ደጋፊዎቻችን: “ራሳችንን ካላስተማርን በስተቀር መቀየር አንችልም”

“ጥላቻ ከፍርሃት እና ካለመረዳት የመጣ ነው” ትላለች ሳቤላ የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪያን ላይ ስላለው የማህበረሰባችን እይታ ስታብራራ:: 

እውነት ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው? አብዛኛውን ጊዜ አዕምሮዋችን ልክ እና የተለመዱ ተብለው የተቀመጡ ነገሮችን ብቻ ማሰብ እንጂ አዲስ ነገርን (እዚህ ጋር ተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪነት አዲስ ነገር ሳይሆን ከጥንት የነበረ መሆኑ እንዳይዘነጋ) ለማስተናገድ ክፍት አይደለም:: ምክንይቱ ደግሞ አዲስ ነገርን ማብላላት የነበረንን መረዳት መለወጥ ማለት ስለሆነ፤ ለውጥ ደግሞ የሆነ ያህል መረታትን ስለሚፈልግ ነው::  ለዚህም አብዛኛው ማህበረሰባችን የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪያንን ማንነት ለመቀበል በፍፁም አይፈልግም:: ለመቀበል ቀርቶ ያለውን እውነታ እንኳን በግልፅ ለመወያየት ጊዜ መስጠት አይፈልግም:: ለነገሩ አስተሳሰብን ከመፈተሽ አጥብቀን በያዝነው የተሳሳተ መረዳት ላይ መቀመጥ ቀላሉ መንገድ አይደል?! 

ታዲያ እንዲህ ስር በሰደደው ጥላቻ ውስጥ አንዳንድ የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪያን መብት ደጋፊዎች እንዴት ሊኖሩ ቻሉ? የዛሬ እንግዶቻችን ከልጅነት ጀምሮ እንደማንኛውም ማህበረሰብ ጥላቻ የነበራቸው መሆኑን ገልፀው፤ አንደኛዋ እንግዳችን  [ራሳችንን ካላስተማርን በስተቀር መቀየር አንችልም] ብለዋል:: ራስን ማስተማርስ ምን ይመስላል? እንግዳችን በአጭሩ “google and educate yourself” ትለናለች:: 

እንደአንድ ራሷን እንደተቀበለች የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ ይሄንን ውይይት መስማት ብዙ የተደበላለቀ ስሜትን ፈጥሮብኛል:: የህዝብ ጥልቅ ጥላቻ በውይይት ውስጥ መስማት ራሴን ሳልቀበል ያሳለፍኩትን የራስ ትግል እና ፍርሃት እንዳስታውስ አድርጎኛል:: የሚጠበቅብንን ትግል ደግሞ ቁልጭ አድርጎ አሳይቶኛል::  በሌላ በኩል ድግሞ ደጋፊዎችን ማግኘት እጅግ የሚያስደስት እና ምናልባት ተስፋን የሚጭርም ነው:: ምናልባት የምለው የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪን የተቀበለች ኢትዮጵያን ማሰብ የዘወትር ተስፋዬ ስላልሆነ ነው:: ምንም ይሁን ምን ግን ትግሉ ያለደጋፊያን እውን እንደማይሆን በማሰብ ብዙ ደጋፊዎች እንዲኖሩን እየተመኘው ይህንን ምርጥ ውይይት ልጋብዛችሁ:: 

ሚድያ ላይ ባትመጡም በየቤታችሁ ሆናችሁ በተለያየ መንገድ ድጋፋችሁን ለምታሳዩን ሁሉ እጅግ እናመሰግናለን::

ማንበብ ፣ መጠየቅ ፣ መፈተሽ ሙሉ ያደርጋል::

Leave a Reply