#2 የመጀመሪያ ፍቅር ምን ይመስል ነበር?

ገና የመጀመሪያ አመት የዩንቨርስቲ ተማሪ እያለሁ ነው…

በተለያየ አጋጣሚ  ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ከሴት ልጅ ጋር ፍቅር ይዞኝ ቢያውቅም ምን ማለት እንደሆነ ጠልቄ አስቤበት አላውቅም፤ ትልቅ ሚስጥር እንደሆነ ግን ያላማካሪ ገብቶኛል። ወደተመደብኩበት ዩንቨርስቲ ስገባ እንዲህ አይነቱን ነገር ከራሴ ጋር እማከራለሁ ብዬ ጭራሽ አላሰብኩም ነበር። እንደ ጓደኞቼ “ቦይሬንድ ጠብሼ” የካምፓስ ህይወትን እንደማጣጥም ነበር የማስበው። 

ታዲያ ገና በመጀመሪያ ወር እኔው ኮሪደር ላይ ካለች ስሟን መሲ እንበለውና ድብን ያለ የአይን ፍቅር ያዘኝ። እንዴት ተፈጠረ ጥሩ ጥያቄ ነው። በባህሪዬ በጣም ተግባቢና ተጫዋች ነኝ፥ በገባን በሳምንታት በየዶርሙ ካሉ ልጆች ጋር ተዋውቄያለሁ፥ ማታ አንዳችን ዶርም ሙዚቃ ስንሰማ እናመሻለን። መሲ ከነበርነው ልጆች አርፍዳ ስለመጣች አልተዋወኳትም ነበር። የሆነ ቀን ማታ ነው አንዳቸው ዶርም እንደለመድኩት ለማምሸት ስሄድ አንደኛው እንልጋ ላይ ጋለል ብላ የዶርሙን ጨዋታ እየኮመኮመች ነው። ኩዊር የሆናችሁ ሰዎች የአይን ለአይን መገጣጠምን ማስረዳት ያለብኝ አይመስለኝም፤ ልብ ስርቅ የሚያደርግ እይታን ተለዋወጥን። በቅፅበጥ ያ ሚስጥሬ ሲጋለጥ ተሰማኝ። በሙዚቃውና በጨዋታው መሃል “፥ ሜሉ፥ መሲ ትባላለች ኢንጅነሪንግ ዲፓርትመንት ናት አርፍዳ መጥታ ነው•••” እንደገና ተያየን፤ እንደገና ልቤ ስርቅ አለ። ምሽቱን ምንም ሳታወራ እኔም እንደተጫዋችነቴ ብዙ ሳላወራ ወደዶርም ሄድኩ። የተፈጠረውን ሳሰላስል እና የተሰማኝ ተሰምቷት ይሆን ስል አመሸሁ:: 

ከቀናት በኋላ በድጋሚ ተገናኘን፣ ብዙም አላወራንም… ምን እንደማወራ ጠፋብኝ እሷም ዝምተኛ ስለሆነች ነገሩን ያከብደዋል:: ከብዙ አለማውራት እና መዘጋጋቶች በኋላ አንድ ቀን ምሽት ላይ እኔ ዶርም መጣች:: አልጋዬ ላይ ቁጭ ብለን እያወራን ድንገት መሳም ፈለኩ:: ለመጠጋትም ለመጠየቅም ቋንቋው አልነበረኝም:: ከንፈሯን በመቅፅበት ሳምኳት… ድንጋጤ ወረረኝ:: ምንም ሳትል ካልጋ ዘላ ወደውጪ ወጣች… ቀጥሎ የሚፈጠረውን ማውራት ያለብኝን ማሰብ አልቻልኩም:: ደረጃውን ስትወርድ ተከተልኳት፤ ልትናገርብኝም መሰለኝ:: የመሳሜ ድንጋጤ እና የእሷ ምላሽ የፈጠረብኝ ድንጋጤ ተደራርቦ ምን ልበላችሁ… “የት ልግባ አስብሎኛል::  ጨለም ወዳለበት ፅድ ስር ቁጭ አለች፤ አጠገቧ ተቀምጥኩ:: “ይቅርታ” አልኳት ድምፄን ዝግ አድርጌ::  “ለምን እንደዛ አደረግሽ?” መልስ አልነበረኝም… ተነስታ ወደዶርም ሄደች፤ መልስ ለሌለኝ ነገር መከተል ይለብኝ ስላልመሰለኝ ከደቂቃዎች በኋላ እኔም ወደዶርሜ ገብቼ ተኛሁ:: 

ምናልባት ለሳምንት ያህል አላወራንም፤ ፍፁም እንደማይተዋወቅ ኮሪደር ላይ እንተላለፋለን:: አኩርፋለች በሚል ወደምንሰበሰብት ዶርምም ማዘውተሬን ተውኩኝ:: 

የሆነ ቀን ብቻዬን ዶርም ቁጭ ብያለሁ፣  አልጋዬ ፊት ለፊት ስለሆነ የሚያልፍ ሰው ያየኛል:: መሲ እንደድንገት ገብታ በሩን ዘጋችው፣ በድንጋጤ ካልጋዬ ተነሳሁ… ቃል አልተነፈስንም ለደቂቃዎች በሚሞቅ ትንፋሽ ውስጥ የዶርሙን በር ተደግፈን ተሳሳምን:: 

የማናውቀውን  የፍቅር ግንኙነት ሀ ብለን ከዛች ቀን ጀምሮ ጀመርን::…

እናንተም የምታካፍሉን ካለ በ etqueerfamily@gmail.com ልትፅፉልን ትችላላችሁ።

Leave a Reply