በወጣትነት ጊዜዬ በአማርኛ የተፃፈ ኩዊር ነክ ነገር ማግኘት ይቅርና ምን ተብሎ እንደሚፈለግም አላውቅም ነበር:: ጉግል ሳደርግ ያገኘኋቸው ነገሮች ሁሉ ከውጪው አለም ጋር የተገናኙ ስለሚሆኑ ለኔ ባደኩበት መስመር የሚሄድ ፅሁፍን ለብዙ ጊዜ ማግኘት ተቸግሬ ነበር::

ንስንስ ምን ያህል እንዳስደሰተችኝ ለመግለፅ ይከብደኛል:: በአክራሪ ቤተሰብ እና ኃይማኖት አድገን ለመጣን ደግሞ እጅግ በጣም ትልቅ ነገር ነው:: ሃገራችን ላይ በእምነትና ወሲባዊነት ዙሪያ ያለውን እውነታ ቁልጭ አድርጋ አሳይታናለች:: ሃይማኖት አስተማሪዎች እንዴት ማህበረሰቡን አንደቀረፁትና እየቀረፁት እንዳሉ አሳይታለች:: ይህም ደግሞ በግል ህይወታችን ብቻ ሳይሆን ፣ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት፣ ከቤተሰብ እንዲሁም ከፍቅር አጋራችን ጋር ጭምር ትልቅ ችግር ሊፈጥርብን እንደሚችል ተርካለች:: የሁሉም ኩዊር ሴቶች ታሪክ በተለያየ ኃይማኖት ውስጥ ያደጉና ያሉ ቢሆንም ምን ያህል ተመሳሳይነት እንዳለው ያስረዳል:: በቤተ እምነቶች ላይ ያለው ኩዊርነትን የመግፋት ጠንካራ አቋም ብዙዎችን ከቤተ እምነት እንደገደባቸው ያሳየናል:: እንደዛውም ደግሞ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ቢሆንም እንደሰላማዊት ያሉ ደግሞ በቤተ እምነት አሁንም ተካፋይና አባል ሆነዋል::
ይቺ መጽሔት ኃይማኖት ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚልን ጉንጭ አልፋ ክርክር ሳይሆን የተለያዩ ኩዊር ሴቶችን ነባራዊ ሁኔታ ይዛ መቅረቧ ለብዙዎች ተስፋን እንደምትሰጥ አልጠራጠርም:: “ኩዊርነቴ ትክክል ነው ወይስ አይደለም?” የሚለውን የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ኩዊርን ጥያቄ እነዚህ ከህይወት ተሞክሯቸው የተካተቱት ታሪኮች ምንም ቢሆን ጠቃሚ ናቸው እላለሁ:: ምላሽ ባይሆኑም የሰውን ተሞክሮ እና ጉዞ በማንበብ የራስን አቋም ማበርታት ይቻላል:: ዛሬም ድረስ ብዙዎች ይበልጥም በኃይማኖት ተፅዕኖ ውስጥ ያደጉ ኩዊር ሰዎች የራስን መቀበል ጉዞው አዳጋች ይሆናል:: ንስንስ ግን በዚህ ጉዞ በተጓዙ ሰዎች ውስጥ ሆና ብርታትን ጭራለች::
<<ኃጢያት ሲፈተሽ>> ላይ ሰላማዊት “ራሳችንን እንድንጠላ፣ ሰዎችን እንድንጠላ የሚያደርግ እግዚአብሔር አለ ብዬ አላስብም” ያለችው “ተጠልተናል” ብለው ላሰቡ ብዙ ኩዊር ሰዎች ደስ የሚል ስሜትን ይፈጥራል፤ ያበረታልም::<<ነፃ መውጣት>> የሚለው ክፍል ላይ ደግሞ ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሎችም ያለንን ጥላቻ እንድፈትሽ የምታስገነዝብ ናት፤ “ውስጤን ስለተዋሃደኝ ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪና ትራንስ ሰዎችን እንደ’ስጋት የመቁጠር ዝንባሌዬንም እየተውኩ ነው” የምትለው:: አብዛኛውን ጊዜ <<ያለጥርጥር>> ላይ “በተጣመመ አስተምሮ” እንዳለችው፣ በዛ ውስጥ ስናድግ ራሳችንን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም [ትራንስ ሰዎች] እንጠያፋለን እናም የፀሃፊዋ ራሷን መፈተሽ እኔንም ራሴን እንድፈትሽ አድርጋኛለች:: ራስን እንዳንሆን በሚያደርግ ህብረተሰብ ውስጥ መኖር ራስን ለማጥፋት እስከመሞከር እንደሆነ <<ያለ ጥርጥር>> ላይ ያለው ታሪክ ያሳያል:: [አካባቢን ለመምሰል ያልሆነውን ማንነት ለብሰን ለመታየት መሞከር] ልብ ይሰብራል:: ያለፈችውን አልፋ ደግሞ በኩራት “ለኩዊርነት የተመረጥኩ” ስትል ፈገግ አሰኝቶኛል:: ፅሁፎቹ ብዙ የሚያሳዝኑ አጋጣሚዎችና ጉዞዎች ቢኖራቸውም፤ እጅግ በጣም አስደስተውኛል:: ጉዞ አያልቅምና ቀጣዩም ጉዞዋቸው የተሻለ እንዲሆን እመኝላቸዋለሁ:: ንስንስን ልጅ እያለሁ ባገኘው ኖሮ ብዬ እንደተመኘሁት በኃይማኖት ተፅዕኖ ውስጥ ያሉ እና ጥያቄ ያላቸው ኩዊር ሰዎች ሁሉ እንዲያገኟት እመኛለሁ:: ራስን መፈለግ እንደኛው አይነት ህይወት ባሳለፉ ሲሆን መረዳትን ይጨምራል::
ከ <<ፍቅር እና ኃጢያት>> ክፍል ላይ ጎልቶ በታየኝ መስመር ሃሳቤን ልቋጭ፥ [የፍቅር ኃጢያትነት መቼም ቢሆን የስሌታችን አካል ሊሆን አይገባም]