እንደ ኩዊር ኢትዮጵያዊ የዓለም ዋንጫን መመልከት 

ሁሌም የዓለም ዋንጫን በቅርበት የምከታተል የእግር ኳስ ደጋፊ ነኝ። ማህበራዊ እና አንዳንድ ጊዜም ከስራ ጋር የተገናኙ ግዴታዎቼን በመተው ብዙ ጊዜ ከቴለቪዥኑ ጋር ተጣብቄ የተቻለኝን ያህል ጨዋታዎችን እመለከታለሁ። ቡድኖቼን ከአንድ እስከ አምስት ደረጃ ሰጣቸው እና እያንዳንዳቸው ወደቀጣዩ ደረጃ ሲያልፉ ወይም ሲወድቁ እከታተላለሁ። ምንም ሌላ ቡድኖችን ብደግፍም ለኔ የተሳካላቸው አፍሪካዊ ቡድኖች የመጀመሪያ ምርጫዎቼ ናቸው። ለምሳሌ ሉዊስ ሱዋሬዝ የሚባለውን ስም ስሰማ እ.ኤ.አ. በ2010 ጋና ወደ ሩብ ፍፃሜ እንዳታልፍ በእጁ የመለሰው ኳስ ትዝ ይለኝና ያንገፈግፈኛል።

የዓለም ዋንጫ ትኩረት ሰጥቼ በየአራት ዓመቱ በጉጉት የምጠብቀው ነገር ነው። የአፍሪካ ቡድን ወደ ሩብ ፍፃሜው በማለፍ ያሳየው ታሪካዊ ግስጋሴ የዘንድሮውን ጨዋታ ልዩ አድርጎታል። የሞሮኮን ጨዋታ ከአንድ ወጣት የቤተሰብ አባል ጋር ነበር የተመለከትኩት እናም እነሱ በልባቸው፣ በኩራት እና በትጋት ሲጫወቱ እያየን በደስታ አብረውን ዘለልን። በካዛብላንካ እና በማራኬሽ የነበረው ደስታ አዲስ አበባ ውስጥ እንዳለ ሆኖ ተሰማኝ። ሁላችንም አፍሪካውያን እንድንኮራ አደረጉን ምክንያቱም እኔ ስኬታቸው የሁላችንም አፍሪካውያን እንደሆነ አድርጌ ስለምመለከተው ነው።

ዘንድሮ ግን ካለፉት አመታት በተለየ በዓለም ዋንጫው እራሴን ማጣት አልቻልኩም። ጨዋታዎችን ስመለከት እንኳን የጥፋተኝነት እና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተሸክሜያለሁ። እንደ ኢትዮጵያዊ ኩዊር ሴት በኳታር ዉስጥ የተዘጋጀውን የዓለም ዋንጫን መመልከቱ በመንግስት የተደገፈን ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ እና ትራንስ ጠልነት የማያቋርጥ ማስታወሻ ነው። ኳታር ከኩዊርነት ጋር ለተያያዙ ሁሉም ነገሮች ያላትን ጥላቻ በግልፅ ከመግለፅ ወደኋላ አላለችም። በኳታር ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት ሕገወጥ ስለሆነ እናም በእስራት ወይም በሞት ቅጣት ስለሚቀጣ ይህ በራሱ የሚጠበቅ ነው። ትራንስ ሴቶች “ሴትን በመምሰል” ወንጀል ሊታሰሩ ይችላሉ እናም በግዴታ ተመልሰው እንዲቀየሩ ሊገደዱ ይችላሉ። ይህም ጡቶችን ለማስቆረጥ የግዳጅ ቀዶ ጥገና እና የልወጣ ሕክምና (conversion therapy) ወደ ሚደረግበት “የባህርይ ጤና ጣቢያዎች” መላክን ሊያካትት ይችላል። ህጉ “የሴቶች ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት” የሚለውን ነገር በቀላሉ ማግኘት አለመቻላቸው በሀገሪቱ ያለውን የፆታ አድሏዊነት አመላካች ነው።

ከእነዚህ እውነታዎች አንጻር ኳታር በአንድ ጀምበር የኩዊርነት ወዳጅ ትሆናለች ብዬ አልጠበኩም። ነገር ግን የምዕራባውያን አገሮች እና ተቋማት ከኳታር ጋር ተቃርነው ይቆማሉ ብዬ ጠብቄ ነበር። የኳታርን ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ እና ትራንስ ጠልነት ለማስተናገድ ጠብ እርግፍ ሲሉ ማየት እንግዳ ነገር ነው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የአንዳንድ የአውሮፓ ቡድን አምበሎች ድጋፋቸውን ለማሳየት ሊለብሱት የፈለጉትን የኤልጂቢቲኪው (LGBTQ) ቀስተ ደመና OneLove (አንድ ፍቅር) የእጅ ላይ የሚታሰር አርማ ፊፋ ማገዱ ነው። ፊፋ አርማውን እጁ ላይ ላሰረ ማንኛውም ተጫዋች ቢጫ ካርድ እንደሚሰጥ አስታውቋል። ብስጭቱንም ያባባሰው ጉዳይ ደግሞ የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ሁላችንም ትኩረታችንን እግርኳስ ሜዳው ላይ ብቻ እንድናደርገው መምከሩ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ተራ ነገር የሆነ እንዲመስል ማድረጉ ነው። ከፊፋ እና ከዓለም ብዙ ጠብቄ ነበር።

በኳታር ላይ ያለው የኩዉር ሰዎች አያያዝ፣ የስደተኛ ሰራተኞች በደል እና የአለም ዋንጫ ለኳታር የተሰጠበት ሂደት በዚኛው የዓለም ዋንጫ መደሰትን አስቸጋሪ አድርጎታል።

የሞሮኮን ድል ለማክበር ፈልጌ ነበር። ለአፍሪካ ድል ነው። ሆኖም ግን በሜዳው ላይ ብቻ ማተኮር አልቻልኩም። እናም በዚህ ምክንያት የዓለም ዋንጫ ለእኔ ያለው ትርጉም በዚህ አመት ትንሽ ቀንሷል።

Leave a Reply