ሦስተኛው የንስንስ እትማችን ለንባብ በቅርቡ እንደምትበቃ ስንነግራችሁ በደስታ ነው። በራስን ማሳወቅ (መግለጥ) ጉዳይ ላይ ስንመራመር ሰዎች ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ራሳቸውን የሚያሳውቁባቸው (የሚገልጡባቸው) በርካታ ተሞክሮዎችና መንገዶች ተመልክተን በጣም ስንደነቅ ነበር ።

ከዚህ በታች ከንስንስ የተወሰዱ ሐሳቦች እና የተሳታፊዎቹ ቃላት ኃይለኛ እና አንደበተ ርቱዕ እንዲሁም እንደ ኩዊር ሰዎች ያለንን ጥልቅ እና የተለያየ ተሞክሮ ያሳያሉ። ራስን ማሳወቅ ጉዞ ነው፤ መጽሔቱን ለእናንተ ለማካፈል እንናፍቃለን።
‘ሌዝቢያን’ ብዬ ጉግል ያደረኩበት ቀን ይመስለኛል እራሴን የተቀበልኩበት ቀን። ከዚህ በፊት ስሜቱ እንዳለሽ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን መቀበል አትፈልግም ምክንያቱም አስቸጋሪ ይሆንብሻል።”
– ዮሃና
“ለአባቴ ራሴን አሳወኩት፣ እናም ያ ተሞክሮ ሁሉ ነገር ነው፤ አባቴ በጣም ተረድቶኝ ስለነበረ ተስፋ ማድረግ የምችለው ሁሉ ነበር። ወላጆቻቸው ልጆቻቸው ስለማንነታቸው ሲነግሯቸው ፊልም ላይ የምናያቸውን ሁሉ አደረገ፣ “ኦ፣ አውቃለሁ። እወድሻለሁ. የፈለግሽውን መሆን ትችያለሽ …”
– ብሌን
“ይመስለኛል ኩዊር ማንነቴ እድሜዬ እየጨመረ ሲመጣ አድጓል ምክንያቱም ራስን በጥልቅ መውደድ እንዴት እንደሆነ መማር ትጀምሪያለሽ። ቤተሰቤን እና ማኅበረሰቤን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መውደድን እንደተማርኩ ያህል ነው። እናም አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ነገሮች የሚጋጩ ይመስላሉ ፣ ነገር ግን እንችላለን፣ ምንም ባንግባባም ወይም ባንስማማም እንኳ እኛም አንዳችን ቦታ መሰጣጣት እንችላለን ።”
– ሚከሊና
“ይህን የኩዊር ማኅበረሰብ ካገኘሁ በኋላ ነው ራሴን ሙሉ በሙሉ የተቀበልኩት። ብዙ ሰዎች ራሳቸውን ሲቀበሉ ማየት የሚያጽናና ነበር” አለች። “ይህ ምንም ማለት እንዳልሆነ እና እንደ ትልቅ ነገር መታየት እንደሌለበት ሳውቅ መጨነቄን አቆምኩ”።
– ዮርዳኖስ
“ምንም እንኳን [ወንድሜ] በአልጋ ላይ ከያዝን ከቀናት በኋላ ምንም እንደማይፈጠር ላረጋግጥላት ብሞክርም፣ [የፍቅር ጓደኛዬ] ወደ ቤተ ክርስቲያን በኃይል ቢወስደንስ ወይም ለቤተሰብ ቢናገርስ ወይም አንቺን በማበላሸት ቢወቅሰኝስ ወይም ለፖሊስ ቢናገርስ … የሚል ስጋት አድሮባት ነበር። ሌሎች በርካታ ሁኔታዎችን ማሰላሰል ቀጠለች።”
– ብ
“ድምፄን ዝግ አድርጌ “ሌዝቢያን ነኝ” አልኳት:: የሹፈት ሳቅ ሳቀች…”I don’t accept this” ብዙ ተመላለስን… ለማስረዳት ሞከርኩ፤ አልተሳካልኝም:: እንዴት ቻው እንደተባባልን አላስታውስም:: ቤቴ ገብቼ በጣም አለቀስኩ፣ ጓደኝነት ምንድን ነው? ብዙ አወጣሁ አወረድኩ:: በነገርኳት ነገር በጣም እንደተጎዳች ደጋግማ ፃፈችልኝ:: ምንም ጥያቄ አልጠየቀችኝም፤ አላዳመጠችኝም:: ደጋግማ ሐጢያተኛ እንደሆንኩ እና ወደራሴ እንድመለስ ፃፈችልኝ:: መልዕክቶቹን አነብና ደግሜ እንዳላነባቸው አጠፋቸዋለሁ። የለመድኩት “ሳምሪዬ ዛሬ የት እንሁን?” አይደሉማ! በጣም ልብ የሚሰብሩ ነበሩ። በጣም ስለምንዋደድ ብቻ ሳይሆን የሴቶች መብት ዙሪያ ያላት ጠንካራ አቋም፥ አትቀበለኝም ቀርቶ ለማዳመጥ ይከብዳት ይሆናል የሚል ምንም ጥርጣሬ አልነበረኝም። ለመጨረሻ ጊዜ ስመልስላት የተሰማኝን ሁሉ ነው የፃፍኩላት፥ በይበልጥ ያተኮርኩት ደግሞ “ምን አይነት ጓደኝነት ነው ለማዳመጥ እንኳን ቦታ የማይሰጠው?” “እንዴት ይሄ ሁሉ አመት ስንዋደድ አንድ ማንነቴ እዚህ ላይ አደረሰሽ?” ላይ ነበር። ከሷ መልስ አልነበረም።”
– ኤ
“አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ቦታ ቁርሀን እንዲቀራልኝ አደረኩ ሌላውን ሳልናገር ለማዘር ጭንቀት እንዳለብኝ ብቻ ነገርኳት። ለሁለት ወር በተከታታይ ቢቀራልኝም የነበሩኝ ስሜቶች (ለሴቶች ያለኝ ስሜት) አለመቀየሩን ሳውቅ በጣም መጥፎ ስሜት ውስጥ ገብቼ ነበር። እራሴን ምን ያህል እጠላው እንደነበር መግለፅ አልችልም። ሁልጊዜ የቆሻሻነት ስሜት እየተሰማኝ መኖር እንዳለብኝ ሳስብ ይበልጥ ሁሉም ነገር ይከብድብኛል እራሴን ማጥፋት ብዙ ግዜ አስቤያለው ግን የ እናቴን ሁኔታ ሳይ ያለእኔ ማንም እንደሌላት ሳይ ተወዋለሁ። “
– መ
“እንደ አንድ ወጣት ኢትዮጵያዊ ሰው እንዴትና መቼ ራስን ማሳወቅ አለብኝ ብለሽ ብትጠይቀኝ አፋጣኝ ምላሻዬ DON’T ይሆን ነበር። ይህ ምላሽ የተወለደው በፍርሃት እንደሆነ አውቃለሁ፣ ነገር ግን ከዚህ ፍርሃት በስተጀርባ ያሉት አደጋዎች እውነተኛ እና ጉልህ እንደሆኑ አውቃለሁ። ነገር ግን፣ ራስን ለማሳወቅ ከቆረጣችሁ፣ እንደ መኖሪያ ቦታ ያለ የራሳችሁን ገቢ ምንጭ ጨምሮ የድጋፍ እቅድ እንዲኖራችሁ እመክራለሁ እና ተመሳሳይ ተሞክሮ ካላቸው ሰዎች ድጋፍና ምክር ማግኘት ይኖርባችኋል። ደህንነታችሁ ማንነታችሁን ከማሳወቃችሁ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለውጥ የሚያመጣው ጤናማና በሕይወት እስካላችሁ ድረስ ብቻ ነው ። ስለዚህ የመጀመሪያው ምክሬ ሁልጊዜ ደኅንነትን ጠብቆ መኖር ነው፤ ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር ይመጣል።”
– እ