ኩዊርነት እና የአዕምሮ ጤና

ስለአዕምሮ ጤና ምንም ግንዛቤ አልበረኝም:: የአዕምሮ ህመምም ጨርቅን አውልቆ መንገድ ላይ መውጣት እንጂ ብዙ አይነት የአዕምሮ ጤና ችግሮች እንዳሉ አላውቅም ነበር:: ሰው ጨነቀኝ ሲልም የቅንጦት እንጂ ምን ያህል ትክክለኛ የአዕምሮ ህመም እንደሆነ አላውቅም ነበር:: በሃይማኖት ውስጥ ስላደኩም የአዕምሮ ህመም ከሰይጣን ጋር የተገናኘ እና ፀሎት የሚያስፈልገው እንደሆነ ነበር የማምነው:: 

የመጀመሪያው ራስን የመቀበል ትግል የአዕምሮ ጭንቀትን ቁልጭ አድርጎ አሳይቶኛል:: በተቃራኒ ፃታ አፍቃሪ ትክክለኛነት ብቻ በሚያምን ህብረተሰብ ውስጅት ራስን ኩዊር ሆኖ ማግኘት በወጣትነቴ ከገጠሙኝ ፈተናዎች ትልቁን ቦታ ይይዛል:: የሃጢያተኝነት እና ጥፋተኝነት ስሜት ብቸኝነትንና ድባቴን ፈጥሮብኛል:: ከትምህርት ቤት መልስ ቤተሰቦቼን ርቄ በክፍሌ ውስጥ መደበቅ የዘወትር ስራዬ ነበር:: ከ”ቀልብሽ አይደለሽም” ይሉኛል ብዙ ስለማስብ፣ ስለምጨነቅ:: እንዴት ራስን መቀበል አያስጨንቅ? እኔ ብቻ ኩዊር የሆንኩ ይመስለኝ ስለነበር “ጤነኛ አይደለሁም” እል ነበር:: ማታ ማታ እንቅልፍ አጣለሁ፤ አምርሬ አለቅሳለሁ:: በሰውም፣ በቤተሰብም፣ በሃገርም መጠላት ቀላል አይደለም:: ያስደብታል፣ ያስጨንቃል፣ ያማል! 

ሁለተኛው ራስን ካለመቀበል ቀጥሎ የአዕምሮ ጤናዬን የተፈታተነኝ ሌላው ተግዳሮት ራስን ለመለወጥ የሚደረገው ትግል ነው:: የወንድ ጓደኛ ይዤ ስለማይመቸኝ እቀይራለሁ፣ ስቀይር ለውጥ ይመጣል ብዬ በማሰብ:: ለውጥ ለማምጣት መታገሉ፣ ከማልፈልገው ወንድ ጋር መፍትሄ ይሆናል ብዬ ወሲብ ማድረጌ የአዕምሮ ጤናዬ ላይ ጠባሳን ጥሎብኛል:: ራስን በማስገደድ በሚደረግ ነገር ድባቴ ውስጥ ከቶኛል::  ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ራሴን ስቀበል መንገዱ አልጋ በአልጋ የሚሆን ነበር የመሰለኝ:: እርግጥ ራስን መቀበል ትልቅ ስጦታ ነው:: ነገር ግን ተግዳሮት ይቀጥላል:: 

ሶስተኛው ፈተና ጓደኝነት ምስረታ ላይ ነው:: አስታውሳለሁ አንድ እሁድ ቀን በጊዜው ከነበረችኝ ጓደኛዬ ጋር አብረን መቀጠል እንደማንችል እየተላቀስን አወራን:: እንዴት እዚህ ሃገር ላይ እንዲህ አይነት ግንኙነት ተስፋ ይኖረዋል በማለት ለመለያየት ወስነን እየተጯጯህን ነበር:: ነገሮች ሁሉ ጨለሙብኝ፣ ራሴን ተቀብዬ ከዛ ደግሞ ራስን አለመኖር ምን ይሉታል? ታዲያ ፈጣሪዬ ምንድነው ሃሳቡ? እኔ ማነኝ? ነገዬ ምንድነው? በውዝግብና ጭንቀት መሃል እየነዳች የነበረውን መኪና መሪ በቅፅበት ለመጠምዘዝ ታገልኩት፤ እንደምንም ፍሬን ይዛ ዳር ላይ ቆምን:: በጣም ደነገጥኩ! የልብ ምቴ ፍጥነቱ በጆሮዬ ተሰማኝ:: የማወራው ጠፋኝ፤ ጓደኛዬም እንደዛው:: ሳንጋጭ በሰላም ተለያየን:: ነገር ግን ያ ቅፅበታዊ ውሳኔ ከነበረኝ የአዕምሮ ጭንቀት እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ተረድቻለሁ:: 

እነዚህ ህመሞች ኩዊር ስለሆንን የመጡብን ሳይሆኑ ኩዊርነትን በማይቀበል ማህበረሰብ ውስጥ ስላለን የመጣብን ተግዳኖት ነው:: ችግሩ እኛ ወይም ማንነታችን ሳይሆን የማህበረሰብ ችግር ነው::

አሁን ላይ በጥሩ የፍቅር ግንኙነት ላይ ብሆንም የኩዊር ጉዞ ቀላል አይደለም ቤተሰብ፣ ቅርብ ጓደኛ፣ መንገደኛውም በተገኘው አጋጣሚ ስለመታሰር አንዳንዴም መገደል የሚማከሩብን ነን:: “እነዛንማ ዘላለም ማሰር ነው” ይላሉ አጠገባቸው ስላለው ምንም ሳያውቁ:: ይሄ ደግሞ ለአዕምሮ ጤናችን ትልቅ ተግዳሮት ነው:: የአዕምሮ ጤናችን በተለያየ አጋጣሚ ለተለያየ ህመም ሊጋለጥ ይችላል:: በግሌ አጋጣሚውን ስላገኘው የአዕምሮ ጤና ምክር አገልግሎት ረድቶኛል:: በተገኘው አጋጣሚ የምክር አገልግሎት ማግኘት ጥሩ መፍትሄ ነው:: ሌላው የአዕምሮ ጤናዬን ለመጠበቅ በማህበራዊ ሚዲያ በኩዊር ዙሪያ የሚመጡ እና የሚለቀቁ ጥላቻን የያዙ ነገሮችን ለሰኮንድ አላነብም፤ አላይም:: አካባቢዬም ላይ ተመሳሳይ ፃታ ጠል የሆኑ ሰዎችን አላቀርም እንደ እድል ሆኖ በቤተሰቤ ውስጥ ስለጥላቻ አይወራም ነገር ግን ጥላቻ ያላቸው ጓደኞችን ቀስ በቀስ አርቃለሁ:: ኩዊር ዙሪያ የሚፃፉ አስተማሪ እና አስናኝ ገፃችን እከታተላለሁ፣ መፅሃፎችን ሳገኝ አነባለሁ:: ከፍቅረኛዬ ጋር በየግላችን የተጓዝነው ጉዞ ምን ያህል ተፅዕኖ እንዳሳደረብን በግልፅ እወያያለሁ:: አለም አቀፍ የአዕምሮ ጤና ሳምንት እንደመሆኑ ኩዊር ኢትዮጵያውያን ለሆናችሁ ሁሉ ማለት የምፈልገው ብቻችሁም እንዳልሆናችሁ ነው:: ራስን የመቀበል ጉዞ ቀላል ባይሆንም ዛሬ ላይ የተሻሉ መረጃዎች ስላሉ እነሱን ማንበብ ፣ እርስ በእርስ በመቀራረብ አለን መባባል:: እያለፍንበት ስላለው የአዕምሮ ጭንቀትም ሆነ የተለያየ ህመም በግልፅ ልንወያይ ይገባል:: እነዚህ ህመሞች ኩዊር ስለሆንን የመጡብን ሳይሆኑ ኩዊርነትን በማይቀበል ማህበረሰብ ውስጥ ስላለን የመጣብን ተግዳኖት ነው:: ችግሩ እኛ ወይም ማንነታችን ሳይሆን የማህበረሰብ ችግር ነው:: የአዕምሮ ጤናችንን እንጠብቅ፤ እንከባከብ። ለሌሎች የተሻለ ነገ ለመፍጠር ዛሬ ላይ በግልፅ እንወያይ::

Leave a Reply