ለማህበራዊ ሚዲያ ግንኙነትዎ ጠቃሚ ጥቆማዎች

የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ ሌዝቢያን ነኝ። እንደአብኞቻችሁ  ኩዊር ሰዎች ጋር የምገናኝበት የፌስቡክ አካውንት አለኝ:: በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ ሰዎች ግር የሚሉ መልዕክቶች ይመጡልኛል። እድሜዬ ሰላሳዎቹ ውስጥ ነው፥ የመጀመሪያ የሴት ፍቅረኛ ስይዝ 18/19 አመቴ ገደማ ነው… ይህን መንገር የፈለኩት… ለኩዊር ማህበረሰብ፣ ባህል እና ዴቲንግን አዲስ አለመሆኔን ለማስረዳት ነው።

ብዙ ጊዜ የሚመጡት መልዕክቶች የሴት ስም የያዙ ቢሆንም… አፃፃፉ፣ የሌዝቢያንን አነጋገር ዘይቤ የማያውቅ ወንድ ልጅ መሆኑን ለማወቅ ጊዜ አይወስድም። ለመልዕክቱ ምላሽ ሳልሰጥ አንድ ሁለት ቀን ከቆየሁ የወንድ የመራቢያ አካል ፎቶ ተልኮ አገኘዋለሁ። 

ሌላኛው አይነት ደግሞ መተማመንን ለመፍጠር ለማህበረሰቡ አዲስ እንደሆኑ እና ገና በእድሜም ልጅ እንደሆኑ ይግልፁና የማህበረሰቡን አባል በምን መልኩ ማግኘት እንደሚችሉ ይጠይቃሉ። ይሄኛው ታክቲክ ደግሞ የእናንተን ማንነት ብቻ ሳይሆን የኩዊር ማህበረሰቡን ማንነት ለአደጋ ሊያጋልጥ የሚችል አጋጣሚ ነው።

ታዲያ ይሄንን ነገር ለማውቅ ቀላል ቢመስልም… እነዚህ ሰዎች ይሄ ነገር እየተሳካላቸው ቢሆንስ ብዬ ሳስብ ኩዊርነታቸውን ገና ያወቁ፣ ማህበራዊ ሚድያው ላይ በቅርቡ የሚመጡ ሰዎች ያሳዝኑኛል። ለእንደዚህ አይነቱ ገጠመኝ 1 2 3 የሚል መፍሄ ባይኖረኝም… መልዕክት የላኩልን ሰዎች እነማን ናቸው? የጋራ ጓደኞቻችን እነማን ናቸው? በኮሜንት እና ታግ ከነማን ጋር ነው የሚተዋወቁት? እና የመሳሰሉትን መጠየቅ ይረዳል።

ለመልዕክቶች ሁሉ ምላሽ መስጠት አይጠበቅብንም።

የብዙዎችን ማንነት ደግሞ ገፆቻቸው ላይ ከሚኖራቸው እንቅስቃሴዎች በጥቂቱም ቢሆን ማወቅ ይቻላል።

እስቲ እናንተም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስለምትወስዷቸው ጥንቃቄዎች አካፍሉኝ።

Leave a Reply