ሌዝቢያን መሆኔን ከተቀበልኩ ጀምሮ ለተለያዩ ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች በግልፅ ነግሬያቸዋለሁ:: ቅርብ ከምላቸው ጓደኞች አንስቶ በስራ አጋጣሚ እስካገኘኋቸው ሰዎች ድረስ:: ለእነዚህ ጓደኞችና ባልደረቦች ለመናገር የሚያነሳሱኝ ሁለት ምክንያቶች ናቸው፣ አንደኛ ይቀበሉኛል ወይም ምንም አይመስላቸውም ሲሄን ሁለተኛው ደግሞ የት ያገኙኛል አላውቃቸው አያውቁኝ የሚለው አስተሳሰብ ነው:: አብዛኛውን ጊዜ የመጀመሪያ ምክንያቴ ስህተት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ በጥቂቱም ቢሆን ዋጋም አስከፍሎኛል::
ለረዥም አመት አብረን የነበርን የቅርብ ጓደኛዬ በጣም ስለሰው መብት የምትከራከር፣ ደግ እና ለሰው አዛኝ ናት:: ለሷ ለመንገር ስወስን ሁለቴ እንኳን አላሰብኩኝም:: ይህቺ ጓደኛዬ በደንብ ታውቀኛለች አውቃታለሁ፤ ጥሩ ጊዜዎችን አብረን አሳልፈናል:: ለመንገር በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን የምለው ሁሉ ሲጠፋብኝ አስታውሳለሁ:: ከምንድነው የሚጀመረው? የትኛውን ቃል ነው የምጠቀመው? ደግሜ ደግሞ ኧረ እሷ ይሄ አይጠፋትም እላለሁ:: ከነገርኳት በኋላ የነበረው ፊቷ ዛሬም ድረስ ይታየኛል:: የቀይዳማ ፊቷ ፍም ለበሰ… የእሷ ፍም መልበስ ይበልጥ እኔን አስደነገጠኝ:: ለደቂቃዎች ማለት ይቻላል ምንም አላወራንም:: ለአመታት ካወቀችኝ እና ጓደኛዬ ካልኳት አንደበት [ወንድ ጓደኛ ስላልተሳካ እዚህ ላይ ደረሽ?] የሚለውን አልጠበኩም:: ለሰው ልጅ መብት ሁሌም የምትከራከረው የኔ መብት እና ማንነትን እንዴት መረዳት ያቅታታል? የተናገረችኝ ነገሮች ልብን ይሰብራሉ:: ለአመታት የቆየንባቸው ጓደኝነት ታድያ ምኑ ላይ ነው? እሷ በምታስበው መንገድ መመላለስ ነው? ከሁሉም የባሰው እንደዛ ተባብለን በተለያየን ማግስት “ስላንቺ እያሰብኩ ራሴን አመመኝ” የሚለው የስልክ መልዕክት ነው:: ራስን ተቀብሎ ለሌላው ማካፈል ላይ ለመድረስ ያለውን ውጥረት እና ፈተና ዜናውን ለሚቀበለው ሰው አይታየውም:: ጓደኛዬም ዜናውን ስለእሷ አደረገችው:: የፍቅር ጓደኛ ጋር መለያየት እንዲህ አይከብድም… የክህደት ስሜቱ ለመዳን ጊዜን ይወስዳል:: ከዚህ አይነቱ ክህደት ሙሉ በሙሉ መዳኔን እኔንጃ ነገር ግን ከማንኛውም ጓደኛ…ይቀበሉኛል ብሎ ማሰብ የዋህነት እንደሆነ አስተምሮኛል:: ለማያውቁት ሰው መብት መከራከር ቀላል ነው፤ አጠገብ ያለው ግን ትልቅ ፈተና!
… ለሌላው የቤተሰብ አካል መናገር እንደሌለብኝ አጥብቆ መከረኝ…እርግጥ ዛሬ ላይ መናገር አልፈልግም ነገር ግን እሱ በነፃነት በሚኖርበት አለም ላይ ለኔ በሚስጥር ይዞ መኖርን መምረጡ አስገርሞኛል፤ አስቆጥቶኛልም::
በቅርቡ ደግሞ ለአንድ ዘመዴ ልነግረው ወስኜ ተገናኘን… ይሄም ዘመዴ ከዘመዶቼ ሁሉ ነፃ የሆነ ነው:: ባህልና ሀይማኖትን መጠየቅ እና መፈተሽ የሚወድ ጎልማሳ ነው:: ስለማንነቴ እያጫወትኩት በመሀል ያቋርጠኝና እንዴት ምርጫ እንደሆነ ሊከራከረኝ ይጀምራል:: “ምርጫሽን እደግፋለሁ ግን…” ይለኛል:: ብዙ ላጫውተው ያሰብኩትን ጣልቃ እየገባ ልቤን ዝቅ አደረገው:: ጭራሽ እንዴት ዛሬ ትነግሪኛለሽ አለኝ:: ቀጥሎም ለሌላው የቤተሰብ አካል መናገር እንደሌለብኝ አጥብቆ መከረኝ…እርግጥ ዛሬ ላይ መናገር አልፈልግም ነገር ግን እሱ በነፃነት በሚኖርበት አለም ላይ ለኔ በሚስጥር ይዞ መኖርን መምረጡ አስገርሞኛል፤ አስቆጥቶኛልም::
ተቃራኒ ፃታ አፍቃሪ ሰዎች ግን በምን አይነት አለም እንደምንኖር ያውቃሉ? እንዲህ አይነቱን ትልቅ ሚስጥር እና ማህበረሰቡ ፈተና ያደረገብንን ነገር “ሎተሪ ደረሰኝ” አይነት ዜና የሚጠብቁት ለምንድንነው? ማን ስለዚህ በአካባቢያችን በነፃነት ሲያወራ አየንና ነው መንገር የሚቀለን? ጠዋት ማታ ስለጥላቻ እና ዛቻ እየተወራ ምን ይጠብቀኛል ብለን ነው የምናወራው?
በዙሪያችሁ ያሉ ኩዊር ሰዎች ራሳቸውን አውጥተው መናገር እንዲችሉና መልካም ግንኙነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ምን እያደረጋችሁ ነው? ከመብት ድጋፍ ባለፈ አጠገቤ ያለው ሰው ነው ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ? ሰዎች ስለማንነታቸው ሲነግሯችሁ ትልቁ ስጦታ በጥልቅ ማዳመጥ ነው:: ይሄ ስለእናንተ አይደለም፣ የእናንተ መድረክም አይደለም:: አንድ ሰው አምቆ የያዘውን የማንነት ክፍል አምኗችሁ እያካፈላችሁ ነው እናም ዝምታን ይፈልጋል:: ለአብዛኞች የመጀመሪያ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ማለት የፈለግነውን ነገር ጊዜ መውሰድ ይኖርብናል፣ ሰዎች ታሪካቸውን ስላካፈሉን አመስግነን “የመጀመሪያዬ ነው እንዲህ አይነት ገጠመኝ እወድሻለሁ(እወድሀለሁ) በደንብ ተረጋግቼ ላስብና ደግሞ እንወያያለን” ማለት የመጀመሪያው መግቢያ ማድረግ እንችላለን::
እንደኔ አይነት ገጠመኝ ያላችሁ ኩዊር ቤተሰቦች ደግሞ ስለገጥማችሁ ሁሉ አዝናለሁ፤ የመጨረሻው እንደሚሆንልንም ተስፋዬ ነው። ለሌሎች መናገር ግዴታ አይደለም እና ያሉንን ኩዊር ቤተሰቦችና የእኛን መብት አጥብቀው የሚከራከሩልንን ጠበቅ አድርገን በእነሱ ግንኙነቶች ውስጥ በሰራናት ትንሽ አለም ውስጥ ሙሉ ማንነታችን መኖር ነው። ብዙ ብናጣም ጥቂቶች ብዙን ሆነውልናልና ዙሪያችን በጥቂት ብዙዎች ይብዛልን።