የአዕምሮ ጤንነታችንን መንከባከብ

በየአመቱ በመስከረም 30 የሚውለውን የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀንን ስናከብር ይህ ቀን ለLGBTQ+ ኢትዮጵያውያን ያለውን ፋይዳ በውል ማጤን አስፈላጊ ነው።

ቢቢሲ ከሰሞኑ እንደዘገበው የአለም ጤና ድርጅት አፍሪካ በአለም ላይ ራስን በማጥፋት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው ብሏል። በተጨማሪም አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ራስን የማጥፋት መጠን ካላቸው 10 አገሮች ውስጥ ስድስቱ መገኛ መሆኗን ዘግቧል።

በኢትዮጵያ የአዕምሮ ጤና ችግር የሚያጋጥማቸውን ሰዎች ለመርዳት በቂ የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎች ባለመኖራቸው ችግሩ የበለጠ ተባብሷል። በተለይ በLGBTQ+ ማህበረሰብ ሊደርስብን የሚችለውን መገለል፣ መድሎ እና አካላዊ ጥቃት በመፍራት የሚያጋጥሙንን የአዕምሮ ጤና ችግሮች ማካፈል አልቻልንም።

ስማቸው እንዳይገለጽ በሚመርጡ ሁለት ኩዊር ድርጅቶች የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ከተሳተፉት LGBTQ+ ኢትዮጵያውያን 41 በመቶ የድብርት ምልክቶች ታይቶባቸዋል። ጥናቱ በመቀጠልም “ይህ አሃዝ የአለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው ግምት 5 በመቶ እና የብሄራዊ የጤና ዳሰሳ ጥናት ደግሞ ካስቀመጠው ግምት 9 በመቶ ሲወዳደር በጣም ከፍተኛ ነው” ብሏል። “ይህ የሚያሳየው LGBTQ+ ኢትዮጵያውያን እንደሌሎች ተጋላጭ ቡድኖች በተለይ ለድብርት የተጋለጡ ስለሆኑ የአዕምሮ ጤና አጠባበቅ ያስፈልጋቸዋል።” ጥናቱ እንደሚያሳየው ከሁሉም LGBTQ+ መካከል በጣም ተጋላጭ የሆነው ግሩፕ ባይሴክሹዋል ሴቶች ሲሆኑ በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት የድብርት ምልክቶች የሚታዩባቸው ናቸው።

የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎችን ማግኘት ግዴታ እና አስፈላጊ ቢሆንም በመላው ኢትዮጵያ እና በተቋሞቻችን ላይ ካለው ሆሞፎቢያ፣ ባይፎቢያ እና ትራንስፎቢያ አንፃር ብዙ ጊዜ አይገኝም እና አደገኛም ሊሆን ይችላል።

እነዚህን ገደቦች ከግምት ውስጥ በማስገባት የአዕምሮ ደህንነታችንን ለመንከባከብ ምን ማድረግ እንችላለን? ከዚህ በታች ጥቂት ሃሳቦች ይገኛሉ።

1. በመሠረታዊ ነገሮች ላይ እናተኩር
በአዕምሯዊ ጤንነታችን ላይ መጥፎ አጋጣሚዎች ከመግጠማቸው በፊት አዕምሯዊ ጤንነትን ለመጠበቅ መሰረታዊ የሚባሉትን ነገሮች  ሁልጊዜ  በማድረግ እራሳችንን መንከባከብ አለብን። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ጤናማ አመጋገብ፣ ሜድቴት ማድረግ እና ጥሩ እንቅልፍ መተኛት የአዕምሯዊ ደህንነታችንን ለመጠበቅ የዘወትር ውሎአችን አካል መሆን አለበት።

2. ቀስቅሴዎችን መለየት
ከቤተሰብ፣ ከጓደኞች፣ ከፍቅር ጓደኞች ፣ ከትምህርት ቤት፣ ከስራ ወይም ከሌሎች ነገሮች ሊመነጩ የሚችሉ የአዕምሮ ጤንነታችንን ሊያጓድሉ የሚችሉትን ነገሮች ለይቶ ማወቅ አስፈላጊ ነው። የሚያስጨንቁንን ነገሮች ማወቃችን ጉዳዩ ልንርቀው የምንችልበትን ወይም የምንቀጥልበትን መንገድ ለመፈለግ ይረዳናል።

3. የፈጠራ ስራዎችን መሞከር
ማድረግ የምንወደውን ወይም መማር ስለምንፈልገው ነገር እናስብ – እንደ ስዕል፣ ሙዚቃ፣ ዳንስ፣ ምግብ ማብሰል ወይም መጻፍ የመሳሰሉትን እንሞክር፤ እንዲሁም በምንችለው ያህል የራሳችን ለማድረግ የፈጠራ ችሎታችንን እንጠቀም። እነዚህ እንቅስቃሴዎች የአዕምሮ ጤንነታችንን ለመጠበቅ እና መጥፎ ቀናት ሲያጋጥሙን እንደ ማዘናጊያ በመሆን ያገለግላሉ።

4. ድጋፍ ሊሆኑን የሚችሉ ሰዎችን መፈለግ
ከሌሎች ተመሳሳይ ፈተናዎች ውስጥ ካሉ ወይም ለችግሮቻችን ቦታ መፍጠር ከሚችሉ ሰዎች ጋር መነጋገር ብስጭታችንን ሊያበርድ እና ምቾት ሊሰጠን ይችላል። ስለዚህም ሌሎች LGBTQ+ ሰዎችን ወይም ማንነታችንን የሚቀበሉ አጋሮችን መፈለግ ጠቃሚ ነው።

5. የ LGBTQ+ ማህበረሰብን የሚደግፉ ድርጅቶችን ያግኙ
ወደ ኩዊር ኢትዮጵያ (etqueerfamily@gmail.com) ብትጽፉልን ካሉት የጤና ባለሙያዎች እና ሌሎች ሊያግዙ ከሚችሉ ሰዎች ጋር ልናገናኛችሁ እንሞክራለን።

1 thought on “የአዕምሮ ጤንነታችንን መንከባከብ”

Leave a Reply