አጫጭር ታሪኮች ከግል ማስታወሻ ላይ: የቅርብ ጓደኛዬ

ከስር ያቀረብንላችሁ  <<አጫጭር ታሪኮች ከግል ማስታወሻ ላይ>> ከኩዊር ማህበረሰብ በፍቃድ ከሚላኩልን የግል መልእክቶች፣ የግል ማስታወሻዎች እንዲሁም ግለ ታሪኮች ላይ እየቀነጫጨብን ወደእናንተ የምናደርስ ይሆናል። እነዚህ የፅሁፍ ቅንጭብጫቢዎች ልክ ህይወታችን አስልተን እንደማንኖራት ሁሉ የቆምንበትን የህይወታችንን ትክክለኛ ገፅ  የሚያመላክቱ  አንዳንዴ መግቢያ፣ ሌላ ግዜ ተሟልተው ያልተፃፉ እንዲሁም የተዘበራረቁ ፅሁፎች ናቸው። 


ይሄን ፅሁፍ ከምታነቡ ማንኛችሁም የኩዊር ቤተሰቦች የእናንተንም ማስታወሻ እንደምንቀበል በደስታ እያሳወቅን በetqueerfamily@gmail.com ኢሜይል እንድትልኩልን እንጠይቃለን። .

የሰዉን ጥላቻ በየቀኑ እያስተናገዱ መኖር እንዴት እውነት እውነት ይላል? ከቤቴ ስወጣ ስለአለባበሴ አንድ ሰው አስተያየት ይሰጣል፣ የማያውቀኝ የታክሲ ተሳፋሪ ስለ “ግብረሰዶም መስፋፋት” ይዘላብድልኛል፣ እና ሌሎችም። በዚህ ሁሉ ውስጥ ለጓደኛ አምኖ ራስን መግለጥ ትልቅ የአእምሮ ዝግጅት ይጠይቃል።  ማንነትን ለሌሎች ማሳወቅ ከቤተሰብ ቀጥሎ ለቅርብ ጓደኛ ይከብዳል። ሁለነገር ይወራና ማንነት ተሸፋፍኖ ያልፋል። 

ብዙ ዐመት ብንተወወቅም ማንነቴን ለመንገር ብዙ ጊዜ ወስዶብኛል… የነገርኩሽ ቀን እንዳልጨናነቅ ብለሽ ጥያቄ እንኳን አልነበረሽም፤ አልተቀያየርሽም።  በማንነት ዙሪያ አውርተነው ስለማናውቅ አዲስ ነገር ቢሆንም አዲስ ነገር እንዳልሆነ አድርገሽ ሌሎች ወሬዎችን ቀጠልሽ። “ያ ሁሉ መርበትበት ለዚህችው ነው እንዴ?!” አስብሎኛል። ያንቺ መቀበል ፍቅርን አስተምሮኛል፤ እውነተኛ ጓደኝነት በሁኔታዎች እንደማይገደብ አስታውሰሽኛል። ብዙዎች ማንነቴን ሲያውቁ መሸሻቸው ማንነቴን ለመግለፅ ቢያስፈራኝም፥ እንዳንቺ አይነቶች እንድ ሆነው ሺዎችን የሆኑ ስላሉ ደግሞ በጣም ደስ ይለኛል። 

ማንነቴን ከነገርኩሽ በሗላ ለቅርብ ጓደኛችን ነግሬያት አለመቀበል ብቻ ሳይሆን ገስፃ ጓደኝነታችንን ስታቋርጥ የሆንሽውን መቼም አልረሳውም፤ ቀን እና ማታ መልዕክት እየላክሽ ያፅናናሽኝን። በማንነትሽ መገፋትን ባታሳልፊውም ሁሌም ለመረዳት ያለሽ ጉጉት ያስደስተኛል። እውነት እድለኛ ነኝ። ሌላ  ብዙ አስር አመታትን እንድናሳልፍ ምኞቴ ነው። ለፍቅርሽ፣ ምክርሽና አለሁ ባይነትሽ በጣም አመሰግናለሁ። እወድሻለሁ። 

ጓደኛሽ AW

Leave a Reply