በማህበረሰባችን ውስጥ ስለተሻለ ተራማጅ እንክብካቤ ጉዳይ

ወጣት ኩዊር ኢትዮጵያዊ ሴት ነኝ፤ እንደ እድል ሆኖ ፃታዊ ተማርኮዬን የተቀበልኩት ከኢትዮጵያ ውጪ ሆኜ ነው:: ከቆይታ በኋላ ስመለስና በተለምዶ “ወንዳወንድ” ከሆነች ኩዊር ሴት ጋር ፍቅር ሲይዘኝ ነበር ኢትዮጵያ ውስጥ የኩዊር ግንኙነት ምን እንደሚመስል የተጋፈጥኩት:: 

ሴትን ማፍቀር ትክክል አይደለም በተባለበት ቦታ ላይ ማፍቀር የተራማጅነት እና ጀግንነት አንዳንዴም የንዴት እና የብስጭት ስሜት ነበረው:: የኩዊር ፓንሴክሽዋል ማንነት እንዳለው ሰው፤ ለሁሉም ፃታ ተማርኮ እንዳለው ሰው ኩዊርነት ሁልጊዜ ሰፊና ነፃነት የሚሰጥ ስሜት አለው:: የፍቅር አጋሬ ስለፃታዊ ዝንባሌ እና ፃታዊ ተማርኮ ያላት አመለካከት የተቃራኒ ፃታ አፍቃሪነትን እንደመጀመሪያ እና ነባር አድርገው የሚያስቡ ጊዜው ያለፈባቸው ትርክቶች (hetronormative) አይነት መሆኑ በጣም አስደንጋጭ ነበር::

ሴትን ማፍቀር ትክክል አይደለም በተባለበት ቦታ ላይ ማፍቀር የተራማጅነት እና ጀግንነት አንዳንዴም የንዴት እና የብስጭት ስሜት ነበረው::

በተለያየ መንገድ ፆታዊ ዝንባሌዬ ቁጥጥር በዛበት:: በተለምዶ “የሴት” የሚባለውን አለባበስ ስለብስ የምበረታታበትና በተለምዶ “የወንድ” የሚባለውን አለባበስ ግን ስለብስ ብዙም ተፈላጊ እንዳልሆንኩ ይሰማኝ ነበር::   ኩዊር ግንኙነቶች እንኳን አንደኛዋ የ”ሴት” ገፅታን (femme) የያዘችና ሌላኛዋ የ”ወንድ” ባህሪይን (butch) መሆን አለባት አይነት በሁለትዮሽ ፆታ የተቃኘ አለም ውስጥ ነበር የምትኖረው:: በስርዓተ ፆታ ዙሪያ ላነሳቸው የሞከርኳቸው ወሳኝ ውይይቶች ሩቅ አልሄዱም::

በብዙ ምክንያት የፍቅር ግንኙነቱ ተቋርጧል፤ ለእኔ ከነበረን ግንኙነት በላይም ትልቅ ውይይት የሚሻ ነገር ጥሎብኛል:: ሆነም ቀረ ሲስተሞች ራሳችንንና የእርስበእርስ አተያያችንን ይቀርፃሉ፤ ያንን ደግሞ መፈተሽ ያስፈልጋል:: ኦድሬ ሎርድ “የባለቤቱ መሳሪያ የባለቤቱን ቤት አያፈርሰውም”ትላለች::  ራሳችን እንደጨቋኝ እየተመላለስን የኩዊርና የትራንስ ሰዎችን ነፃነትን መሳካት መጠበቅ አንችልም:: ይልቁንስ በእኛ መሃል ቁጥጥር ስናበዛ የበላይነትን እናበረታታለን::

ከጥቂጥ አመታት ወዲህ ያለው የኩዊር እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ለሚኖሩ LGBTQIA+ ሰዎች ጥቃትን አባብሷል:: ይህ ጥቃት የተባዕታዊ ስርዓት (patriarchal) እና ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ ጠልነት ነው፤ ያው ሁለተኛው ያለመጀመሪያው አይኖርም:: ወንዶች እና የበላይነት “መብታቸው” በማህበረሰባችን ውስጥ በሁሉም ቦታ ተንሰራፍቶ ይገኛል ስለዚህ ብቸኛው አማራጭ የሚመስለኝ እርስ በእርሳችን መተሳሰብ ነው:: የተባዕታዊ ስርዓት እንዴት በግንኙነቶቻችን ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ መፈተሽ አለብን:: አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ግንኙነት ያለንን ሰዎች፥ የፍቅር ግንኙነት ወይም ሌላ፤ ላለመጉዳት ራሳችንን እንድንገመግም እንዴት መተጋገዝ አለብን?

የተባዕታዊ ስርዓት እንዴት በግንኙነቶቻችን ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ መፈተሽ አለብን::

ኩዊር ኢትዮጵያውያን መቼ እና እንዴት አርነት ወጥተን፣ ማንነታችን ተቀባይነት አግኝቶ ሃገራችን ላይ እንደምንኖር አላውቅም:: ነገር ግን ለእርስ በእርሳችን እና ለማህበረሰባችን አርነትን እና እንክብካቤን ለማምጣት ብዙ ማድረግ እንችላለን:::: ከአርነት መውጣት ይቻላል የሚለውን ምኞት ልንኖረው ይገባል፤ ሁላችንም ልንሰራበት የሚገባም እሴት ነው:: ኩዊር ቦታዎች የበለጠ ተራማጅ እንዲሆኑ፣ ፍቅር የበዛባቸው፣ ሁሉን አካታች እና የበለጠ ደህንነት የሚጠብቁ እንዲሆኑ መስራት እንደሚቻል አምናለሁ:: የተሻለ ይገባናል፤ በይበልጥ ደግሞ ከእርስ በእርሳችን::

Leave a Reply