መልካም የኩራት ወር ቤተሰብ

ከጥቂት ዓመታት በፊት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥነበርኩ። ኅዘን በማስተናገድበት ወይም ኅዘን ውስጥ በምሆንበት ጊዜ፣ ስናደድ ወይም መጎዳት ሲሰማኝ ያለመተኛትና ያለመብላት ዝንባሌ አለኝ። ይህ ሁኔታ አስቸጋሪና ወደ ሳምንት ገደማ የሚዘልቅ ነው። ይህን ሁኔታዬን ለማንም መንገር አልፈልግም ነበር፤ ለቤተሰቤም ቢሆን፤ እናቴ ለብቻዬ ልትተወኝ ትሞክራለች። ከትንሽ ቀናት በኋላ ስለኔ ደኅንነት እጅግ መጨነቅ እንደጀመረች ተረዳሁ፤ እናም ሥጋቷን ለመቀነስ ከሷ ጋር ወጣ ብለን ትንሽ እንድናወራ ወሰንኩ።

ከትንሽ ጭውውት በኋላ እናቴ እንዲ አለችኝ  “ልክ አንድ ነገር ሲያስጨንቅኝና ላወራው የማልችለው ነገር ሲሆንብኝ ወደ ቤተ-ዕምንት እሄዳለሁ፤ ከፈጣሪዬ ጋር ለማውራት ወይም ከማያውቁኝ ጋር ስላስጨነቀኝ ነገር አወራለሁ። ይሄኛው አማራጭ ግምት ቢወስዱብኝ ወይም ቢፈርዱብኝ  እንኳን እስካላወኳቸው ድረስ ብዙም አያስጨንቅኝም። እያለፍሽበት ያለውን ነገር ለመናገር ቀላል ላይሆንልሽ እንደሚችል እገምታለሁ፤ ምናልባትም ሙሉ ዐቅምሽን አሰባስበሽም ቢሆን ለመናገር ከባድ ሊሆንብሽ ይችላል። ግን ለምን ልክ አንቺን የሚመስሉሽ ጋር ሄደሽ አታወሪያቸውም?”

ከቀድሞና የረጅም ጊዜ የፍቅር አጋሬ ጋር ትልቅ የማያግባቡን ነገሮች ውስጥ ነበርኩኝ። ነገሩን ለእናቴ የምገልጽበት ቋንቋ አልነበሩኝም እሷም ከሌላ ሴት ጋር ያለኝን ግንኙነት የምትረዳበት ቋንቋ ይኖራታል ብዬ አላሰብኩም።

እናቴ 71 ዓመቷ ነበር፤ እናም ለሷ ማንነቴን ማሳወቅ አስቤውም አላውቅም፤ ስለኔ ኩዊርነት ሃሳቡ ኖሯትም እንደማያውቅ ገምቼ ነበር። እናም በተደጋጋሚ ወንድ በጭራሽ እንደማላገባ ከማወጅ ባለፈ ስለኩዊርነቴ በግልጽ ከእናቴ ጋር አውርተን አናውቅም። ያም ብቻ አይደለም ለሷ (አሁንም ቢሆን) ምልክት ሰጥቷት አያውቅም፤ እየተጎዳሁበት ባለሁበት ሁኔታ ውስጥ እንኳን፤ ግራ በመጋባትና ርግጠኛ ባለመሆን ውስጥም ቢሆን የደኅንነቴ  ጉዳይ ቅድሚያ የምትሰጠው ነገር ነው። ልዩ መሆኔን መቀበል ችላና ልዩ መሆኑ ተቀባይነት የሌለው ነገር እንደሆነም መረዳት ችላ ነበር። 

ከዛም እናቴ “የኔ ወደሆኑ ሰዎች” ጠቆመችኝ። ድጋፋቸውን ሊሰጡኝ እንደሚችሉ አውቃለች፤ እናም እሱን ነው ያደረኩት። “እኔን ወደሚመስሉኝ ሰዎች” ሄድኩኝ። እናቴ ጥላ የሚሆኑኝ ሰዎች እንዳሉኝ ተሰምቷታል። አምሳያዎቼ የሆኑ LGBTQI ሰዎች።

እናም ደገፉኝ፤ ወገኖቼ፤ የኔ ኩዊር ማኅበረሰብ፤ የኔ ጥላ ከለላ።

መልካም የኩራት  ወር ቤተሰብ

Leave a Reply