ለ “ዴቲንግ” ፈቃድ

የርቀት ፍቅር ግንኙነት ላይ ነበሩ፣ ውጪ ሃገር የምትኖረዋ አብረው አዲስ አበባ ላይ ከቆዩ በኋላ ወደውጪ የምትመለስበት ቀን ስለነበር ወደ አየር ማረፊያ እየወሰድኳቸው ነው::

ተቃቅፈው የፍቅር ቃላትን እየተቀባበሉ ከኋላ ተቀምጠዋል፤ አየር ማረፊያ እንደደረስን ጊዜያቸውን እየተሻማሁባቸው ስለመሰለኝ የግል ጊዜ እንዲኖራቸው ብዬ ከመኪናዬ ወረድኩ:: ቻው እስኪባባሉ ውጪ ላይ እንደቆምኩ ለመለያየት ያላቸው ጭንቀትና ፍርሃት ተሰማኝ፣ ምናለ እነዚህ ሁለት የተፋቀሩ ሴቶችን በመሃላቸው ያለውን ርቀት ማቀራረብ ብችል ብዬ ተመኘሁ:: በወቅቱ በሰፊው ያለያይዋቸውን ውቂያኖሶች ለጥቂት ደቂቃዎች ማጥፋት የምችለው ወደአየር ማረፊያው በመውሰድ መሆኑን ለመገንዘብ ትንሽ ደቂቃዎች ፈጅቶብኛል:: የኔ የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪነት ለእነሱ ራሳቸውን መሆን ፍቃድ ሆኗቸዋል:: አዲስ ፍቅር ውስጥ ያሉ ሁለት ሰዎች ቻው እየተባባሉ:: ስለደህንነታቸው መጨነቅ አላስፈለጋቸውም፣ ፍቅራቸውን መደበቅ አልተገደዱም፤ ወይም እንዴት መሆን እንዳለባቸው አላስጨነቃቸውም:: ይልቁንስ በጣም አስፈላጊው ነገር ላይ ነው ያተኮሩት፤ እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ያለምንም ገደብ  ቻው መባባልን::

የኔ እዛ ቦታ መገኘት ፈቃድን ሰጥቷቸዋል እኔ፥ ባህር በቅርብ በለቀቅነው ፓድካስታችን (“በአዲስ አበባ የሌዝቢያን ትውውቀ (ዴቲንግ) ጅማሬ”) ላይ እንዳለችው “በምርጫ ቤተሰብ” ስለሆንኩ ነው::

ምንም እንኳን ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ መሆን የሚያመጣው ተግዳሮት ቢኖርም፣ ባህርም በቀልድ እያዋዛች አዲስ አበባ ላይ ያለውን የትውውቅ ጅማሬ (“ዴቲንግ”) ከግል ልምዷ ጋር አጫውታናለች:: ከመተዋወቅ ጀምሮ እስከ ዘላቂ ፍቅር እና በዛም ውስጥ ያሉትን ችግሮች እያወጋች የልብ ትርታ ያለው ሰው መሆን ምን ማለት እንደሆነ ታስታውሰናለች:: 

በገበያ ማዕከል በአጋጣሚ የተዋወቁ ፣ ከመተዋወቅ ያደገው ፍቅራቸው አሁንም ጠንክሮ እንደቀጠለ  ስለምታውቃቸው አንድ ፍቅረኛሞች በዝርዝር ስታጫውተን በውስጣችን ላለው የፍቅር ስሜት ተስፋን ይሰጣል:: ምንም እንኳን እኛ ልምዱ ባይኖረንም ይህ ሊሆን እንደሚችል ማወቃችን በፌስቡክ ሰዎችን በጓደኞቻችን ወይም በጓደኛ ጓደኛ ይበልጥ ለመተዋወቅ እንድንሞክር ያበረታታናል::

ወደ አየር መንገድ ያደረስኳቸው ፍቅረኛሞች ከብዙ አመት በኋላ አሁንም ደስተኛ ሆነው አብረው አሉ፤ በምርጫ ቤተሰብ መሆናችንም እንደቀጠለ ነው:: ፍቅራቸው ህይወት፣ነፃነት እና የትውውቅ ጅማሬ (“ዴቲንግ”) የማይታበል መብታችን እንደሆነ ያስታውሱኛል::

የትውውቅ ጅማሬን (“ዴቲንግ”) ቀጥሉበት፣ በማያ አንጄሎ ቃላት “በፍቅር ላይ እምነት ለመጣል የሚያስችል በቂ ድፍረት አንድ ተጨማሪ ጊዜ እና ሁልጊዜ አንድ ተጨማሪ ጊዜ ይኑረን።”

ለባህር መልካም ዕድል እንመኝላታለን:: እድለኛዋ ሴት ወደእርሷ መንገዷን ታግኝ!

Leave a Reply