ከኩዊር ሴቶች ጋር አዲስን አመት ስንቀበል

የዚኛውን አመት በአል ልዩ ያደረገው አዲሱን አመት ከልዩ ቤተሰቦቼ ጋር በመቀበሌ ነው፤ ከኩዊር ቤተሰቦቼ ጋር ደግሞም ከኩዊር ሴቶች ጋር:: ልዩ ያደረገው ከኩዊር ሴቶች ጋር ማሳለፌ ብቻ ሳይሆን በጣም ደስ የሚል ጊዜና ለየት ያለ ስሜት ነበረው:: እኛን ከሆን ሰው፣ የእኛን አመለካከት ከሚጋራ ሰው ጋር ልዩ ቀንን አብሮ ማሳለፍ የሁልጊዜ ገጠመኝ አይደለም:: ልዩ የሚያደርገው በመጀመሪያ የምርጫ ቤተሰብ ትሆኛለሽ እናም ልዩ ቀናቸውን ካንቺ ጋር በማሳለፋቸው ደስተኞች ናቸው:: 

አመት በዓል ለሁሉም ሰው ልዩ ቀን ነው ነገር ግን ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ይበልጥ ትልቅ ነገር ነው:: ከምንወደው ሰው ጋር የምናሳልፈው ጊዜ ቢሆንም ለኔ ግን ወደአዕምሮዬ የሚመጣው የሚሰራው ስራ ብዛት ነው:: ሁሉ ነገር ስክትክት ያለ እና ፍፁም መሆን አለበት። ለእኛ ለሴቶች፥ ባል የማግኘት አቅማችንን የምናሳይበት እና የምናረጋግጥበት ጊዜ ነው:: እናቴ በደንብ ካልሰራው ባል እንደማላገኝ ትነግረኝ ነበር:: የሚገርመው ደግሞ ያ ነበር እቅዴ:: ለዛም ይመስለኛል እስካሁን ዶሮ ወጥ መስራት የማልችለው:: አንድ ነገር አለመስራት መቻል የሚያኮራ ነገር እንዳልሆነ አውቃለሁ ግን በቃ ማንነቴ በቤት ውስጥ ስራ መስርት ላይ እንደማይወሰን ለእናቴ ማረጋገጥ ፈልጌ ነበር ነገር:: ይሄ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሴት ገጠመኝ ይመስለኛል:: ለብዙ ሴቶች፥ ጓደኛዬም እንደነገረችኝ ቀኑን በመተኛት እና ምንም ልዮ ቀን እንዳልሆነ እየተሰማቸው የሚያሳልፉት ቀን ነው:: 

ከኩዊር ሴቶች ጋር ስለነበረኝ ጊዜ እና ስሜት አውርቼ አልጨርስም:: ሁሉም ሲደሰቱ፣ አንዳንዶቹ ከፍቅር አጋሮቻቸው ጋር ሌሎች ደግሞ ከቅርብ ጓደኞቻቸው ጋር ማየት በጣም ደስ ይል ነበር። ምንም እንኳን እንደዚህ አይነት ጊዜ ሳሳልፍ የመጀመሪዬ ቢሆንም ለኔ የቤትነት ስሜት ነበረው:: ሁሉም ሰው ሲዝናና አይቻለሁ እና የእኔን እርካታ ነው የተጋሩት:: 

እንደእኔ በበዓል ዋዜማ ስራ ለሚሰራሰው ምግብና መጠጥ ቀድሞ መዘጋጀቱ ደስ ብሎኛል:: በዓል ቀን የምትተኛበት እና ምንም ሳይመስላት ለምታሳልፈው ጓደኛዬ ምቹ ቦታ መሆኑም በጣም ደስ ይል ነበር:: ለእኛ እጅግ አስደሳች እና የማይታመን ጊዜ ነበር:: ኩዊር ቤተሰቦቼ ሲዝናኑ እና በነፃነት ከመረጡት ጋር ሲደንሱ ማየት አስደሳች ነበር:: ከመደሰት በላይ ነበር በቃ ስሜቱ እናም ቀኑ ልዩ ስሜትን ፈጥሮልኛል:: ለኔ በዐሉ ፍፁም እንዲሆን ወጥ መስራት እና ብዙ ስራ መስራት አልተጠበቀብኝም፤ ጊዜውን ከመረጥኳቸው የኩዊር ቤተሰቦቼ ጋር እየተዝናናሁ አሳልፌያለሁ:: 

ግን አንድ ምኞት አልተሟላም:: ለጨዋታው ሲባል እኩለ ለሊት ላይ የመሳሳም ጊዜ መኖር አለበት:: ያንን ስላላደረግን ይቺ ኩዊር ትንሽ ከፍቷታል:: ምናልባት ለሚቀጥለው አዲስ አመት አንድ ሰው እስማለሁ:: ኧረ ግን ዳንሱ እና መተቃቀፉ በደንብ ተክቶታል:: ከዛ ውጪ እጅግ ድንቅ ጊዜ ነበር፤ አዲሱን አመት ከኩዊር ቤተሰቦቼ ጋር ማሳለፍ በመቻሌ በጣም ተደስቻለሁ::

Leave a Reply