በቅርቡ «The Lavender Scare» ን አየሁት ፣ ማመን የሚያቅት ስሜት ነበር ማለት እችላለሁ::
« The Lavender Scare » “በፌደራል መንግስት በኩል በተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪነት የተጠረጠሩ ሰራተኞችን በሙሉ ለመለየት እና ለማባረር የሚያደርገን ዘመቻ” የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ነው። በUS ፌደራል መንግስት ውስጥ እንዳያገለግሉ በተላለፈው አስፈፃሚ ትዕዛዝ ከ5000 እስከ 10,000 የሚደርሱ LGBTQ+ ሰዎች ስራቸውን እንዳጡ ይገመታል።
«Lavender Scare» ከ70 ዓመታት በፊት በአሜሪካ ውስጥ የነበሩ የኩዊር ሰዎችን ልምድ ያሳያል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ስራቸውን ያጡበት፣ ብዙዎች በቤተሰቦቻቸው አማካኝነት ማንነታቸው የተጋለጠባቸው ፣ ብዙዎች ከቤታቸው የተባረሩበት እና ብዙዎች እራሳቸውን ያጠፉበት ወቅት ነበር። ወንጀላቸው፡ በአሜሪካ ውስጥ የLGBTQ+ ሰው መሆን!
ፊልሙ እ.ኤ.አ. በ1950ዎቹ በአሜሪካ ውስጥ የኩዊር ሰዎችን መባረር እና ማንነታቸው መጋለጥ ላይ የሚተርክ ቢሆንም፣ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ላይ ያለኝን ልምድ እንዴት እንደሚያንጸባርቅ ማየት የሚገርም ነው። ምንም እንኳን ፊልሙን ከቀስተደመና ባንዲራ ካሸበረቀ እቃ ውስጥ ፋንዲሻ እየበላሁኝ ባይም፣ ፊልሙን ካየሁበት ቦታ ባሻገር ፣ ኩዊርነቴ ቢጋልጥ የሚሆነው ነገር በፊልሙ ላይ ከሚታየው እጅግ የከፋ ነገር ነው።
በፊልሙ ውስጥ ከተካተቱት አንዳንድ ይዘቶች ውስጥ የመንግስት ሰራተኞች እና የተመረጡ ፖለቲከኞች የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪያን ላይ ያላቸው የጥላቻ አመለካከቶች ይገኙበታል። ኩዊት ሰዎች የ « ኤፍቢአይ » እና ሌሎች የህግ አስከባሪዎች እንዴት እንደሚመጡባቸው ኩዊር እንደሆኑ “እስኪያምኑ” ድረስ እንደሚያፋጥጧቸው የገለፁበት መንገድ እኔም በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረኝ ገጠመኝ ነው። ፊልሙን እያየሁ ከፖሊስ ጋር የነበረኝን አስፈሪ እና አሸባሪ ገጠመኝ ድጋሚ ኖርኩት፤ ፖሊሱ ስልኬን እየጎረጎረ የግል ጥያቄዎችን የጠየቀኝ ነገር ሁሉ መጣብኝ:: የLGBTQ+ ማህረሰብ የሚያልፉትን ስቃይ እና ሽብር እያሰብኩ የዝምታ እንባዬን አነባሁ:: እንባዎቼ ለኔም ነበሩ መሰለኝ::
በፊልሙ ላይ ተንጸባርቆ ያየሁትን ድፍረት መቼ እንደማሳድግ ወይም እንደሚኖረኝ ሳስብ ነበር። በጣም ደፋር ከሆኑት ድርጊቶች ውስጥ አንዱ ፍራንክ ካሜኒ በማደራጀት እና « White House » ፊት ለፊት በተቃውሞ ሰልፍ ለጌ እና ሌዝቢያን መብት የሚጠቁሙ ምልክቶችን ይዘው ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ እና ሲታገሉ ማየት ነው። አንዱ ጌ ሰውዬ ከተባረረ በኋላ ወደነበረበት ለመመለስ መብቱን ለማስከበር የታገለበትን መንገድ አደነቅኩኝ።
ባለፈው እና በአሁን ጊዜ መካከል ተጣብቄ ተመሰጥኩ። ፍራንክ ካሜኒ ከስራው ሲባረር የታገለውን እና በLavender Scare ጊዜ የተጫወተውን ወሳኝ ሚና እንዴት እንደተፅጫወተ በስሜት እና በቀልድ ሲናገር ልቤ በደስታ ተሞላ። አሜሪካ ብዙ ርቀት ተጉዛለች። አሜሪካ ምናልባት ከ70 ዓመታት በፊት የነበረችበት ቦታ ላይ ነን። እናም የኩዊር እንቅስቃሴው ምን ያህል እንደደረሰ መመልከቴ ተስፋ ሰጠኝ። ትንሽ ተስፋ አስቆርጥም አድርጎኛል።
ፍራንክ ካሜኒ የፌደራል መንግስትን በድፍረት ሲሞግት የፍቅር አጋሬ እያሾፈችብኝ ነበር። “ምንም ሀሳብ እንዳትወስጂ” እያለች ደጋግማ ስታሾፍብኝ ነበር። እንደዛ ደፋር እሆናለሁ ወይ ብዬ አሰብኩ። ምን አይነት ኢትዮጵያ ነው የልጅ ልጆቻችንን የምንተወው ብዬ አሰብኩ። እንደ LGBTQ+ ማህበረሰብ መንግስት እኛን እንደ ሰው እንዲቆጥረን የሚፈታተን ማንኛውንም ነገር ለማድረግ በጣም እንፈራለን። መስዋእትነት ለመክፈል ፈርተናል፤ የሚገባም ነው። እና እኛ ካላደረግን ምንም አይለወጥም።
እኔ እንዳየሁት ኢትዮጵያ ውስጥ የልጅ ልጆቻችን ከ70 ዓመት በኀላ Lavender Scareን በድብቅ ይሆን የሚያዩት? የት ይሆን የምንሆነው? ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል::