“ሴት ነኝ:: ክርስቲያን ነኝ:: ሌዝቢያን ነኝ::”

ሁሉም ነገር የጀመረው 18 አመቴ እያለ ክፍል ውስጥ አብራኝ የምትቀመጥ ልጅን እየወደድኳት ስመጣ ነው:: ምን ማለት እንደሆነ በወቅቱ ባይገባኝም ሴቶች እንደምወድ ግን አውቅ ነበር:: ደፋሯ እኔ እንዴት እንደተሰማኝ ነገርኳት እሷ ግን ምላሿ ዝምታ ነበር:: ምንም አልመሰላትም ነበር እኔ ግን ከነገርኳት በኋላ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማኝ:: ይሄንን ስሜት ማረም የምችለው የወንድ ጓደኛ በመያዝ ነው ብዬ ወንድ ጓደኛ ያዝኩኝ:: ወንዶች አልገቡኝም:: ቆንጆ ወንዶች፣ የተማሩ ወንዶች፣ ጎበዝ ወንዶች ጋር ግንኙነት ለመጀመር ሞከርኩኝ፤ ምንም አይነት ስሜት ሊሰጠኝ አልቻለም::

ከጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሴት ጋር ተሳሳምኩኝና “ለምንድነው ይሄ ትክክል እንደሆነ የሚሰማኝ?” ብዬ አሰብኩኝ:: ትከሻዋ ውስጥ ሆኜ የሚሰማኝ ደስታ ለምን ወንዶች ጋር ስሆን እንደማይሰማኝ ይገርመኝ ነበር:: ሃፍረት፣ የጥፋተኝነት ስሜትና መመለስ ያልቻልኳቸው ብዙ ጥያቄዎችም ነበሩኝ:: ያኔ ብዙም ኢንተርኔት ስላልነበረ እንዲሁም ፊልሞች የኩዊር ገፀ ባህርይን የያዙ ስላልነበሩ ይሄንን ስሜት ከየት አመጣሁት? እንደኔ ለሴት ስሜት ያላቸው ሰዎች እንዳሉ እንዴት ማወቅ እችላለሁ? ብቸኝነት ተሰማኝ፤ ይሄንን ስሜት እና ሃሳብ “ለመተው” እና “ኖርማል” ለመሆን ሞከርኩኝ:: 

አሁን እግዚአብሔር እንደሚወደኝ አውቃለሁ! ይሄንን ህይወት አልመረጥኩትም፤ ተመርጬ ነው::

ከሴት ጋር ግንኙነት ብጀምርም ራሴን ግን አልተቀበልኩም:: ራስን ሳይቀበሉ ግንኙነት መጀመር ከባድ ነበር:: ቤተክርስቲያን መሄድ ጀመርኩ ነገር ግን በሄድኩ ቁጥር ሁሌ ተመሳሳይ ፃታ በማፍቀሬ ሃጢያተኛ እንደሆንኩ ይሰብካሉ፣ወሲባዊነት እና መንፈሳዊነት ውሃ እና ዘይት እንደሆነ እንደማይቀላቀሉና የሀሰት ህይወት እየኖርኩ እንዳለሁ በአንድም በሌላም ያስተምራሉ:: የምቆምበት አጣሁ:: እዚህ ጋር ከሴት ፍቅር ይዞኛል ፤ ሴት ካፈቀርኩ ይጠላኛል ብዬ ያሰብኩትን እግዚአብሔርንም እወደዋለሁ::

ሃጢያተኝነት ተሰማኝ:: ሌዝቢያንነቴን በፀሎት ላባርረው ሞከርኩኝ:: “እግዚአብሔር ለምን እንደጓደኞቼ የተቃራኒ ፃታ አፍቃሪና “ኖርማል” አላደረገኝም?”  እያልኩ በጣም አለቅስ ነበር:: ነገሮች ሁሉ በሁለቱ አለም ውስጥ ሲወሳሰቡብኝ ነበር እንዲህ ከመኖር ራሴን ባጠፋስ ብዬ ያሰብኩት:: ራሴን ለማጥፋት ወስኜ ነበር፤ እግዚአብሔር ይመስገን ያ ሁሉ ቢሆን ኖሮ አሁን ያለኝን ደስ የሚል ኑሮ አልኖረውም ነበር:: 

ሰዎች ከውስጣቸው ጋር ሰላም ከሌላቸው ከሌሎችም ጋር ሰላም አይኖራቸውም ብዬ አምናለሁ:: ከብዙ ጊዜ በኋላ ራሱ ከራሴ ጋር እታገል ነበር:: ከዛ ግን ኢንተርኔት በደንብ መጣ፣ ኦንላየን ዴቲንግ፣ ሰዎችን መተዋወቅ፣ ሰዎችን ብተዋወቅና ስለራሴ ብዙ ማወቅ ብጀምርም ሃጢያተኛ ነሽ ተብዬ ስለተማርኩ እግዚአብሔር እንዲቀይረኝ እፀልይ ነበር:: የተነገረኝ እንደዚህ የሆኑትን ሰዎች መጥላት እንጂ ሆኖ መገኘት አይደለም::

አሁን እድሜዬ 27 አልፉል ይሄ እድሜ ሁሉም ሰው ወይ እንዳገባሁኝ ወይም ለማግባት እቅድ ላይ እንደሆንኩኝ የሚገምትበት ጊዜ ነው:: ቤተሰቦች፣ ጓደኞቻችሁ እና ጎረቤቶቻችሁ “መቼ ልታገቢ ነው?” ፣ “ልጁ ማነው?” ፣ “ጓደኛ ለምን አትይዥም?” “እድሜሽ ቆሞ አይጠብቅሽም ፈጠን ብትይ ይሻላል?” እና የመሳሰሉትን አግባብ ያልሆኑ ጥያቄዎች ይጠይቃሉ:: ሰዎች ስለራሳቸው ብቻ ቢያገባቸው እና ቢተውን ምኞቴ ነው! ለረዥም ጊዜ ግራ ገብቶኝ ነበር ምክንያቱም ኑሮዬ ከውጪ ወደውስጥ ነበር፤ ራሴንና እግዚአብሔርን እንደመስማት ሰዎች የሚሉኝን እሰማ ነበር:: ጓደኞቻችሁ ሁሌ ስለወንድ ጓደኞቻቸው ሲያወሩ እኛ (ሌዝቢያን ሴቶች) እዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ስለማይወራ ሁሌም ጓደኛ የሌለን ተደርገን እንወሰዳለን::

ከአምና ጀምሮ የሴት ፍቅረኛ አለችኝ:: ከአንድ ሴት ጋር ተወስኖ መኖር እንደሚቻል ሰዎች እንዲያውቁ እፈልጋለሁ:: ሌዝቢያን ወይም ጌይ መሆን ማለት ወሲብ ወይም ሥጋዊ መሻት አይደለም:: ከዚህ በላይ ነው፤ ፍቅር ማለት ነው::

ከአምና ጀምሮ የሴት ፍቅረኛ አለችኝ:: … ሌዝቢያን ወይም ጌይ መሆን ማለት ወሲብ ወይም ሥጋዊ መሻት አይደለም:: ከዚህ በላይ ነው፤ ፍቅር ማለት ነው::

አሁን እግዚአብሔር እንደሚወደኝ አውቃለሁ! ይሄንን ህይወት አልመረጥኩትም፤ ተመርጬ ነው:: ክርስቶስ ሴቶች እንደሚማርኩኝ ያውቃል:: የማመልከው አምላክ ሁሉንም አይነት ሰዎች ይወዳል፣ ውሸት እና ሃሰተኛ ህይወት እንድኖር አይፈልግም፤ እሱ እንደፈጠረኝ ራሴን ተቀብዬ እንድኖር እንጂ ፣ ይህንንም ስጦታ ሌሎች ራሳቸውን እንዲቀበሉ እንድረዳ እና እንዳበረታታ ሰጥቶኛል::

ሴት ነኝ:: ክርስቲያን ነኝ:: ሌዝቢያን ነኝ:: ማንም ሌላ ሊነግረኝ አይችልም ምክንያቱም ይሄ ማንነቴ ነው:: እኔ ነኝ:: በዚህ ልሰናበታችሁ፦ 

በእኛ እና በእግዚአብሔር ማንም አያገባውም:: ማንም:: 

ወደ ሮሜ ሰዎች 8፥ 38- 39

“ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ::”

Leave a Reply