ሁላችንም ሺላ አዲያምቦ ሉሙምባ ነን

ማሳሰቢያ፡  ቀጣይ ፅሁፍ መደፈርን ያትታል

ሌላ ትርጉም የለሽ ሞት ። ሌላ በአጭር የተቀጨ ሕይወት። ሺላ አዲያምቦ ሉሙምባ የ25 ዓመት ወጣት ነበሩ። ሺላ ከሁለትዮሹ ስርዓተ ፆታ ውጪ ያሉ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ኬኒያዊ ሲሆኑ “ወንጀላቸው” ኩዊር መሆናቸው ብቻ ነበር። ተደፍረው ተገለዋል። እኔ ልሆን እችላለሁ። ማናችንም ልንሆን እንችላለን። አንዳችን እንሆናለን። መቻቻል በሌለባቸው ማኅበረሰቦች ኅዳግ ላይ ቤታችንን ያደረግን በወሲባዊ እና ስርዓተ ፆታችን የተገፋን ሰዎች ለዓመፅ ተጋላጭ ነን። ሙታናችን ይከማቻል፣ የሞታችን ቁጥር ከአቡጃ ወደ ያውንዴ እየጨመረ ነው። ለመደበቅ እምቢ ባልን መጠን የዚያኑ ያህል እንገደላለን።

ከዚህ በፊት እንደነበሩት ፣ ወደፊት ለመግፋት መንገድ መፈለግ አለብን። እያንዳንዱን ሞት ዋጋ እንዲኖረው ማድረግ አለብን። የሺላ ሞት ወደፊት እንድንገፋ ሊገፋፋን ይገባል ። አዎ፣ ሉሲዩስ አናዩስ ሴኔካ ለመጥቀስ፣ “አንዳንዴ መኖር እንኳን የድፍረት ተግባር ነው”።

እኔ ሺላ ሉሙምባ ነኝ፤ ድፍረታቸውንም በውስጤ እሸከማለሁ።

Leave a Reply