ኢትዮኩዊር ፖድካስት: የድብቅ ፍቅር ማስታወሻ

ውድ ሜላትና ሳሮን

“እንዴት ሰው ይሄንን ችግር አለበት ብሎ ያስባል?” ፍቅረኛዬ ብርዳማ በሆነ ቀን ላይ በሞቀው አልጋችን ላይ ዝም ብለን በቶኒ ሞሪሞሰንን አገላለፅ “ጣፋጭ፣ ያላለቁ አረፍተነገሮች ያሉበት ወሬ፣ የቀን ህልም እና መግባባት ከሚያስደስተው ይልቅ አለመግባባቶች” ላይ እያለን በግርምት ጠየቀችኝ::

ምንም እንኳን ይሄ የሆነው ከብዙ አመታት በፊት ቢሆንም ቤታችሁ ስለ ፍቅራችሁ እና ህይወታችሁ ለኢትዮኩዊር ፖድካስት ቃለመጠይቅ ላደርጋችሁ ስቀመጥ የተሰማኝ ይሄ ነው::

በእያንዳንዱ ጥያቄ ስለፍቅራችሁ ስትነግሩኝ ለእርስ በእርስ ያላችሁን እንክብካቤ በቀላሉ ማየት ችያለሁ:: ታጋሽ እና መረዳት ያለበትን ፍቅራችሁን እያየሁ የሁለታችሁን ፍቅር በማይገባ መልኩ ያከበደባችሁ አለም ላይ አለመናደድ አልቻልኩም:: 

ቤታችሁ ስደርስ የተሰማኝ ሁሉም ነገር የተለመደ እንደሆነ ነው:: ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ የምትኖሩት የተለመደ አኗኗር መሆኑ፤ እናንተም የተገናኛችሁበት መንገድ፣ እንዴት እንደተፋቀራችሁ እና የእየለት ኑሯችሁ እንደማንኛውም ፍቅረኛሞች የተለመደ ታሪክ ነው::

በውይይታችን መሃል እንዴት  ሁለታችሁም በምታውቋቸው ጓደኞች ኦንላይን እንደተዋወቃችሁ ስትነግሩኝ ይሄ እንደማንኛውም የዘመኑ ፍቅረኛሞች ታሪክ ነው ብዬ አሰብኩኝ:: እንዴት እንደተዋወቃችሁና የመጀመሪያ ቀን ስትገናኙ ያላችሁን ትውስትታ ስታወሩልኝ ህልም በሚመስል መልኩ ስትተያዩ በሁለት ፍቅረኛሞች መሃል ያለን ውይይት በስውር እያዳመጥኩ እንዳለሁ እንደተሰማኝ አልክድም::

ሜላት፥ በውይይታችን ላይ ጠለቅ ብለን ስንገባ ድፍረትሽን አደነቅኩት:: እንዴት አንድ ሴት የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪያን ጠል በሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ ስጋቱን ወስዳ ያውም የወደደቻትን ልጅ ኩዊርነት ሳታውቅ ስሜቷን መግለፅ ቻለች? ምናልባት ፍቅር ግማሹ የእምነት መኖር ነው:: ቆራጥ ነሽ፤ ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ በመሆንሽ እስከ 15 አመት ሊያሳስርሽ በሚችልበት ሃገር ላይ ያንን  መወሰንሽ::

ፍቅር በግማሹ ደግሞ የማያውቁትንም መመርመር ነው:: ሳሮን፥ አንቺም ደፋር ነሽ! ከዚህ በፊት ከሴት ጋር ግንኙነት ባይኖሽም..ስሜትሽ ምን ማለት እንደሆነ ለመመርመር መፍቀድሽ:: ሁለታችሁም ደፋር ናችሁ፤ ኩዊር ጠል የሆነውን ህብረተሰብ ንቃችሁ ለእርስ በእርሳችሁ መሆን መቻላችሁ:: ለኩዊር ሰዎች የጦር ሜዳ በሆነችው ኢትዮጵያ እንደሁለት ሴቶች ፍቅራችሁን መቀጠል መቻላችሁ ወኔያችሁን ያሳያል፤ ሁለት የፍቅር አርበኞች ናችሁ::

ምንም እንኳን የፍቅር ታሪክ ውስጥ መግባት የሌለበት ርዕስ ቢሆንም ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ ጠል በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ ስለሆነ የምንኖረው  ከተቃራኒ ፃታ አፍቃሪነት ውጪ ያለን ማንኛውም ዝንባሌ አጥብቆ የሚፀይፍና የሚከለክል ማህበረሰብ መሃል የሚወለደውን ፍራቻ፣ ጭንቀር፣ ራስን መቀበል፣ ስጋት እና የደህንነት አለመፅናትን እያነሳን አወራን::

በነበረን የ45 ደቂቃ ውይይት በተለያዩ የስሜት ማማዎች ላይ አስወጥታችሁኛል፤ ደስታ፣ ንዴት፣ ሃዘን:: በስተመጨረሻ ግን በልቤ የቀረው ቅልል ያለ ስሜት እና ደስታ ነው:: ምንም እንኳን ፍቅራችሁን እንድትደብቁ ባደረገው ማህበረሰብ ብናደድና ብበሳጭም ይቻላልን አሰብኩ::ምናልባት አንዱ የፍቅር አገላለፅ ለማሳደግ ችሎታውና የውስጥ ፍላጎቱ መኖር ነው:: የእሳት ነበልባል በእሳት ማጥፊያ ስጋት ቢኖርበትም በዙሪያው እንክብካቤ ካለ ቦግ ብሎ ብርሃንን ይሰጣል:: ፍቅራችሁ የተስፋ አለመቁረጥ ዋጋ ምስክርነት ነው፥ ችግሮችን ትቋቋማላችሁ፤ ስጋቶቹ እና እርግጠኛ ያልሆነው ነጋችሁ ከፊታችሁ ቢሆንም ደስተኝነታችሁ ላይ በማተኮራችሁ ሌላውን ሁሉ ይሽረዋል::

አዲስ አበባ ላይ የምትኖሩ ሌዝቢያን ፍቅረኛሞች እንደመሆናችሁ ብዙ ስጋቶች አሉባችሁ፤ ነገር ግን የፍቅር  ግንኙነታችሁን መቀጠላችሁ አብዮታዊ ነው! ልዩ ጭምርም::

እውነትም እንዴት ሰው እንዲህ አይነቱን አብዮታዊ ፍቅር ይቃረናል?

ከፍቅር ጋር

የኢትዮኩዊር ፖድካስት አቅራቢያችሁ

Leave a Reply