በዓላትን ከቤተሰብ ጋር ማሳለፍ ምን ይመስላል? ኩዊር የሆነችው እንግዳችን እንዲህ አጫውታናለች።
እንደኩዊር ሰው በዓላትን ከቤተሰብ ጋር ማሳለፍ ምን ይመስላል?
በበዓላት ላይ ቤተሰባቼ የተለያዩ የባህል ልብሶችን ለብሰው ቀኑን ሙሉ ሳሎን የተለያዩ ወሬዎች እያወራን እና የበዓል ፕሮግራሞችን ቲቪ ላይ በማየት ነው የምናሳልፈው። ልጅ እያለሁ በጣም የምወደው ጊዜ ነበር፤ አዲስ ጫማ እና ልብስ የሚገዛልን ሰሞን ነው፤ ከጎረቤት ልጆች ጋር አብር የመጫወቱ ፍቃድ ከሌላው ቀን በተለዬ ይኖራል። የእምነት በዓላት ቀን ደግሞ ሲሆን ቤተክርስቲያን በመሄድ ነበር የምናሳልፈው። ኩዊርነቴን ካወቅኩ ጀምሮ ግን በዓል ራሱን የቻለ ውጣውረድ አለው።
አብሮ ማሳለፉ መሳቅ መጫወቱ ቢያስደስትም እንደኩዊር ግን ማንነቴን መደበቄን ሁሌ የማስታውስበትም ቀን ነው። ሁሉም ግልፅ ሆኖ ሲጫወት ማንነቴን ቢያውቁ ምን ይሉኝ ይሆን የሚለውን አለማሰብ አይቻልም። ስለዚህ ያ ደግሞ ብዙ ሆነን ብንቀመጥም የብቸኝነት ስሜት አለው።

በምን አይነት መልኩ ነው በእነዚህ ጊዜያት የብቸኝነት ስሜት የሚሰማሽ?
ምናልባት በዓላት ላይ ስለሆነ ከሁሉም ጋር በአንድ ክፍል ጊዜ ኖሮን የምንገናኘው ይሄ ጥያቄ ከሌላው ቀናት በተለየ ያሳስበኛል። ምንም እንኳን ቤተሰቦቼ ስለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ያላቸውን አመለካከት ጠይቄ ባላውቅም ሃይማኖተኛ ከመሆናቸው አንፃር ዱብ እዳ እንደሚሆንባቸው አልጠራጠርም። ስለዚህ ሁሌ በዓላት ሲመጡ ምናልባት ይሄ ሁሉ የበዓል ስሜት ማንነቴን ቢያውቁ ይቀራል፤ የመጨረሻዬም በዓል ይሆን ይሆናል ያስብለኛል። በጨዋታቸው መሃል ስለማያውቁት ህይወቴ በሃሳብ እሄዳለሁ።
የፍቅር አጋርሽን ለበዓል ቤተሰብ ጋር ለማምጣት አስበሽ ታውቂያለሽ?
አዎ! ራሴን ከተቀበልኩ በሗላ የፍቅር አጋሬን እንደ ቅርብ ጓደኛዬ ለቤተሰቦቼ አስተዋውቄያቸው የተለያዩ በዓላትን አብረን አሳልፈን እናውቃለን። የመጀመሪያው በዓል ላይ አስታውሳለሁ ተራርቆ መቀመጥ፣ አለመተያየት፣ ብዙ ስለራሳችን አለማውራት ነበር፤ ያውቁብን ይሆን ወይን ፍራቻ። ምንም እንኳን ምን እንደሆንን ባያውቁም ቤተሰቦቼ ስለወደዷት በጣም ደስ ብሎኝ ነበር። በመጣችባቸው በዓላት ላይ ሁሉ ቤተሰቦቼ እንደ ቅርብ ጓደኛዬ በደንብ ነበር የሚንከባከቧት። ነገር ግን ሁሌም “አግብታችሁ ደግሞ ያሳየን” ትል ነበር እናቴ፤ “ተጋብታችሁ” ማለቷ ነው እያልንን እንሳሳቅ ነበር።
በዓላትን ከሌሎች ኩዊር ሰዎች ጋር አሳልፈሽ ታውቂያለሽ? ምን አይነት ጊዜ ነበር ወይም ምን አይነት የሚሆን ይመስልሻል?
ከኩዊር ጓደኞች ጋር በዓልን አሳልፌ አላውቅም። ምናልባት ግን ማንነቴን ከሚደግፉ ጓደኞቼ ጋር አሳልፌ የማውቀውን በዓል ማንሳት እችላለሁ። ለምናገረው እና ለምቀልደው ነገር ሁለቴ ሳልጨነቅበት ምን ይሉኛል ሳልል አንድ በዓልን አሳልፌያለሁ። ኩዊር ሙዚቀኞችን ከፍተን እያጣጣምን በወቅቱ ከነበረችው የፍቅር አጋሬ ጋር ስለግንኙነታችንን እንዲሁም የሚያስቁ ትዝታዎቻችንን እያነሳን በጣም ደስ የሚል ጊዜ አሳልፌያለሁ። ራስን መሆን እንዴት ሊገለፅ እንደሚችል አላውቅም “ይቀበሉኝ ወይ?” የሚለው ጥያቄ የለም በሃሳብ ጭልጥ ማለት የለም፤ ቦታው ላይ ሆኖ በሁሉ ነገር ሙሉ ሃሳብን መስጠት ነው። ይሄን አይነት ስሜት ከአጋሮች ጋር በማሳለጥፍ ከተሰማኝ ሌላ ኩዊር ከሆኑ ሰዎች ጋር ማሳለፍ የሚፈጥረውን ስሜት መግለፅ ያቅተኛል። አብዛኞቻችን ምናልባትም ተመሳሳይ የቤተሰብ አመለካከት ስለሚኖረን ጥልቅ የሆኑ ውይይቶችን በማድረግ በጣም ደስ የሚል ጊዜ እንደሚሆን አስባለሁ።
ከቤተሰብ ጋር ምን አይነት በዓል ብታከብሪ ትመኛለሽ?
እናቴ መቼ ታገቢያለሽ ወይም ትወልጃለሽ የማትልበት ፣ በሃሳብ የማልበርበት ፣ ማንነቴን ተረድተው ያለምንም ጭንቀት እንደልጅነቴ የማሳልፍበት… በዓል በመጣ ቁጥር ከአለባበሴ ጀምሮ እነሱን ለማስደሰት የማልሯሯጥበት ቀን ነው በዓል የሚሆነው። ነገር ግን ያ ስላልሆነ ዛሬ ላይ ሰላሳዎቹ ውስጥ ሆኜ በዓል በመጣ ቁጥር የሚጠይቁኝን ለመመለስ ወይም ለመሸወድ እዘጋጃለሁ።
1 thought on “ኩዊር፣ በዓላት እና ቤተሰብ”