Leave a Reply