የኩራት ቀን፡ የነፃነት እፍታ

ለመጀመሪያ ጊዜ ፕራይድ የተካፈልኩት ከሃገር የመውጣት ገጠመኙ ተፈጥሮ ነው፤ ከአንድ አምስት ስድስት አመት በፊት:: አንድ የአውሮፓ ከተማ ላይ በጣም በትልቁ ደምቆ የተከበረበት ቀን የመጀመሪያው ትውስታዬ ነው::

ልክ አዲስ አበባ ላይ እንዳለው እንደታላቁ ሩጫ ዋና ጎዳናዎችን በተለያዩ ሙዚቃ እና ዳንሶች ታጅቦ ኩዊር ማህበረሰብን ማየት እንዴት እንባ አያስመጣ! የደስታ እንባ!

ነፃነት ለካ እንደዚህ ደስ ይላል፤ ራስን ሆኖ መኖር! ከጥግ እስከጥግ ከተለያዩ ህብረቀለማት አሸብርቃ ማየት! ማክበር መከበር ደስስስስ ይላል::

 ከማይረሱኝ ነገሮች ውስጥ ሶስቱን በአጭሩ ላካፍላችሁ::

“ነፃነት ለካ እንደዚህ ደስ ይላል፤ ራስን ሆኖ መኖር! ከጥግ እስከጥግ ከተለያዩ ህብረቀለማት አሸብርቃ ማየት!
ማክበር መከበር ደስስስስ ይላል::”

1. ደስታ እና ፌሽታ

በሺዎች የሚቆጠሩ ከተለያየ ሃገር እና ዜግነት የተወጣጡ ኩዊር ሰዎች ደስ በሚሉ ትዕይንቶች እና ሙዚቃዎች ታጅበው ቀናቸውን በደስታ እና ፌሽታ ሲያከብሩ ማየት በጣም ስሜታዊ አድርጎኝ ነበር:: ከኢትዮጵያ እንደመምጣቴ ደግሞ አስቡት:: በየሰፈሩ ለሰርግ ፕሮግራም መንገዶች እንደሚዘጉት ዋና ዋና ጎዳናዎች ለዚሁ የኩራት ቀን ተዘግተው በትልቁ ሲከበር ማየት ደስ ይላል:: የተለያዩ ኩዊር አርቲስቶች በሙዚቃ እና ዳንሶች አዝናንተውናል:: አላፊ አግዳሚው እያየ በአውራ ጎዳና ላይ እንደብሔራዊ በዓል ሲከበር ማየት እንዴት ስሜታዊ አያደርግ!  ለካ ይሄም ይቻላል አስብሎኛል፤ ምናልባትም አንድ ቀን ተራው የኢትዮጵያ ይሆናል:: 

2. የተለያዩ ስርዓተ – ፃታዊ ዝንባሌዎች እና አገላለፅ 

የተለያዩ ስርዓተ ፃታ ዝንባሌዎችን መተዋወቅ እንዲሁም ማንም ሰው የወደደውን ለብሶ በዓሉ ላይ ማየት ትልቅ ትምህርት ነበር:: ምንም እንኳን በኩዊር ዣንጥላ ውስጥ ብሆን የመጣሁበት ጥብቅ ባህል ከሁለትዮሹ የስርዓተ ፃታ አለም (ወንድ እና ሴት) ውጪ መኖርን እንዳላይ ጋርዶኛል:: ለዚህም የኩራት ቀን በዓሉ የመደሰቻ ብቻ ሳይሆን የመማሪያም ጊዜ ነበር:: ከመማር ብቻ ሳይሆን የሰዎችን የተለያየ ማንነት የማክበሪያ! ያደኩበት ማህበረሰብ “የሴት ይመስላል ይቅርብኝ” “የወንድ ነው ይሄ አይሆንም” እየተባባሉ…ገና ለተወለደው ልጃቸው ሰማያዊ ኬክ እየቆረሱ..ለሴት ልጃቸው ሐምራዊ እያለበሱ..ብቻ በሁለትዮሽ ተጋርጄ ስላደኩኝ..የተለያዩ አገላለፆችን ለማየት መቻሌ ደስ ብሎኛል:: ኩዊርነት ከእኔ ሌዝቢያንነት በላይ ጥልቅ እና ሰፊ መሆኑን አስገንዝቦኛል::

3. እምነት

አብዛኞቻችን በቤተሰብ ምክንያት የተለያየ ኃይማኖት ውስጥ አድገናል:: ይሄ ደግሞ ኩዊርነት እና ኃይማኖት አብረው የማይሄዱ ብለን በትልቅ ፈተና እንድናልፍ ወይም አሁን ድረስ ለብዙዎች ጭንቅ እንዲሆን እንቅፋት ሆኗል:: 

በዚህ በዓል ላይ ከተለያዩ እምነት የተወጣጡ ኩዊር የቤተ እምነት አገልጋዮችን ማየት በጣም አስደስቶኛል:: የተለያዩ ፅሁፎችን የያዙ የቤተ ክርስቲያን አስተማሪዎች ነበሩ:: “ክርስቶስ ይወዳችኋል” “ክርስቶስ ይወደኛል” እና የመሳሰሉትን:: ለብዙዎች ራስን መቀበል ከሚያከብዱ ነገሮች መሃል ኃይማኖት ትልቅ ቦታን እንደመያዙ እንዲህ አይነት ግሩፖችን ማየት ራስን ለመቀበል ትግል ላይ ላሉ ነግሮችን በትንሹም ቢሆን ያቀላሉ እና እጅግ ደስ ይላል::

Leave a Reply