“በራሴ እንዴት እንደምኮራ ለመግለፅ ቃላት ያጥረኛል”

“ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመኖር አንድ የምትይን ነገር ምንድነው?” ብለን አዲስ አበባ ውስጥ የምትኖር ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ ሴት ጠይቀን ነበር መልሷም እነሆ

“ስሜቱ ብዙ እና ውስብስብ ስለሆነ አንድ ነገር ብቻ ማለት የሚቻል አይመስለኝም::  ከጥሩ ስሜቶቹ ጀምሬ በመጥፎው ከምጨርስ እስቲ መጥፎ ስሜቶቹ እና ጎኖቹን ላጫውታችሁ:: ከቤቴ ስወጣ የተቃራኒ ፃታ አፍቃሪ ካባዬን ሁሌም አጠልቃለሁ፣ ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ ጠል ከተማ ላይ ጥላቻው በየት እና እንዴት ሊመጣ እንደሚችል ስለማላውቅ ሁሌም ዝግጁ ነኝ፣ ለመጠላት እና ምላሽ ላለመስጠት:: ከታክሲ ውስጥ ያወቃችሁት ሰው፣ አብራችሁት የምትሰሩት ሰው፣ ማንነታችሁን ያልነገራችኋቸው ጓደኞቻችሁ፣ እናም የቤተሰብ አባላት ጥላቻውን ሊሰነዝሩ ይችላሉ:: እንደ”ተቃራኒ ፃታ አፍቃሪ” ምንም ምላሽ መስጠት ያቅተኛል፤ አንዳንዴ “ስለሰው ምን አገባን” እላቸዋለሁ… ውስጤ ማለት የሚፈልገው “ስለኔ ህይወት ምን አገባችሁ?!” ቢሆንም:: አቤት የሰው ልጅ ጥላቻ! ቃላቱ ከየት እንደሚመጣላቸው ራሱ ግራ ይገባኛል፤ እውነት አሁን አንድ ሰው ማንነቱን ቢያውቁ እንዳሉት ይወጉት ይሆን እላለሁ?! ጓደኞቼ የምላቸው ሲሆኑ ደግሞ ጭላንጭል ቢያገኙ እንደሚክዱኝ ወይም አሳልፈው ሊሰጡኝ እንደሚችሉ አስባለሁ:: ሁሌም አዕምሮዬ እነዚን ያውጠነጥናል:: ውጥረት ነው! “ዛሬ ደግሞ ምን ሊሉ ይሆን?” ጭንቀት! በዚሁ ምክንያት ብዙ የቅርብ ጓደኞች አርቄአለሁ፣ ከቤተሰብ ጋር ያለኝንም ጊዜ በጣም ቀምሻለሁ:: ከብዙ ጥላቻ ይበልጥ ደግሞ ወቅቶች አሉት ኢትዮጵያ በጥላቻ የምትናጥበት… ጀርባዬን ቁንጥጥ አድርጎኝ እውልና ቤቴ ስገባ ሊደክመኝ ከሚገባው በላይ ድክም ይለኛል:: “አታገቢም እንዴ?” የሚሉት ጥያቄዎች ደግሞ ሌላ ድካሞች ናቸው:: የቱ ጋር ታብራራላችሁ? ባልፈልግስ? ብቸኝነት ብመርጥስ? ይሄንን እንኳን ለማለት በማይቻልበት የጭቆና መዓት ውስጥ እንዴት ስለማንንነት ይነሳል:: ካባዬን እንዳጠለኩ አለሁ:: የማወቀው ቤቴ ስገባ፣ ኩዊር ጓደኞቼ እና ማንነቴን በነፃነት እንድኖር ከሚያበረታቱኝ ጓደኞቼ ጋር ስገናኝ ብቻ ነው:: 

በብዙ ጥላቻ መሃል መኖር ውስጥ ቆሞ መገኘቴን አደንቀዋለሁ:: እንደሚለፈለፍብን ጥላቻ እና ዛቻ ቢሆን አልቀን ነበር::

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ምን ደስ ይላል መሰላችሁ? ጥላቻን ተቋቁሞ የእለት ተእለት ኑሮን መምራት መቻል:: በራሴ እንዴት እንደምኮራ ለመግለፅ ቃላት ያጥረኛል:: ራስን መምረጥ ትልቅ ነገር ነው፣ ለሰዎች አልኖርም ብሎ ማወጅ ትልቅ ስጦታ ነው:: ምንም እንኳን የተቃራኒ ፃታ ካባዬን ማድረግ ብገደድም ውስጤ ሰላም መሆኑ ያስደስተኛል:: መምረጥ ያለብኝን ጓደኞች ማወቅ መቻሌ፣ የምሄድባቸው እና የማገኛቸውን ሰዎች መምረጥ መቻሌ፣ ቤተሰቦቼ የራሳቸውን ኑሮ ኖረዋል… አሁን ደግሞ እኔ ለእኔ መኖር አለብኝ ላይ መድረሴ ያኮራኛል:: የኩዊር ጓደኞቼ ጋር ምሳ ሆነ እራት መብላት አንድ ተቃራኒ ፃታ ጠል የሆነ ሃገር ወይም ከተማ ላይ አይታሰብም ነገር ግን ተገናኝነትን እንበላለን፣ እንዝናናለን፣ በስራ እንደጋገፋለን:: በብዙ ጥላቻ መሃል መኖር ውስጥ ቆሞ መገኘቴን አደንቀዋለሁ:: እንደሚለፈለፍብን ጥላቻ እና ዛቻ ቢሆን አልቀን ነበር:: ነገር ግን ከድካም ስነቃ አዲስ ቆዳዬን ደግሞ ይዤ እንቀሳቀሳለሁ፣ ማንም ምንም ቢል መኖር መቀጠሌ አይገርምም ታዲያ?! በጥላቻ ውስጥ ሁሉ ለራስ ፍቅር መስጠት መቻል አያስደስትም?! ድብን ይበል ጠላት እኔ መኖሬን እቀጥላለሁ 🙂 እንግዲህ በአጭሩ ኑሮ ይህቺን ትመስላለች… የደስታም የሀዘንም እንባ የተሞላባት ይበልጥ ግን መቋቋምን እና ብዙ ስለራስ ማንነት የምማርባት ጎዳና ናት:: ተስፋዬ የትላንት ጭንቀቴ ምስክር ስለሆነ በዚህ ሁሉ ውስጥ መኖርን በእየለቱ እመርጠዋለሁ::”

Leave a Reply