“በቅርቡ እንደምታገቢ የነገርሽኝ ነገር ብዙ ጥያቄዎችን እንድጠይቅ አድርጎኛል”

ቤዛዬ የመጀመሪያ ፍቅር ወይም ወሲብ አይረሳም ይባላል:: ይበልጥ ለእንደ እኔ አይነቱ ኩዊር ሴት ታሪኬን ስናገር ፣ ኢትዮጵያ ላይ ሆነሽ መጀመሪያ እንዴት አወቅሽ… እንዴት ተዋወቅሻት እና የመሳሰሉትን ስጠየቅ  እንዴት ስምሽን አላነሳ!  ሃያ አመት ሳይሞላን፣ ወሲባዊነት ምኑም ሳይገለጥልን… የራስ ትግልና የአካባቢው ተፅኖ በነፃነት የነበረንን ነገር እንዳናጣጥም ጭራሽ የዘወትር ፀብ ያለበት ፣ ምንነቱ ያልታወቀ ግንኙነት እንዲኖረን ሆነ:: ወይ ልጅነት! የዶርም በር ከቆለፍን ጥርጣሬ እንዳይኖር ብለን በሩን ተደግፈን ልባችን እስኪጠፋ የምንሳሳመው ነገር ትዝ ይልሻል?  የውስጥን ጥያቄ መሸወጃ የተማሪ አቅም የሚችለው ሚንት አረቄ ልፌ ዶርምሽ መጥቼ እየነዘነዝኩ የማስቸግርሽ ትዝ ይልሻል? ስንጣላ ስንታረቅ ስንዘጋጋ ደግሞ መልሰን ስንደዋወል ይኸው ያ ልጅነት አስራ ስንት አመት ሆነው … 

ከኔ ሌላ ሴት ጋር ግንኙነት ኖሮሽ ባያውቅም አብረሽው ስላለሽው ልጅ እርግጠኛ እንዳልሆንሽ ታወሪኝ ነበር… ያ ብቻ አይደለም ብዙ ጊዜ እንዴት ሴቶች ለፍቅር ግንኙነት እንደሚጠይቁሽ ትነግሪኝ ነበር

ብዙ ተጠፋፍተን ስለነበር ሰሞኑን የነበረን የስልክ ወሬ አሁንም ሳስበው ሰውነቴን ይወረኛል… ድንግጥ እላለሁ:: ከኔ ሌላ ሴት ጋር ግንኙነት ኖሮሽ ባያውቅም አብረሽው ስላለሽው ልጅ እርግጠኛ እንዳልሆንሽ ታወሪኝ ነበር… ያ ብቻ አይደለም ብዙ ጊዜ እንዴት ሴቶች ለፍቅር ግንኙነት እንደሚጠይቁሽ ትነግሪኝ ነበር… ምንም እንኳን ኩዊር / ሌዝቢያን ነኝ ብለሽ ባታስቢም ወይም ባትነግሪኝም… በዚህ ዙሪያ ስጠይቅሽ ፈቃደኛ ካለመሆን በተጨማሪ ደባብሰሽ ማለፍሽ ብዙ ይለኛል፤ እኔም ምንም ልረዳሽ ባለመቻሌ ያሳዝነኛል:: በእምነት እና ወሲባዊነት ላይ የተፃፈውን የንስንስን አንደኛ እትም አንብበሽ “በጣም relate አደረኩኝ” ያልሽኝ ትዝ ይልሻል? የሁላችንም እርምጃ የተለያየ ስለሆነ ደግሞ ገፍቼ አልጠየኩሽም:: ነገር ግን በቅርቡ እንደምታገቢ የነገርሽኝ ነገር ብዙ ጥያቄዎችን እንድጠይቅ አድርጎኛል… ቤዛዬ እርግዝናሽም ትዳርሽም በፈቃድሽ ነው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ:: ስልኩ ላይ እንኳን የማቅማማት ነገር ተሰምቶኛል ግን ምን ማለት እችላለሁ? እርምጃሽን ምንም ማድረግ አልችልም:: ብቻ ራስሽን ከመሆን የከለከለሽ አውቅልሻለሁ የሚለው ማህበረሰብ ከሆነ ያሳዝናል፤ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? አላውቅም:: ይበልጥ ጥያቄ የሚሆንብኝ… ከተለያየን ከብዙ አመት በኅላ የፍቅር ግንኙነት እንዲኖረን ጥያቄ ጠይቀሽኝ በወቅቱ ፈቃደኛ አልነበርኩም… ከዛም ግን ለሌላ ሴት ፍላጎት እንደሌለሽ ደግሞ ጨመርሽልኝ… ይሄ ድንግርግር ያለ ህይወት…ፍራቻሽንም እረዳዋለሁ::

የፍቅር ግንኙነት ኖሮን ስለነበረው ነገር ምንም ሳናወራ፣ ምንነታችንን ሳንነጋገር… ወንድ ልጅ ጋር ግንኙነት ለመጀመር ግድ ያልሰጣቸው የድሮ የፍቅር አጋሮቼ… ወንድ አግብተው ወልድዋል:: “ምን እየተሰማቸው ይሆን?” እላለሁ በፊልም እና በሙዚቃው የኩዊር ሰዎችን ህይወት ሲያዩ ትዝ ይላቸው ይሆን? ወይስ የእለት ተለት ትግል ነው? ከኔ ጋር በተለያየ አጋጣሚ ስንገናኝ የነበረንን ነገር ያስቡት ይሆን? ካልሆነ ነፃነትን በሚነፍግ ሃገር ላይ የማሰብ እና የማሰላሰልን ነፃነት ባገኙ! ምናልባት የኔ ብቻ ምኞት ይሆናል::…

ምን እንደምልሽ አላውቅም:: እርምጃሽና መንገድሽ ብርሃንን እንዲያስጨብጥሽ፣ የውስጥሽን እውነት እና ሚስጥር ከራስሽ ጋር መወያየት እንድትችይ እመኝልሻለሁ:: ከምንም በላይ ዋጋ ቢያስከፍልም ራስሽን መሆን እንድትችይ እመኝልሻለሁ:: ሁላችንም ነፃነት ይገባናል:: እወድሻለሁ! ደግሞም ከጎንሽ ነኝ… ምን ያህል አመት ቢፈጅ ፈቅደሽ ማውራት ላይ ስትደርሺ ከጎንሽ እንደሆንኩ እንዳትረሺ! 

Leave a Reply