“ኩዊር ግን ምን ማለት ነው?” ፊዮና ስለ”ዴቲንግ” ያወራንበት ፖድካስት ላይ ጠይቃናለች:: ይሄንን ጥያቄ የጠየቅናቸው ኩዊር ሰዎች ምላሻቸውን እነሆ፥
“ኩዊር ለእኔ ነፃነት፣ ጥንካሬ እና አካታችነት ነው:: ነፃነት ስል እንደቃሉ በአንድ በተወሰነ ስያሜ ጋር የሚጣጣም ማንንነት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ማንነቶቻችንን የማሰስ ነፃነት ማለት ነው:: ጥንካሬ ስል በህይወት ለመኖር የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች ለማለት ነው:: አካታች ምክንያቱም ገደብ የሌለው ለሁሉ የተፈጠረ እና ያቀፈ ቦታን የሚያገልፅ በመሆኑ ነው::”
– መ
“ራሴን ስያሜ አልሰጠውም ነገር ግን ሰዎችን ጌ ወይም ሌዝቢያን ከምል ኩዊር ማለት ይቀለኛል:: የተለያዩ ሰዎችን በአንድ አቅፎ የያዘ ነው:: ነፃ የሚያደርግ እና ከወሲባዊነት ባሻገር ያለን ማንነት ፈጥሯል:: ነፃነትን ይሰጣል::”
– ራሔል
“ኩዊር ነፃነት ነው:: ኩዊር ወሲባዊነት እና ስርዓተ ፃታን ለራስ በሚሰማን መልኩ የመግለፅ መብትን ይሰጣል:: ኩዊር አለምን የመቃኛ እና የማሰብያ መንገድ ነው:: ኩዊር ሰዎች እነሱ ለራሳቸው በሚሰማቸው መልኩ በወሲባዊ ዝንባሌ እና ስርዓተ ፃታቸው መቀበል ነው:: ኩዊር ለሁሉም ሰው መብት መታገል ነው ፣ የተሰማቸው እንዲሰማቸው እና ስርዓተ ፃታ እና ወሲባዊ ዝንባሌያቸውን ከጭንቀት ነፃ በሆነ መልኩ መኖር እንዲችሉ መታገል ነው፣ ከሚጠበቅብን ነገር ውጪ የሆነ ነፃነት እና ራሳችን ይገባናል በምንለው መልኩ ራስን የመሆን ፍቃድ ነው::”
– ብስራት
“ ለኔ ኩዊር ማለት
- ራሴን አለመመደብ
- የነፃነት ትግል ማለትም ሌላውን ሳልጎደ የፈለኩትን እንደተሰማኝ ማድረግ
- ጥብቅ ኢትዮጵያዊነት/ክርስትና/ተቃራኒ ፃታ አፍቃሪ ብቻ ልክ እና የተባዕታይ ስርዓት የበላይነትን / ባህልን መቃወም መቻል
- ከራሴ እና ከምወዳቸው ሰዎች ጋር ጤናማ ግንኙነት ለመመስርት የሚሰራ ጥረት
- ፍቅርን በሰፊ መንገድ ለመለማመድ መቻል
- ማንነቴን ለማወቅ የዕድሜ ልክ ጀብዱ
- በመኖሬ እንዳፍር ያደረገኝን እያንዳንዱን ነገር አጥብቄ መቃወም
- የኩዊር ሰዎች በነፃነት፣ ያለሃፍረት፣ ጭቆና ወይም አመፅ እንዲኖሩ ከሚታገሉት አካል መሆን”
– ኤክሰ
“ኩዊር ነኝ” ስል በአጭሩ ተቃራኒ ፃታ አፍቃሪ አይደለሁም ማለት ነው:: ወይንም ከራሴ አልፌ የሌሎችን የተለያዩ ስርዓተ ፃታ እና ወሲባዊ ዝንባሌዎች እደግፋለሁ፣ አከብራለሁ ማለትም ነው:: ኩዊር በጉብዝና መኖር ማለት ነው:: ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ + ወንድ/ ሴት በሆነች ሃገር ላይ “ኩዊር ነኝ” ስል ምንም እንኳን በማንነቴ ህጋዊ ባልሆን መኖሬን እቀጥላለሁ የሚል መፈክሬ ነው:: ኩዊር የሌሎችን የህይወት ተግዳሮት ለማዳመጥ ጊዜ መስጠት እና መረዳት ነው:: ኩዊር የሰው ልጅ ጭቆናን ማውገዝ ማለት ነው:: ኩዊር ራስን መውደድ መቀበል ነው::
– ኢ