“ሰው … ማንነቱ መከበር አለበት”

ግንቦት 9 የተመሳሳይ ፃታ ተማርኮ፣ ትራንስ እና ከአንድ ስርዓተ ፃታ በላይ ተማርኮ ማንነቶች ባላቸው ሰዎች ዙሪያ የሚደርሱትን ጥላቻዎች፣ መብት ጥሰቶች፣ መድልዎ እና ጥቃቶች ግንዛቤ የማስጨበጫ ቀን ተደርጎ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ይከበራል:: (International Day Against Homophobia, Transphobia and Biphobia /IDAHOBIT)

ይህንን ቀን በማስመልከት የኩዊር ማንነት መብት ደጋፊ የሆነችውን እመቤት ለቃለ መጠይቅ ጋብዘናታል::

የተለያዩ ወሲባዊ ዝንባሌ እና ፆታዊ ማንነቶችን እንዴት ልትደግፊ ቻልሽ?

ደጋፊ መሆን የምርጫ ነገር አይመስለኝም:: እኩልነት፣ የሰዎች ክብር፣ የሰውነት መብታቸው መጠበቁ፣ ምርጫቸው መከበሩ እነዚህ ነገሮች ያንቺ እሴት ውስጥ ካሉ ወይም ዋጋ የምትሰጫቸው ነገሮች ከሆኑ ከዛ በኋላ ምክንያት ያለው ነገር አይደለም:: አውቶማቲክ ነው ማለት ይቻላል:: አብረሽ መሆን ትፈልጊያለሽ፣ መደገፍ ትፈልጊያለች:: ማድረግ በምትችይው ወይም ደግሞ ባንቺ ቦታ በሆነው ልክ መደገፍ ትችያለሽ ወይም ይኖርብሻል:: ከላይ የጠቀስኳቸው እሴቶችሽ ሲሆኑና ከዛ ውስጥ ሲመጣ ደጋፊ መሆን ከዛው የሚቀጥል ነገር ነው እንጂ የምርጫ አይመስለኝም:: ‘’እስቲ ዛሬ እንዴት ደጋፊ ልሁን?’’ ብለሽ ሳይሆን ዋጋ የምትሰጫቸው ነገሮች እነዚህ ከሆኑ አብሮ የሚቀጥል ነገር ነው የሚመስለኝ::

ከድሮም ጀምሮ የኩዊር ማህበረሰብ  ደጋፊ ነበርሽ?

ሁሌም ባልለው አሁን እንዳለኝ አረዳድ እና እውቀት ባላስብም ለምን ይሄን ያህል በጣም እንደምንጨነቅና እነሱን ለመጫን እንዲህ አድርጉ እያልን ለመጋፋት እንደምንሞክር አይገባኝም ነበር:: ድሮ ባንስማማም ብንስማማም የራሳቸው የሰው ምርጫ ነው፣ እኛን የማይነካን ወይም የማይጎዳን ነገር ከሆነ፣ ሰዎች በግላቸው በራሳቸው ህይወት ላይ የሚመርጡት ነገር ከሆነ ለምንድነው የምንጋፋቸው ከሚል ነበር አስተሳሰቤ እንጂ በንቃት መደገፍ አልነበረም::  በኋላ ላይ ግን ጉዳዮቹ በደንብ ሲገቡኝ ከምርጫም በላይ ማንነት እንደሆነ ሳውቅ ከዛ በኋላ በጣም ለረዥም ጊዜ ይሄንን ጉዳይ እደግፋለሁ ቅድም እንዳልኩት ድሮ ላይ የነበረኝ አስተሳሰብ አሁን ባለሁበት ደረጃ ልክ ባይገባኝም፣ ለምን ሰው እንደምንጋፋ ስለማይገባኝ “ለምን ሰው አይተዋቸውም፤ ለምንድነው የምንጨነቀው?!” የሚለው ነበር::

እንዲህ አይነቱ ድጋፍ ለምን አስፈላጊ ነው ትያለሽ?

በጣም አስፈላጊ ነው:: ምክንያቱ ሰው ስለሆንን ሰው ደግሞ ማንነቱ መከበር አለበት::በጣም ቀለል ያለና መሰረታዊ ነገር ይመስለኛል:: <<ሰው መከበር አለበት>>  የሚለው የሰው ልጅ እኩልነት እና ክብር አስፈላጊ መሆኑ የሚያጠራጥር ነገር አይደለም:: ከዛም በላይ ደግሞ ሰዎችን በተለይ ደግሞ በማንነታቸው የሚገለሉ ሰዎች፣ በማንነታቸው ማህበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት የሌላቸውን ሰዎች መደገፍ አስፈላጊ ነው:: የሰው ልጅ ከሁሉም መስመር የሚደርስብሽ ጥቃት፣ ተቀባይነት የሌለሽ እንደሆንሽ ወይም ማንነትሽ በጣም የሚጠላ እንደሆነ የሚሰማሽ ጥላቻ ተጨማሪ ድጋፍ ይፈልጋል ብዬ ነው የማምነው:: እንደውም ለማንኛውም የተጨቆነ ማንነት ከምትሰጭው ድጋፍ ይልቅ ለዚህ ትልቅ ድጋፍ መስጠት እንዳለብኝ ነው የማምነው ፣ ምክንያቱም ጥላቻ እና መገፋት ከሁሉም ቦታ ስላለ አንቺ ደግሞ በራስሽ በኩል መደገፍ አለብሽ ብዬ አስባለሁ:: እውነትም ደግሞ ይሄ እኩልነት ያለበት አለም፣ መብት የሚከበርበት አለም፣ የሰዎች ማንነት ከሰውነት እንዳያሳንሳቸው የምትፈልጊበት አለም እንዲፈጠር ከፈለግሽ ኩዊር ሰዎችን መደገፍ እና እዛ ማንነት ላይ የሚመጣውን ጭቆና መቃወም ግዴታ ነው:: ምክንያቱም የተወሰኑ ሰዎች ያነሱበት አለም ሌሎቻችን እኩል የሆንበት አለም የእውነተኛ ፍትህ ያለበት አለም ስላልሆነ:: 

አንቺ  ድጋፍሽን በምን መልኩ ነው የምትገልጭው?

የመጀመሪያው ነገር የራስን ቦታ በማወቅ ነው:: የኩዊር ማህበረሰብ አካል ወይም ያንን ማንነት እንደሌለው አካል ቦታን ማወቅ፣ እነዚህን ማንነቶች መረዳት ነው:: እኔ የማደርገው ነገር ራሴን ማሳወቅ ከዛ ደግሞ ለአመታት በማህበረሰቡ ያለፍኩባቸውና የተማርኩባቸውን ትክክል ያልሆኑ እና መጥፎ አስተሳሰቦች መመርመር እና አለመማር ነው:: ሌላው ሁልጊዜ መጠየቅ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ:: ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ባለው በጣም አደገኛ ሁኔታ ሁልጊዜም ክፍት በሆነ መልኩ ድጋፍ ላታሳይ ትችያለሽ ነገር ግን ቢያንስ በአካባቢሽ በማህበረሰብሽ ጥላቻን አለመታገስ አንደኛው ነው:: ለምሳሌ በቤተሰብ እና በጓደኛ መሃል ውይይቶች ሲደረጉ እና እነዚህን ማንነቶች ወይም ኩዊር ሰዎችን የሚቃወም፣ የሚያሳንስ ነገሮች ስትሰሚ መናገር፣ ሰዎችን ማስተማር በተለይ ደግሞ ከነሱ የተሻለ እኔ ከኩዊር ማህበረሰብ በተሻለ የተጠበቀ ቦታ ነው ያለሁት ምክንያቱም የኔ ሃሳብ እንደአስተያየት ሊቆጠር ይችላል፤ ተቃራኒ ፃታ አፍቃሪ ስለሆንኩ:: ‘’አስተያየቷ ነው’’ ተብሎ ስለሚታሰብ ከምለው ነገር ጋር ባይስማሙም ቶሎ ወደ ጥላቻና ወዲያው ወደድርጊት ላይመራ ይችላል:: ስለዚህ እኔ የተሻለ ቦታ ላይ ስለሆንኩ በሄድኩበት ቦታ ሁሉ መሟገት እችላለሁ፤ ስለኩዊር ሰዎች መጥፎ ነገር ሲወራ ከሰማሁኝ መናገር አለብኝ ብዬ ስለማምን እናገራለሁኝ:: በተለይ ደግሞ ለመማር ክፍት የሆኑ ሰዎችን እንዲማሩ አግዛለሁኝ:: መረጃዎች መስጠት ሊሆን ይችላል፣ የሚያነቡት፣ የሚያዩት ወይም የሚያዳምጡት ነገር መስጠት:: ከምንም በላይ ግን ራሴን ማሳወቅና በንቃት እንዲህ አይነት ጥላቻ ውስጥ አለመግባት በጣም ትልቅ ስራ ነው:: ምክንያቱም ብዙ ሰዎች አሉ እዚህ ጥላቻ ላይ የሚጨምሩ እና እንደድጋፍ ስርዓት ወጥተሽ ባትሟገቺ እንኳን እዚህ ጥላቻ ላይ አለመጨመር በጣም ትልቅ ነገር ነው:: በተለይ እንደኢትዮጵያ ያለ ሃገር ላይ ለጥላቻ ብዙ ቦታ ስላለ አንደኛው የጥላቻ አካል አለመሆን ነው:: ብዙ ጊዜ የማደርገው ራሴን ማሳወቅ፣ ሁልጊዜም ለመማር ክፍት መሆን፣ ሰዎችን መጠየቅ፣ እና ሰዎችን ማስተማር ነው:: 

ሌሎች ኢትዮጵያውያን የኩዊር መብት ደጋፊ ወይም አጋር እንዲሆኑ ምን ይረዳቸዋል ብለሽ ታስቢያለሽ?

ይሄ ጥያቄ ከባድ ነው አይደል? ኢትዮጵያ ውስጥ ጥላቻ እንዳይኖር ማድረግ በራሱ አጋር ለመሆን ከመድረስ በፊት ጥላቻው ራሱ እንዲቀር ማድረግ ለኔ የመጀመሪያው ትልቅ ደረጃ ይመስለኛል:: ሁልጊዜ በጣም የሚያሳስበኝ ሰዎች እንዴት ነው ሌላን ሰው እንዳይጠሉ ማድረግ የምንችለው የሚለው ነው:: ጊዜ የሚፈጅ ነገር ነው ግን ደግሞ እኔ ቢያንስ በማወራቸው ሰዎች ሳይ በጣም በተደጋጋሚ እዚህ ጉዳይ ላይ በማውራት በተወሰነም ቢሆን ለውጥ አያለሁ፣  ሙሉ ለሙሉ መቀበል ባይሆንም ጥላቻውን ግን እንዲተዉ፤ በሰዎች ማንነት ላይ ያለ ጥላቻን እንዲተዉ የማድረግ ለውጥ አያለሁኝ::

አሁን ለብዙ አመታት የማውቃቸው ጓደኞቼ ስታይ አለም አቀፍ ኩዊር ማህበረሰብንም ስታይ የምናውቃቸው የምንወዳቸው አርቲስቶች ራሳቸው እየገለጡ በመጡ ቁጥር የተለመደ ነገር እየሆነ ነው:: ፊልሞችና ዘፈኖች ላይ እየተለመደ በመጣ ቁጥር እንደድሮ በጣም ከኛ የራቀ ነገር አይደለም፤ እየቀረበ መጥቷል:: ስለዚህ ሁሌም በምንሰራው ስራ እነዚህን ጉዳዮች ማቅረብ!  እኔ አጠገቤ የማውቀው ሰው፣ የምወደው ሰው፣ የምወደው ቤተሰቤ ይሄ ማንነት ሊኖራቸው ይችላል ብሎ ማሰብ ሰዎችን ይረዳል ብዬ አስባለሁ:: በተለይ ደግሞ ከጓደኞቼም ሆነ ቤተሰቦቼ ጋር ስለኩዊር ጉዳይ ሳወራ የማደርገው ነገር አንድ ኩዊር የሆነ ሰው ከኩዊር ማንነቱ በላይ እንዲያስቧቸው ነው:: አንድ ሰው ያ ብቻ አይደለም ወስባዊ ወይም ፃታዊ ዝንባሌሽ አንድ ማንነትሽ ሊሆን ይችላል ግን ከዛ ውጪ የሆኑ ብዙ አይነት ማንነቶች አሉሽ እና ሰውን እንደዛ ሙሉ አድርጎ ማሰብ ይገባል:: ኩዊር ሰዎች ማንነታቸው ላይ ጨምረው እንዲያስቧቸው እና በዚህ ብቻ እንዳያይዋቸው ሳደርግ <<ሰው>> የሚለውንም መመዘኛ በዛ ውስጥ ያይዋቸዋል አይደል? በአንድ አይነት ማንነት ብቻ ስታይ ወደጥላቻ ያመራል ነገር ግን ሰዎች ብዙ አይነት ማንነት እንዳላቸውና በአንድ ማንነታቸው ብቻ እንዳይወስኗቸው ሲያደርጉ ትንሽ ሰውነት ይሰጠዋል እና እሱ በጣም ይረዳል ወይም እኔ ባወራኋቸው ሰዎች ረድቷል:: ደጋፊ ባልላቸውም ጠላትና ጠል እንዳልላቸው አድርጓል:: ሌላው የሰዎች ታሪክ በጣም ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ::

ስለኩዊር ሰዎች ስናወራ ከእኛ በጣም የራቀ ወይም ውጪ ብቻ ያለ የሚመስለው ሰው አለ ወይም ደግሞ በቃ እንደሰው ሁላ የማያስበው ሰው አለ በጣም እንግዳ የሚሆንባቸው ሰዎች አሉና ወደእኛ ቀረብ ስታደርጊው ጓደኛዬ ሊሆን ይችላል ጓደኞቼ ሊሆኑ ይችላሉ ወይም የቤተሰቤ አባል ውስጥ ሊሆን ይችላል እኛ ውስጥ ያለ ሰው፣ የምንወዳቸው ሰዎች ናቸው ብሎም ማወቅ በጣም ይረዳል ብዬ አስባለሁኝ::

ኢትዮጵያዊ ለሆኑ የኩዊር ማህበረሰብ የምታስተላልፊው መልዕክት አለ?

በርቱ! በጣም ይገባኛል ምን ያህል ከባድ ህይወት እንደሆነ ግን እውነትን መርጦ መኖር በራሱ ትልቅ ነገር ነውና የእናንተ መኖር በራሱ ለዚህ ሃገር ላለው እኩልነት በጣም ትልቅ ነገር ነው:: የእውነተኛ ማንነትን መርጦ መኖር ትልቅ ትግል መሆኑን እንድታውቁ እና እንድትበረቱ ነው::

Leave a Reply