“በጠዋቱ ማሳጅ ፈልጌ ኢንተርኔት ላይ ጥሩ ነው ያሉት ቦታ ሄድኩ:: ከተማዋ ቅውጥ ያለች ናት… መርካቶን አስታውሳኛለች:: ትርምስምስ ያለውን ሰፈር አልፌ ማሳጅ ቤቱ ግር ደረስኩ:: ሽታው እና የቤቱ እርጋታ አትውጪ ያሰኛል::
ለቀኑ የተመደበችልኝ የማሳጅ ባለሙያ ስትመጣ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን ከሩቅ የሚገምተው ውስጤ ወዲያው መረመራት:: ኩዊር ትመስላለች አልኩ ለራሴ:: ከመልበሻ ክፍል ወጥቼ የማሳጅ አልጋው ላይ እንደተቀመጥኩ… የትውውቅ አይነት ወሬ ጀመረች… “እዚህ ስትመጪ የመጀመሪያሽ ነው?” “ምን አይነት ማሳጅ ነው ብዙ ጊዜ የምትወስጂው?”… ከኢትዮጵያ መምጣቴን እና ለማሳጅ ያለኝን ፍቅር እየተጨዋወትን እንደድንገት “ልጆች አሉሽ ወይ እና ባለትዳር ነሽ? ” ወይ ጥያቄ ጠየቀችኝ:: ትዳርም ልጅም እንደሌለኝ መልሼ እሷን መልሼ ጠየኳት:: በፍጥነት “I don’t want” ብላ የመለሰችው መልስ አሳቀኝ:: ምላሿ “ትዳሩን ወይስ ወንዶችን ነው የማትፈልጊው?” ብዬ እንድጠይቃት ድፍረት ሰጠኝ:: ይበልጥ ሳቅን! ሳንነጋገረው በዝምታ ውስጥ ቤተሰብ መሆናችንን ተገላልፀናል::

ከሃገር ወጥቶ የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪያን ጠል በሆነች ሌላ የአፍሪካ ሃገር ላይ እንደኔው ኩዊር ሴት ባልተጠበቀ እጋጣሚ ማግኘት ይገርማል:: ከዛ ቀጥሎ የነበረው ውይይታችን በጣም ጥልቅ እና አበረታች ነበር:: ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የማህበረሰብ አረዳድ.. እሷም ቤትሰቧን ሸሽታ ብቻዋን እንደምትኖር.. የፍቅር ግንኙነት መመስረት እንዴት ከባድ እንደሆነ.. ብቻ በብዙ የሆድ የሆዳችንን አወራን:: እንዴት ኩዊር እንሆንኩ አወቅሽ ተባብለን ስለአለባበሳችንና ንቅሳቶቻችን እያነሳን ተተራረብን:: “አለባበስሽን አይተሽዋል? አንድ ሌዝቢያን አይታሽ ኩዊርነትሽ ይጠፋታል ብዬ አላስብም… ፀጉርሽ ራሱ መልዕክት አለው” ብላ አሾፈችብኝ:: ለነበረኝ ቆይታ እጅግ አመስግኛት ፈቃደኛ ከሆነች መገናኘት እንደምንችል ጠየኳት… ስልክ ተለዋውጠን አጋጣሚውን እያሰላለልኩ ወደሆቴሌ ተመለስኩ::
አይገርምም?! እነዚህን የመሳሰሉ አጋጣሚዎች የእኛን ማንነት እንደወንጀል በሚቆጥሩ ሃገራት ላይ ማግኘት? ሳይነጋገሩ መተዋወቅ? በትንሽ ውይይት ቤተሰብ መሆን? ምንም ሳንባባል ማንነታችንን ተዋውቀን በዛች ስዓት ሚስጥራችንን መጋራት መቻል? ስለአለባበሴ የነገረችኝ አሳቀኝ… አዲስ አበባ ላይ ኩዊር ሴቶች አይተው “ቤተሰብ” ይሉኝ ይሆን? ከቤተሰብ ርቃ ራሷን መርጣ መኖሯ ቢያኮራኝም ያለንበትን ሁኔታ ደግሞ እንዳስብ አደረገኝ.. ከማንነትሽ ወይ ከቤተሰብሽ የሚለው ማህበረሰብ መጣብኝ:: ልጄ ጌ ከሚሆንብኝ ሞቴን እመርጣለሁ የሚለው አስተያየት ትዝ አለኝ::…
ከሮዝ ጋር በነጋታው ከስራ በሗላ ተገናኘን:: ማሳጅ ሰዓት አልበቃ ያለንን ወሬ እስከምሽት አወራን:: የልጅነት ፍቅራችንን እያነሳን ሳቅን፣ ከተማቸው ላይ በኩዊርነታቸው ስለተገደሉ እያወራችኝ አስታወስናቸው:: ደስታ፣ ሃዘን እና ንዴትን እያፈራረቅን ስለብዙ ተጫወትን:: ከሁሉም በላይ ግን ራሳችንን ስለመቀበላችን እና ራሳችንን ሆነን መኖር መቻላችን ትልቅ ድል እንደሆነ ተነጋግረን ተበረታታን::