የመፅሄት መክፈቻ: እምነት እና ወሲባዊነት እትም

እምነት እና ፃተዊ ተማርኮ ኩዊር ለሆንን ብዙዎቻችን በደንብ የተሳሰሩ ነገሮች ናቸው:: አብዛኛውን ጊዜ እምነት ኩዊር ለሆንን ራሳችንን መቀበል እንዳንችል ትልቅ እንቅፋት ይሆናል:: ለዚህም ነው በኩዊር ጉዳዮች ዙሪያ የሚያተኩረውና በየሶስት ወሩ የሚታተመው የመጀመሪያውን የንስንስ መፅሄታችንን በዚህ ጉዳይ ላይ  ያደረግነው::

ኩዊርና ሃይማኖተኛ ወይም መንፈሳዊ መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ኩዊርና በእምነት ውስጥ ላለን ሁለቱ ማንነቶች አብረው እንዴት መሄድ ይችላሉ? እነዚህን ሁለቱን ማንነቶች እንዴት ማስታረቅ እንችላለን? እውነት ሃይማኖት ራስን ለመቀበል ትልቁ እንቅፋት ነው?  

ከእትማችን ውስጥ የተወሰዱ: 

“ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ አለም ፍፃሜ ይነሳል…ግን ተከታታይ የሆነ የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ ጠልነት አይደለም:: ይሄ ተፅእኖ የለውም ማለቴ አይደለም::…በልጅነት፣ ራሴን ሳልቀበል በነበረው ጊዜ ከባድ ነበር:: ያሸማቅቅሻል፣ ቸርች ባልሄድ ያልኩባቸውም ጊዜያት አሉ:: በዚህ ምክንያት የፍቅር አጋሬ ቸርች አትፈልግም ነበር:: ጥላቻው ሁልጊዜ አይደለም በሚል ውይይት አሁን ትሄዳለች:: ሁልጊዜ ቢወራ እኔም የሚመቸኝ አይመስለኝም:: ኢትዮጵያ ውስጥ እንደትልቅ ችግር ስለማይታሰብ የሚነሳውም አልፎ አልፎ ነው፤ የለም ተብሎ ስለሚታሰብም ለዛም ይሆናል:: በደንብ እየታየ ሲመጣ ቸርቾች የመጀመሪያ ስራቸው ነው ብዬ አስባለሁ::”  – ሰላማዊት 

“ቁራን ስለLGBTQ+ ምን እንደሚል በደንብ አላውቅም ስለዚህ ቁርጥ ሃሳብ ለመያዝ ይከብደኛል:: ነገር ግን ከሚነገረን በመነሳት ኩዊር ማንነትን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ለመቀበል ያን ያህል ቦታ የለውም::”  – ነጃት 

“ለመጀመሪያ ጊዜ ከጥሩ ጓደኛዬ ጋር ስለሃይማኖት ግልፅ የሆነ ውይይት ሳደርግ ከቤተሰቤም ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ሩቅ ቦታ ነበርኩ:: ከሁለት ሰዓት ውይይት በኋላ ለትዕዛዛት የሚጨነቅ አምላክ እኔ ከማምነው የፍቅር ትርጓሜ ጋር አብሮ እንደማይሄድ ለራሴ አመንኩ:: በእሱ ባለማመኔ ደህንነት ተሰማኝ:: አለምን የተረዳሁበትን መንገድ ሙሉ በሙሉ መቀየር በጣም አድካሚ ሂደት ነበር ነገር ግን አቅመቢስነትን የሚያሰማኝ ሃይማኖት ቦታ የመመለስ ፍላጎት የለኝም::” – ሄለን 

“ክርስቶስ ለፍቅራችን ሲል ሞተ ከሚለው ፓስተር “የአምላክን መንገድ የማይከተሉ ይጠፋሉ” የሚለው ፓስተር ጆሮዬ ላይ ይበልት ይጮኽ ነበር”:: በቸርች ውስጥ እኔ ብቻ ሌዝቢያን የሆንኩ እና የሃጢያት ሁሉ ትልቅ ሃጢያት ውስጥ እንደተወዘፍኩ ነበር የሚሰማኝ::…” – ቃልኪዳን

“ከሃጢያት ጋር ያለኝ ግንኙነት ይልቅ የለም የምለው ነው:: ኢአማኝ የሆንኩት ከ16 አመቴ ጀምሮ ነው:: እንዲያውም ከመቼውም ጊዜ በላይ ስለ እምነት፣ ሃይማኖትና እግዚአብሔር ያሰብኩት እሷን ካወኳት ጀምሮ ነው፤ የጥፋተኝነት ስሜቷን፣ እምነቷን እና የእሷን እግዚአብሔር ሊገባኝም ልረዳውም አልቻልኩም::” – ስም ያልተጠቀሰ

እምነትና ወሲባዊነት መመርመር እንደኢትዮጵያውያን ያገናኘናል እንዲሁም ይጠቅመናል ብለን እናምናለን:: የመጀመሪያው ንስንስ እትም በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚለቀቅ ስንነግራችሁ በታላቅ ደስታ ነው:: እንደምታነቡትና ሃሳባችሁን እንደምታጋሩን ተስፋ እናደርጋለን::

Leave a Reply