ኩዊርነት በክልል ከተሞች

እኔ በክልል ከተማ ነው ተወልጄ ያደግኩት። የክልል ከተማ ያለው ማህበረሰብ ከዋና ከተማ ማህበረሰብ ነዋሪ በተወሰነ መልኩ ወግ አጥባቂ ነው። ቀላል ለሚባሉ ጉዳዮች ሳይቀር የሚሰጠው የተጋነነ ሀሳብና አስተያየት አብዛኛው ነዋሪ ፈጣሪውን ፈርቶ ሳይሆን ሰው ምን ይለኛል ብሎ ተጠንቅቆ የማህበረሰቡ ጥርስ ውስጥ ላለመግባት እየጣረ ሲኖር ማየት የተለመደ ነው።   ለኔ ከባድ ከነበሩት መካከል ላጋራችሁ 

የመጀመርያው ከባዱ ነገር ራስን ከመቀበል በፊት ባለው ከራስጋ በሚደረግ አለመግባባት ስሜት ውስጥ እያለንስለ ኩዊርነት ምንነት ፣ ይሄ ስሜት ተፈጥሯዊ እንደሆነ ፣ አለም ላይ ብዙ እኛን የሚመስሉ ሰዎች እንዳሉ ፣ ብቻችንን እንዳልሆንን ወዘተ የሚነግሩን ኩዊር ሰዎችን የምናገኝበት አጋጣሚ ቀላል አለመሆኑ ነው። 

በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ኩዊር ሆነን የተፈጠርን ሰዎች ምን ያህል የህይወት ፈታኝ ግዜያትን ፣ አካላዊና መንፈሳዊ ጫናዎችን ልናሳልፍ እንደምንችል መገመት ቀላል ነው።

እኔ እንኳን ብዙ ኩዊር ወዳጆችን ያገኘሁት ወደ አዲስ አበባ በምሄድበት አጋጣሚ እንጂ አንድም ቀን በኔ አካባቢ ያለ ኩዊር ጓደኛ ኖሮኝ አግኝቼም አላውቅም። ነገር ግን ሰዎችን ማግኘት ማውራት ስጀምር የህይወት ልምዶቼን ሳጋራቸው ከነሱም ስማር ምናለበት ቀደም ብዬ ላውቃቸሁ በቻልኩ እላለሁ። ምክንያቱም በግዜው እንደዚህ የማወራው ሀሳቤን የምገልፅለት ኩዊር ጓደኛ ቢኖረኝ ባውቅ ኖሮ ከራሴጋ አለመግባባት  ተፈጥሮብኝ በነበረ ወቅት ምን ያህል ነገሮች ይቀሉኝ እንደነበር ስለሚገባኝ።

ሌላው ደግሞ እንደ እድል ሆኖ ራሳችንን እንደሚሰማን ስሜት ተቀብለን አክብረን የፍቅር ህይወታችንን ለመኖር የክልል ከተሞች የቆዳ ስፋት ምቹ አያደርግልንም ። 01 ቀበሌ የተፈሳ ፈስ 05 ለመድረስ ግማሽ ሰአት አይፈጅበትም የከተማ ስፋት ማነስን ተከትሎ የመዝናኛ ቦታዎች በአንድ አካባቢ ብቻ ተወስነው እንዲገነቡ ሆነዋል ያ ማለት ደሞ እንደልብ በነፃነት እጅ ለእጅ እንኳን ተያይዞ ተዝናንቶ ለመግባት የማይታሰብ ነው ምክንያቱም ምናልባት ከቤተሰብ ወይ ከሰፈር  ወይ ከቸርች ወይ ከትምህርት ቤት አንድ ሰው እዛ ቦታ ላይ ሊያየኝ ይችላል የሚል ስጋት ስለሚኖር። 

በተለይ የአለባበስ ምርጫቸው በተለምዶው አባባል ልጠቀምና “ወንዳወንድ” የሚባሉ ኩዊር ሴቶች ላይ ያለው ጫና ከፍተኛ ነው። ብዙ ግዜ ለአካላዊ ጥቃትም ተጋላጮች ናቸው።  በደምብ አስታውሳለሁ ግዜው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ነበር ። ትምህርት ቤቱ መንፈሳዊ ስለነበር በውስጡ በኮምፓሽን የሚረዱ ልጆችን ይዟል። ከነሱ መሐል ለፕሮጀክቱ ታዳጊ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ውስጥ የምትጫወት ክላስሜት ነበረችኝ። ልጅቷ አለባበሷ አነጋገሯ አበላልሏ አካሄዷና ድምጿ ልክ “እንደወንድ” ስለነበር ትምርህት ቤት ውስጥ እሷን በሚመለከት ብዙ የሚሰጡ አስተያየቶች ነበሩ ከነዛ መሐል “እሷኮ ያ ነገር ነች፣ ካምፕ ውስጥ ስለሚቆዩ እዛው እርስ በእርስ ነው የሚነካኩት” ወዘተ .. 

በዚህም የተነሳ የወጣት ክርስቲያን ህብረት ስናደርግ ብዙ ግዜ በሚባል ሁኔታ የፌሎሺፕ መሪዎቻችን ያሸማቅቋት እንዳትሳተፍም ጭምር ያደርጓት ነበር ። ከሷጋ በጣም የቀረበ ጓደኝነት ስለነበረኝ ብቻ እንኳን እኔ ላይ የነበረው ቁጣ በራሱ ቀላል የሚባል አደለም። አጋንንት እንዳለባት በሽተኛ ይቆጥሯት ስለነበር በግድ ሊፀልዩላት ይፈልጋሉ ያንን ስለምታቅ በጣም ውስጧን ይጎዱት ያሳዝኑት ነበርና ልጅቷ ከዛ በኋላ አንድም ቀን ቸርች አካባቢ ደርሳ አታወቅም። በነሱ ንግግርና ሀሜት ሳብያ ከኔ ጋርም የነበራት ጓደኝነት ተበላሽቶ ቀረ። 

እንግዲህ በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ኩዊር ሆነን የተፈጠርን ሰዎች ምን ያህል የህይወት ፈታኝ ግዜያትን ፣ አካላዊና መንፈሳዊ ጫናዎችን ልናሳልፍ እንደምንችል መገመት ቀላል ነው። 

ባጠቃላይ ኩዊርነት በክልል ከተሞች ላይ በጣም  ትልቅ ጥንቃቄንና ትኩረትን የሚጠይቅ ራሱን የቻለ ከባድ ሀላፊነት ነው።  እያንዳንዱ እርምጃችንን ተጠንቅቀን እንድንጓዝ ምንያህል ትኩረት እንደሚፈልግ ተረድተን ለራሱ ህይወት ሀላፊነት እንደሚሰማው ወጣት የምንቀሳቀስ ከሆነ ግን የማንወጣው የማህበረሰብ የታጠረ አስተሳሰብ አይኖርም።

Leave a Reply