በተለያዩ አፍሪካ ሃገራት የመጓዝ እድሉ ቢኖረኝም የተሻለ የኩዊር ማህበረሰብ ቅንጅት እና እንቅስቃሴ ወዳለባቸው ሃገራት የመሄድ እድሉ አልነበረኝም:: በአጋጣሚ ሆኖ ወደአንደኛው አፍሪካ ሃገር የመሄድ አጋጣሚው ተፈጠረ:: ገና የአየር ትኬቴን ለመቁረጥ ስዘጋጅ ነበር የኩዊር መዝናኛ ቦታዎችን ኢንተርኔት ላይ ማሰስ የጀመርኩት:: ኢንተርኔት ላይ ያገኘኋቸው መረጃዎች ጉዞዬን ይበልጥ አጓጊ አደረጉት::
አንድ ቅዳሜ ቀን ወደአንዱ የኩዊር ባር አቀናሁ::
ብቻዬን ተቀምጫለሁ… አፍሪካ ውስጥ ያለሁ አልመስልሽ ስላለኝ አስር ጊዜ ዙሪያ ገባዬን እቃኛለሁ:: በግራዬ የወንድ ተመሳሳይ ጥንዶች በፍቅር እየተያዩ የልብ የልባቸውን ይጫወታሉ.. በስተቀኜ ስድስት የሚያወሩ ወጣቶች መጠጣቸውን እየተጎነጩ ይወያያሉ.. ይስቃሉ:: ብዙዎች ቆመው ይደንሳሉ::

ቤቱ አፍሪካውያን በሆኑ ኩዊር ሰዎች ደምቋል::
እንዴት ደስ ይላል! ሲያምሩ ስናምር! ነፃነት ሲያስቀና!
አዲስ አበባ ባር ውስጥ የነበረኝን ልምድ ማስታወስ ተገደድኩ:: ከፍቅር አጋሬ ጋር እየደነስን ፍቅረኛሞች ሳይሆን እንደሁለት የቅርብ ጓደኞች ስለምንነበብ ያለው የወንድ ጉንተላ:: የአቅመ ቢስነት ስሜቱ አይረሳም::
ያዘዝኩትን ውስኪ እየተጎነጨው ዙሪያዬን እንደፊልም መመልከቴን ቀጠልኩ:: ማን አየኝ አላየኝ የለም፤ ሁሉም በራሱ አለም ድምቅ ያለ ምሽትን እያሳለፈ ነው::
ስሜታዊ ያደርጋል.. በተለይዩ የአለም ሀገራት ተዘዋውሬ በኩዊር ባር ብዝናናም ይሄኛው ስሜት ይለያል:: አፍሪካ ውስጥ መሆኑ እንዴት ይደንቃል?! ከአዲስ አበባ ለመጣሁ ሌዝቢያን የኩዊር አፍሪካውያንን እንዲህ ያለ ነፃነት ማየት ተስፋን ይጭራል.. ግን ህልምም ይመስላል::
የኩዊር አቀንቃኙ የሊል ናስ “Someone Who Loves Me” ተከፈተ፤ የዘፈን ግጥሙ በእጃችን የተሰጠን እስኪመስል ሁሉም እኩል ያዜማል፤ ይደንሳል:: ብዙዎቹ እርስ በእርስ ይተዋወቃሉ ፥ ምናልባት የቤቱ ደንበኛ በመሆን ይመስለኛል:: ይህም ያለውን ድባብ ይበልጥ አድምቆታል::
ብቻዬን ስለተቀመጥኩ እና ምናልባትም ከዚያው እንዳልሆኩ ስላወቀ በስተቀኜ ካሉት ስድስት ጓደኛሞች አንዱ መጥቶ ራሱን አስተዋወቀኝ:: የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ ወንድ እንደሆነ፣ ከጓደኞቹ ጋር በስራ ተጠምደው ስለሚያሳልፉ ቅዳሜያቸው ጥሩ የመገናኛ እና መዝናኛ ቀን እንደሆነ አጫወተኝ:: እኔም ሌዝቢያን እንደሆንኩ እና ለጉብኝት እንደመጣሁ ነገርኩት:: በመሃል የሪሃና “Bitch Better Have My Money” ተከፈተ… ድሮ የምንተዋወቅ ይመስል እየጮህን አብረን ዘፈንን
Bitch better have my money!
Bitch better have my money!
Pay me what you owe me
Bitch better have my
ከጓደኞቹ ጋር እንድቀላቀል ጋበዘኝ፤ ሁሉም በፈገግታ ተቀበሉኝ:: የወንድ ተመሳሳይ አፍቃሪ ጥንዶች፣ አንድ ሌዝቢያን፣ ትራንስ ሴት እና የተቃራኒ ፃታ አፍቃሪ ኩውር አጋር ናቸው:: የብዙ አመት ጓደኞሞች እንደሆኑ አጫወቱኝ… ከኢትዮጵያ መምጣቴን ስነግራቸው የመጀመሪያው ጥያቄ የእኛ ማህበረሰብ ምን እንደሚመስል ነበር ” ኢትዮጵያ ኩዊር ህይወት እንዴት ነው? እንደዚህ መዝናናት ይቻላል?” ብዙ አውርቼ ምሽቱን ላበላሸው አልፈለኩም… ያለውን እውነታ ግን ነገርኳቸው:: ምንም እንኳን ከእኛ የተሻለ ነፃነት ቢኖር ከመሃላቸው አንዳንዶቹ ቤተሰባቸው እንደማያውቅ ነገሩኝ፤ ባህሉ እና ሃይማኖቱ አሁንም ብዙዎችን እንደሚያታግል አጫወቱኝ:: ነገር ግን በነፃነት ባር ሄዶ መዝናናቱ እና በአደባባይ ማፍቀር መቻሉ ጭቆናውን እንደሚያቀለው ተማመንን:: ስለሃገራችን ሁኔታም የእያንዳንዳችንን ጥንካሬ አስታወሱኝ:: “በጣም የሚደንቅ ነው ቢያንስ እዚህ እስራት የለም በጣም ጠንካሮች ናችሁ” አለኝ።
መጠጥ ጋበዙኝ ፣ ሰልፊ አብረን ተነሳን… ስንደንስ ቪድዩ ተቀራረፅን.. ሁኔታዬን ስለሚያውቁ “ማህበራዊ ሚድያ ላይ ማናችንም አንለጥፍም ለእኛ ማስታወሻ ነው”:: የሆነ ቦታ በድጋሚ እገናኝ ይሆናል ተባብለን የዋትስ አፕ ስልክ ቁጥር ተለዋወጥን… ያ ምሽት የማልረሳው ምሽት ነው:: አንድ አንድ ቀን ፎቶዎቹን ከፍቼ ፈገግ እላለሁ፤ በቪዲዮዎቹ ውስጥ ነፃነትን ድጋሚ አጣጥማለሁ::
ከሁሉም በላይ ደግሞ ለካ ጠንካሮች ነን! በጥላቻ መሃል ነፃነትን ያወጅን ጠንካሮች!