የተጋጩ ስሜቶች፡ አፍሪካ እና ኤለን እና ፖርሽያ

ኤለን እና ፖርሽያ በዚምባብዌ አንድ ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ እየተዝናኑ እንደሆነ በማህበራዊ ሚዲያቸው ሼር አደረጉ:: በሰዓቱ ሳየው የተሰማኝ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ነው:: ኩዊር ጥንዶች ሲዝናኑ ማየት ደስ ይላል:: ነገር ግን ቅናት እና ንዴትም አልቀረልኝም::

ኩዊር ሆኖ ከመኖር ልጀምር መሰለኝ.. እንኳን አደባባይ በነፃነት መውጣት ይቅርና ለራስ እንኳን በነፃነት ኩዊርነትን ለመቀበል ጊዜ ዉስዷል:: በቤተ እምነቱም ሆነ በህዝብ መገናኛ ብዙሃን ስለ”ግብረ ሰዶም” ሲለፈፍ ስለቆየ ለራስን መሆን ብዙ ውጣ ውረዶችን ማሳለፍ የብዙዎቻችን እውነታ ይሆናል:: ኤለን እና ፖርሽያ የብዙዎቻችንን ህልም እና ኩዊር ምኞት በነፃነት በአንድ የአፍሪካ ሃገር ውስጥ እየኖሩት ማየት ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ይፈጥራል:

ራስን ተቀብሎ መኖር ሲጀመር ደግሞ የቅርብም የሩቅም ሰው ሃጢያተኛ እና አፀያፊ ተግባር እንደሆነ በተለያየ መንገድ ያስገነዝቡሻል:: ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ራስን ተቀብሎ መኖር ቢቻልም እነዚህ ያለፈቃድችን የሚመጡብን የጥላቻ ውይይቶች ምንም አይመስሉንም ማለት ውሸት ይሆናል፤ አንድ ሃገር እየኖሩ ሃገር የሌለው ስሜትን ሎሎች እናንተ ላይ መፍጠር መቻላቸው ያሳዝናል:: ይህም በአንድ ወቅት የነበርኩበት ራይድ ሾፌር ከመነሻ እስከመዳረሻዬ “የግብረ ሰዶም መስፋፋትን” በጥልቅ ስሜት ሲያወራኝ የነበረኝን ስሜት እና በወቅቱ እንዴት ራሴን መከላከል እንዳልቻልኩ ያስታውሰኛል::  ኤለን እና ፖርሽያ እነዚህ ካለፈቃድ  የሚዘነዘሩ የጥላቻ ውይይቶችን አስተናግደው ይሆን? ኤለን እና ፖርሽያ የብዙዎቻችንን ህልም እና ኩዊር ምኞት በነፃነት በአንድ የአፍሪካ ሃገር ውስጥ እየኖሩት ማየት ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ይፈጥራል::

የፍቅር ግንኙነት ደግሞ ትመሰርታላችሁ… እንደ ኤለን እና ፖርሽያ እጅ ለእጅ ተያይዞ በፍቅር አይን እየተያዩ ፎቶ መነሳቱ ቀርቶ ያለፍርሃት በአደባባይ አንድ ላይ መቀመጥ በተቻለ:: የፍቅር ግንኙነቶቼ ሳልፈልግ የራሴ ፖሊስ አድርገውኛል… ከፍቅር አጋሬ ጋር በአንድ ሬስቶራንት ተቀምጬ ከተማውን እንደሚያስጠብቅ ፖሊስ ግራና ቀኜን አጤናለሁ… እያንዳንዷን እንቅስቃሴዬን እፈትሻለሁ… በጣም ተጠጋግተን ተቀመጥን እንዴ.. በፍቅር አይን ተያየን እንዴ.. ሰዎች ያውቁብን ይሆን እንዴ… የማያልቅ ጥያቄ እና ፍራቻ:: ቤቴ ውስጥ እንኳን ነፃነቴ መቶ በመቶ አይደለም:: በተለያዩ አፍሪካ ሃገራት ኩዊር በመሆናቸው ብቻ የተገደሉ ብዙዎችን አንብቤያለሁ… ሌዝቢያን ወይም ባይሴክሽዋል በመሆናቸው የተደፈሩ ብዙ አፍሪካውያን ታሪክን በተለያየ ዜና እና የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ተመልክቻለሁ:: ቀጣይ እኔ ላለመሆኔ ዋስትናዬ ምንድን ነው? ኤለን እና ፖርሽያ የብዙዎቻችንን ህልም እና ኩዊር ምኞት በነፃነት በአንድ የአፍሪካ ሃገር ውስጥ እየኖሩት ማየት ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ይፈጥራል::

ከፍቅር አጋር ጋር ከከተማ ወጥቶ ለመዝናናት ብዙ ቅድመ ሁኔታዎች ያስፈልጉታል:: የማርፍበት ሆቴል ዘመዳሞች ነን ብንል አንድ አልጋ ክፍል ያከራዩን ይሆን? ለማንኛውም ሴፍ ለመሆን ሁለት አልጋ ክፍል እንከራይ?  እንዳይጠረጥሩን መንታ አልጋ እንያዝ? ጥያቄው አያልቅም:: ለመዝናናት እና አዕምሮን ለማሳለፍ የወጣችሁበት ከተማ   “ተመሳሳይ ፃታ አንድ አልጋ መያዝ አይቻልም” በሚል ማስታወቂያ ደማቅ አቀባበል ያደርጉላችዃል:: አልጋ ከያዛችሁ በኋላ በርና መስኮታችሁን መዝጋታችሁን ሁለቴ ትመረምራላችሁ፤ ሴክስ ስታደርጉ እንኳን ድምፃችሁ ገፍቶ እንዳይወጣ ራሳችሁን ትገድባላችሁ:: ብትችሉ ፍቅረኛችሁ ታፋ ላይ ቁጭ ብላችሁ ቁርስ በበላችሁ.. ወይም የፍቅረኛችሁን ፀጉር እያሻሻችሁ በፍቅር አይን እየተያያችሁ በተመገባችሁ… ይልቅስ ሊዝናኑ ሳይሆን ለስራ እንደመጡ ባልደረቦች የማያስጠረጥር ርቀት ላይ ቁጭ ብላችሁ ድምፃችሁን ዝግ አድጋችሁ ስለምሽታችሁ ትወያያላችሁ:: በአንድ ወቅት ለስራ የሄድከበት ከተማ ሆቴል መከራየቱን ያላወቀች የሆቴሉ የፅዳት ሰራተኛ፥ ክፍሌን በማስተር ቁልፉ ከፍታ ለመግባት የሞከረችበትን  ቀን አልረሳውም:: ከፍቅር አጋሬ ጋር ብሆን ኖርስ የሚለው ጥያቄ ሲያስደነግጠኝ እና ሲረብሸኝ ውሏል:: ኤለን እና ፖርሺያ ይሄ ሁሉ ጉድትዝ ሳልላቸው ሳያስጨንቃቸው… ኤለን እና ፖርሽያ የብዙዎቻችንን ህልም እና ኩዊር ምኞት በነፃነት በአንድ የአፍሪካ ሃገር ውስጥ እየኖሩት ማየት ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ይፈጥራል::

ከሁሉም የሚገርመው ታዲያ ሃገር አስጠባቂው አፍሪካዊ አንዳችም በእነኤለን ፎቶ ስር የጥላቻ ምላሽ አለመስጠቱ ነው… ባላቸው እውቅና እና የኑሮ ሁኔታ የአንድ የማህበራዊ ሚድያ ጥላቻ ያሳስባቸዋል ብዬ ባላንም ጥላቻ ባለመኖሩ ደስተኛ ነኝ:: የእንኳን ደህና መጣችሁ ምላሽ ማየት ባያስደንቅም ያስገርማል:: ካሉበት በተጨማሪ ሌላ ማየት የሚችሉትን ቦታ አስተያየት የሰጡ ብዙ ናቸው… ቀጣይ ጉዞዎችሁን ደግሞ ወደኔ ሃገር አድርጉ ያሉም ብዙ አፍሪካውያን አሉ:: የራሱን ወገን በኩዊርነት ብቻ ለመግደል እና ለመድፈር… ዘግናኝ እና አሰቃቂ ዛቻን ከመሰንዘር ግድ የማይለው አፍሪካዊ ገንዘብ እና ስም ላላቸው ነጭ ጥንዶች እልልታውን ማቅለጡ በምን ስምት ይገለፃል? ኤለን እና ፖርሽያ የብዙዎቻችንን ህልም እና ኩዊር ምኞት በነፃነት በአንድ የአፍሪካ ሃገር ውስጥ እየኖሩት ማየት ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ይፈጥራል::

Leave a Reply