የትራንስ፣ ነን ባይነሪ እና በየትኛውም ስርዓተ ፃታ ማንነት የማይገለፁ ሰዎችን ታሪኮች ወደመሃል ማምጣት

የትራንስ ስርዓተ ፃታን ግንዛቤ ማስጨበጫ እና ማስታወሻ ሳምንት እንደመገባደዱ የትራንስ፣ ነን ባይነሪ እና በየትኛውም ስርዓተ ፃታ ማንነት የማይገለፁ ሰዎችን ወደመሃል ማምጣት እና የውይይቶች አካል ማድረግን መቀጠል መዘንጋት የለብንም:: የኢትዮጵያውያን ትራንስ፣ ነን ባይነሪ እና በየትኛውም ስርዓተ ፃታ ማንነት የማይገለፁ ሰዎችን ታሪኮች ማጋራት ይኖርብናል:: ከLGBTQ+ ማህበረሰብ እና ከሰፊው ማህበረሰብ የሚመጣን ማግለል እና አካታች ያለመሆንን ችግር አጥብቀን መቃወም ይኖርብናል::

በቅርብ የሚለቀቀው አዲሱ የንስንስ መፅሄት “ሰውነታችን” እትም የተለያዩ ስርዓተ ፃታ እና ማንነት ያላቸውን እና ባህላዊ የስርዓተ ፃታ አረዳድን የማይወክሉ ሰዎች ታሪኮች ታካትታለች:: ቃለ መጠይቅ ካደረግንላቸው ሰዎች መሃል ቆንጅዬዋ እና ደፋር ልብ ያላት ቦኒ የትራንስ ጠል ማህበረሰብ ውስጥ ያላትን የእለት ተእለት ህይወት አካፍላናለች::


ይህ ከታች የጠቀስነው ከቃለምልልሳችን የተቀነጨበ ነው

“የወስነት አካሌ ወንድ ነኝ ግን የበለጠ  ፀባዬ የሚያደላው ወደሴት ነው ወንዶች የሚያደርጉትን ነገር እጠላ ነበር። …  በተለይ ሃይስኩል እና ኤለመንተሪ ላይ ያጋጠሙኝ ጥቃት እና ጥላቻ በጣም ከባድ ነበሩ። እጨነቅ ነበር፤ ትምህርት ቤት መሄድ እስከሚደብረኝ ድረስ “ሴቱ ሴቱ” እየተባልኩ ነው እጠራ የነበረው ያው አነጋገሬም አወራሬም ወደሴት አደላ ነበር። በጣም ይጨንቀኝ ነበር፥ በጣም ይከፋኝ ነበር፥ የማለቅስበት ግዜ ሁሉ ነበረ።”

“መቶ ፐርሰንት ባይሳካም መንገድ ላይ የተለየ አለባበሶችን ላለመልበስ እሞክራለሁ፤ እርግጥ ምቾት ላይሰጠኝ ይችላል ግን የምንኖረው ያልሰለጠነ ማህበረሰብ ውስጥ እደመሆኑ መጠን፤ ለየት ያሉ ነገሮችን ስለማይቀበሉ ራሴን መገድብ የግድ ነው።”

“በዚህ ሃገር በሃይማኖቱም በባህሉም ይሄንን ነገር መቀበል የቻለ ሰው፤ ራሱን እኔ እንደዚህ ነኝ እና ፈጣሪን ደሞ አመሰግነዋለሁ እንደዚህ አድርጎ ስለፈጠረኝ ብሎ ከፈጣሪ ጋ ያለውንም ጸብ ግብግብ መፍታት ከቻለ ይሄ የሰውነትን ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴዎች እንደ አሳሳቅ የምንላቸው የፆታ አገላለፅን የሚያጠቃልሉ ነገሮችን ለመቀበል ፈታኝ አይሆንም።”

Leave a Reply