ሌዝቢያን እንደሆንኩ ያወኩት ገና በልጅነቴ ነው:: ቋንቋውና ምን እንደሆነ ባይገባኝም፤ ስሜቱን ግን አውቄዋለሁ:: በአካባቢዬ ሴቶች ተፋቅረው በነፃነት ሲኖሩ ስላላየሁ ስሜቴ የኔ ብቻ እና ነውር እንደሆነ ነበር የተሰማኝ:: ለሰው የማይነገር ሚስጥር፣ ሃጢያት እና ነውር::
ጓደኞቼ በግልፅ ስለፍቅረኞቻቸው እና ስላፈቀሯቸው ወንዶች ሲያወሩ እኔ ጋር ያለው ስሜት ሌላ ስለነበር እነሱን ለመምሰል ብዙ የፈጠራ ወሬ ማውራት ነበረብኝ:: የሌለን ስሜት አለ እያልኩ ደንበኛ የወንድ አፍቃሪ ሆኜ መታየት:: ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ እንደሚባለው ከተቃራኒ ፃታ አፍቃሪ ሰዎች በላይ እኔ ስለወንድ የወሲብ ግንኙነት ይበልጥ አወራለሁ፤ ወንድ እንደምወድ እና ጥልቅ እውቀት እንዳለኝ እንዲያስቡ ሁሉን አደርጋለሁ::

አልኮል መጠጣት እና ሲጃራ ማጨስ የጀመርኩበትን ቀን ባላስታውሰውም ከ18 አመት በታች ግን ነበርኩ:: አልኮልን ለማንም የማላዋየውን ማንነቴን እንደመደበቂያነት አየሁት:: የቀን ውሎዬ ላይ የምጋፈጠውን ማንነቴን ማስረሻዬ ሆነልኝ:: ስለማንነቴ ስጨነቅ እውልና ምንም እንዳልተፈጠረ ስለዚህ ማንነቴን ከማያውቁት ጓደኞቼ ጋር ስጨፍር ይመሻል፤ የውስጥ ህመሜ ለጊዜው ይረሳል:: እንቆቅልሽ የሆነብኝን ማንነቴን በሲጃራ ሳቃጥለው ቀኑ ያልፍና በቢራ እና ደረቅ አልኮል ደግሞ አመሽበታለሁ:: ከመደበቂያነት ባሻገር ግን አልኮል ድፍረትንም ይሰጠኛል ብዬ ስለማስብ አብሬያት አድራለሁ ብዬ ካሰብኳት ሴት ጋር ለማደር የግድ መጠጣት እፈልግ ነበር:: ተማርኮዬ ተፈጥሮዓዊ ነው ብዬ ስለማላስብ እና ነውር ስለሚመስለኝ ስካሩ ያንን ሁሉ ይሽረዋል:: ነገሩ ለጊዜው ነው! ምክንያቱ ጠዋት ስነቃ ያለው “አንቺ ነውረኛ!” የሚለኝን ስሜት አያጠፋልኝም:: የወደድኳትን ሴት በግልፅ ለማዋራት የስካር ስሜት ውስጥ መሆን ሌላው እንደደህንነትም ነው:: እንደምወዳት እነግራታለሁ እሷም ወይ “ሰክራ ነው” ትለኛለች ወይ ትቀበለኛለች የሚለው እሳቤ ነበረኝ:: ይሄ በአንድ ወቅት ኮሌጅ እያለሁ በጣም የወደድኳትን ሴት “ልሳምሽ?” ብዬ ለመጠየቅ የፈጀውን የቢራ ጠርሙሶች እና የደረቅ አልኮል ብርጭቆዎች ያስታውሰኛል:: በልጅነት የነበሩኝ የወሲብ ልምዶች በአልኮል የታገዙ የሆኑትም ለዛ ነው:: ባልሰከረ መንፈስ ለወሲብ መዘጋጀት አልችልም ምክንያቱም ለሴት ያለኝ ተማርኮ ትክክለኛ ነው ብዬ ስለማላምን በአልኮል መደበቁ በሰዓቱ በግዴለሽነት ያሳልፈኛል ብዬ አስባለሁ::
ኮሌጅ እያለሁ ለአንድ አመት ያህል በሳምንት ቢበዛ አምስት ቀን ቢያንስ ደግሞ ሶስት ቀን ውጪ ነው ያሳለፍኩት:: ይሄ አመት ምናልባት እስከዛሬ ከኖርኳቸው ሁሉ ከባዱ አመቴ ነው ብዬ አስባለሁ:: ይበልጥ ለሴት ያለኝን ስሜት የተረዳሁበት አመት ቢሆንም ራሴን ላለመቀበል ደግሞ የተቸገርኩበትና የተንገላታሁበት አመት ነው:: በየቀኑ እስኪመሽና እስክሰክር እመኝ ነበር:: ማን ከራስ ጋር ይወያያል:: የሃጢያተኛነት፣ ነውረኝነት፣ ጥፋተኝነት እና ሌሎችንም ስሜቶች ማን ያዳምጣል፤ መስከር እየተቻለ!
የሚገርመው ተማርኮዬን በውሎዬ ባየውም ራሴን “መጠጡ ነው የገፋፋኝ”ብዬ አታልለው ነበር:: ደግሜ ደጋግሜ ሴት የሚባል ሁለተኛ እላለሁ፤ ራሴን ግን በሴት እንዳትማረክ ማድረግ አልቻልኩም:: ዛሬ ላይ ቆሜ ሳስበው ምናልባት አጠገቤ አይዞሽ የሚለኝ ባገኝ፣ ራሳቸውን ተቀብለው መኖር የቻሉ ሰዎችን ባውቅ ኖሮ የወሰድኳቸውን መንገዶች አልወስድም ነበር ብዬ አስባለሁ፤ ራሴንም ባልጠላሁት ነበር:: በወቅቱ በፍቅር ግንኙነትም ይሁን በወሲብ ግንኙነት ውስጥ የነበርኩባቸው ሴቶች ሁሉ ተመሳሳይ አስተሳሰብ የነበራቸው ናቸው:: ጊዜ ሰጥቶ ከማውራት ይልቅ በስካር ሆኖ ወሲብን እንዲሁም ሲነጋ ምንም እንዳልተፈጠረ ሳይወያዩበት መለያየትን የሚመርጡ ነበሩ፤ እኔም እንደዚያው:: ምንስ ይወራል? ምኑን አውቄው? ምንስ ማለት እችላለሁ? በተደጋጋሚ የምለው ነገር “ትክክል አልሰራንም መቆም አለበት” ነው:: ሲከፋ ደግሞ ወይ በእኔ በኩል ወይም በእሷ በኩል የስልክም ሆነ የአካል ግንኙነት ማቆም ነው…ስልክ አለማንሳት እና በዛው መጥፋት::
ጊዜ ሰጥቶ ከማውራት ይልቅ በስካር ሆኖ ወሲብን እንዲሁም ሲነጋ ምንም እንዳልተፈጠረ ሳይወያዩበት መለያየትን የሚመርጡ ነበሩ፤ እኔም እንደዚያው:: ምንስ ይወራል? ምኑን አውቄው? ምንስ ማለት እችላለሁ?
እነዚህን ጊዜያቶች ሳስብ ትንሿ እኔ ታሳዝነኛለች:: ማንም ያልነበራት ባለብዙ ጓደኛዋ ነገር ግን ብቸኛዋ ትንሿ እኔ ታሳዝነኛለች:: ለማንም መንገር ያልቻለችው፣ አልኮል ለመዝናኛነት ሳይሆን ለመደበቂያነት የያዘችው ትንሿ እኔ! ከኮሌጅ እስክትወጣ ድረስ ጤናማ የፍቅር ግንኙነት ያልነበራት ትንሿ እኔ!
የሆነው ሁሉ ሆኖ ዛሬ ላይ ከራሴ ጋር ታርቄ የምወደውን ቢራ እና ደረቅ አልኮል በአግባቡ ለመዝናኛነት እጠቀማለሁ:: አልኮል መጠጣትን እንደጀመርኩት መቼ ከመደበቂያነት ወደመዝናኛነት እንደቀየርኩት አላስታውስም:: ራሴን በጣም እንደጎዳሁት መረዳቴ (ምግብ በአግባቡ ባለመመገብ፣ ራስን ባለመጠበቅ…) እና ከራሴ ጋር ጊዜ ሰጥቼ ለመወያየት ስወስን እንደሆነ ግን አውቃለሁ:: ትልቁ ነገር ደግሞ “ለማናባቱ ብዬ ነው ራሴን የምጎዳው?” የሚለው ፉከራዬ ነው:: ከጊዜ በኋላ ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪነት ሃጢያትም ነውርም እንዳልሆነ እና የማንነቴ አንድ ክፍል እንደሆነ ማወቄ ይሄንን እንድጠይቅ አድርጎኛል:: ለዛሬዋ እኔ የተለያዩ ፅሁፎች ረድተውኛል ከሴት ጋር ወሲብ ለማድረግ ዋነኛው ነገር እንደትንሿ እኔ መስከር ሳይሆን ፈቃደኝነትና ጥንቃቄ እንደሆነ እና የመሳሰሉትን::
አልኮል እና ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪነቴ ያስተሳሰረው አልኮል የኩዊር ባህሪይ መገለጫ ሳይሆን አካባቢዬ ያመጣው ተፅዕኖ እንደሆነ አውቃለሁ:: ከራስ ጋር ላለመነጋገር፣ ተስፋ በመቁረጥ እንዲሁም ከላይ የጠቀስኩትን ድፍረት ለማግኘት:: በማይቀበል፣ ለአለም ችግር ሁሉ የኩዊር ሰዎች መፈጠር(መብዛት) ነው ብሎ በሚያስብ ማህበረሰብ ውስጥ ስኖር ስካር በውሎዬ ላይ ያየሁትን ጥላቻና ብቸኝነት አስታጋሽ ነው ብዬ እንዳምን አድርጎኛል:: ጤናማ ያልሆኑ የፍቅር ግንኙነቶችን በማቋረጥና ራሴ ላይ ጊዜ ወስጄ የተሻለ በማድረግ መንገዴን እና ውሳኔዬን ማስተካከል ችያለሁ ብዬ አስባለሁ::
ለማንኛውም የጊዮርጊስ ቢራ እና ጂን በቶኒክ አድናቂ ነኝ:: ዛሬ ላይ ስጠጣ ትንሿን እኔን “በዛ ሁሉ ውስጥ አልፈሽ ዛሬ ላይ ደርሰሻል:: ምንም የሚፀፅት ነገር የለም:: በስተመጨረሻ አሸንፈሻል፤ ታሸንፊያለሽም” እያልኩ ቺርስ እላታለሁ::