ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ጠልነትን መቋቋም

“ስለህመማችሁ ዝም ካላችሁ፤ ገለዋችሁ ደስ ብሏቸው ነበር ይላሉ” ዞራ ኒል ኸርትሰን 

ከተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ ጠል ሰዎች ጋር መገጣጠም ሁሌም የሆነ የሚያስደነግጠኝ ነገር አለ:: ሁሌም የመጀመሪያው አፀፋዊ መልሴ መደነቅ ነው፣ ግራ ያጋባል አውቃለሁ ምክንያቱም የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪያንና ትራንስ ጀንደር ሰዎች ቅድሚያ አረዳድ ጥላቻ እንደሆነ አውቃለሁ:: መንገድ ላይ “ቡሽቲ” ብሎ ሌላውን መሳደብ ወይም አንድ ሰው ማህበራዊ ሚድያ ላይ ሙሉ ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪያን ላይ ጥላቻን የያዘ ቪድዮ ሰርቶ መልቀቅ ሊሆን ይችላል፤ ሁሌም በዝምታ ውስጥ ያስደነግጠኛል:: ቀጥሎ የሚመጣው የቁጣ ስሜቴ ይዘገያል::

ዝምታዬ ጥላቻቸው የሚፈጥርብኝን ህመም ወድጄው እንዲመስላቸው ወይም ሲከፋ ይሄ ይገባኛል የሚል መልዕክት እንዲልክ አልፈልግም::

የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪያንን መሰቀል እና ቆዳ መገፈፍን የሚደግፉ በኢትዮጵያውያን የተለቀቁ ጥቂት ቪድዮዎችን አይቻለው:: በጣም ጉልህ የሆኑ ቪዲዮች ናቸው፣ እውነታዎች ምንም ለውጥ የማያመጡበት እና ዓላማው በኩዊር ሰዎች ዙሪያ የሚነገሩ የስህተት እና ጎጂ ንግግሮችን መድገም፣ ኩዊር ሰዎችን በማስፈራራት እንዲደበቁ ማድረግ እና ሌሎች ኩዊር “እንዳይሆኑ” “መከልከል” ነው::  ለኩዊር ሰዎች እና የኩዊር መብት ደጋፊዎች ላይ የሚያነጣጥሩት ስድብ የያዙ ምላሾችም ተመሳሳይ የሃሳብ መስመርን የያዙ ናቸው::

አብዛኛውን ጊዜ የሚሰማኝ ድንጋጤ ወደ ዝምታ የሚወስደኝ ህዝቡ የሚሰነዝርብንን ጥላቻ ለመወያየት ካለመፍቀድ ወይም ካለመፈለግ ነው:: ይሄ ያሳስበኛል ምክንያቱ ዞራ ኔል ኸርትሰን እንደምትለው ዝምታዬ ጥላቻቸው የሚፈጥርብኝን ህመም ወድጄው እንዲመስላቸው ወይም ሲከፋ ይሄ ይገባኛል የሚል መልዕክት እንዲልክ አልፈልግም:: እየቸገረኝ ያለው ጥላቻቸው ማንነቴ ላይ ምንም ተፅዕኖ ሳይኖረው መቋቋሜን በምን መንገድ ማሳየት እንደምችል ነው::

ለራሴ መቋቋሜን የማሳይበት መንገድ ራስን በማይጎዳ መልኩ ለኩዊር ሰዎች መብት በመቆም ነው፣ ራሴን ኩዊር ነኝ ሳልል የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አድርጌ መታገልን፥ ሁሉም ሰው በነፃነት የመኖር መብቱን ማስጠበቅ:: ሌላው ደግሞ ቤተሰቦቼን እና የቅርብ ጓደኞቼን ለኩዊር መብት እንዲታገሉ ማንቀሳቀስ ነው፤ ኩዊር ባለመሆናቸው ቀጥተኛ አደጋዎችን መቀነስ ይችላሉ:: በተጨማሪም ጥላቻዎች ሲኖሩ ኩዉር ወዳጆቼ ጋር የተሰማኝን ህመም እና ድንጋጤ በግል አወራቸዋለሁ:: ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ ጠልነትን ባያስቆመውም፣ ብዙ ሳላብራራ የሚረዳኝን ሰው ማግኘት ሁልጊዜ ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ የትክክለኝነት ስሜትን ይሰጣል:: በበኩሌ እነዚህ ውይይቶች ቅልል ያለ ስሜት እንዲሰማኝ ያደርጋሉ::

ለእኔ የሚቸግረኝ በየቀኑ በእኛ ላይ በሚሰነዘረውን ጥላቻ ምክንያት ቀስ በቀስ አለመሞት ነው:: ከፈቀድንለት ይገድለናል::

Leave a Reply