ጥላቻ የሚሰብክስ?

ማህበራዊ ሚዲያ ምንም እንኳን ብዙ ጥቅሞች ቢኖሩትም በጥላቻ የተሞሉ ሰዎችን ማየት ደግሞ ሌላው ጎን ነው:: “ጌ እገላለሁ” ከሚለው አንስቶ “የቤተሰቤ አባል ጌ ቢሆን አባርረዋለው” ድረስ የተለያዩ ጥላቻዎችን አይቻለሁ፤ በሚያሳዝን ሁኔታ ስለእኔ ማንነት የቅርብ የምላቸው ጓደኞቼም ይሄንን አይነት መልዕክት ላይክ ሲያደርጉ አይቻለሁ:: አስቡት በጣም የምትቀርቧቸው ጓደኛችሁ እንዲህ አይነቱን ጥላቻ ሲያበረታቱ! ድሮ ድሮ በፍራቻ ዝም እል ነበር:: አሁን እንኳን ጥላቻን የሚሰብክ የቅርብ ጓደኛ የለኝም ስል በኩራት ነው::

“ጌ ማንነት ነው ልክ እንደ ሃይማኖት፣ ስርዓተ ፃታ እና ብሄር…ጌ የአንድ ሰው ማንነት ነው…አሰብኩት ይሄ መልዕክት “እዚህ ጋር የሚሸና [ብሄር/ሃይማኖት]  ነው” ቢል ኖሮ…”

ዛሬ ላይ ስለጥላቻ እንዳነሳ ያደረገኝ ግንብ ላይ የተፃፈው  “ሽንት የሚሸና ጌይ ነው” የሚለው መልዕክት ነው:: ፌስቡክ ላይ ሳየው የተደበላለቀ ስሜት ነበር የተሰማኝ፣ የሰው ልጅ እንዴት ለጥላቻ እንዲህ ይጨናነቃል? እንዴትስ ሃሳቡ ይመጣለታል? በውስጤ ብዙ ጥያቄዎችን ጠየኩኝ፣ በሰፈሩ ሽንት እየተሸና ቢያስቸግር ሌላ መፍትሄ ጠፍቶ ነው?  “5 ብር ያስከፍላል” የሚለው ማስታወቂያ አልበቃ ብሎ ነው? አይደለም! በፖለቲካው ሲጣላ የዋለው ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኩዊር ሰዎችን ለማውገዝ ይተዛዘላል:: አግባብ የሌለው ስድብ ሲሰዳደቡ የነበሩ ሁለት ሰዎች የኩዊር ጉዳይ ላይ ሲሞጋገሱ ይታያል:: የሰው ልጅን እንዴት ጥላቻ ያፋቅረዋል? ሁለቱስ አይቃረኑም? 

“መንገድ ላይ የሚሸና ውሻ ነው” የሚሉ የተለመዱ መልዕክቶች በየሰፈሩ ይታያሉ:: ይሄ መልዕክት ውሻ ካልሆናችሁ በስተቀር እዚህ ጋር አትሸኑም/ከሸናችሁ ውሻ ናችሁ ተብሎ እንደስድብ የተቀመጠ ማስጠንቀቂያ ነው::እንደዚሁ ይሄ መልዕክት ባለው የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ ጠልነት ላይ በደንብ እንጥላቸው የሚል የትውስታም የማበረታቻም መልዕክት ይዧል:: ፌስቡክ ላይ ይሄ መልዕክት የተለያዩ ሙገሳዎችን አግኝቷል:: ብዙዎች ሳቅ በሳቅ ሆነዋል:: ለእኔ የማያስቀው የሰው ልጅ ህይወትን አደጋ ላይ ስለሚጥል ነው:: ቆሻሻን ለማስቆም የተጠቀሙበት መንገድ ድጋሚ እዛ አካባቢ ሰዎች ባይፀዱም ግርግዳው ኩዊር ሰዎችን ለጥቃት የሚያጋልጥ ቆሻሻን ይዟል::

እንግዲህ ፀሃፊው(ዋ) እንዲህ ሃፍረት ሳይሰማው(ት) “ጌ” ስለምትጠሉ እንዲህ ብለናችሁ ከተማችንን ውብ እናደርጋታለን ብለዋል:: ሃሳብ ለሃሳብ ባንስማማ እንኳን የሌላውን ጓዳ ሳናይ እና ስለሌላው ሳያገባን መኖር የምንችልበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? መንግስትም ሆነ የቀበሌ አስተዳደር ወይም የሰፈሩ ኗሪዎች እንዲህ አይነቱን ጥላቻ “አይ ይሄ መልዕክት አግባብ አይደለም” ብለው ያስጠፉታል ብዬ አላስብም:: አብዛኛው ህዝብ ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ ጠል ስለሆነ የብዙሃን ድምፅ ይመረጣል::

ጌ ማንነት ነው ልክ እንደ ሃይማኖት፣ ስርዓተ ፃታ እና ብሄር…ጌ የአንድ ሰው ማንነት ነው…አሰብኩት ይሄ መልዕክት “እዚህ ጋር የሚሸና [ብሄር/ሃይማኖት]  ነው” ቢል ኖሮ…

Leave a Reply