ክፍል ሁለት: “የሆነ ቀን ፍራሽ ላይ ጋደም ብለን ሞቅ ያለ ጨዋታ ይዘናል…  እኔ እና እሷ አንድ ጋቢ ለሁለት ለብሰናል”

(ክፍል ሁለት)

ይህ የሦስት ተከታታይ ክፍል ፁሑፍ ሁለተኛ ክፍል ነው።

ጠዋት ስራ ባይኖርም ጓደኛችን ጉዳይ አለኝ ደርሼ ልምጣ ብላ ወጣች  እኛ ተነስተን ወደ አዲሱ ቤታቸው ሄደን፣ ከቤተሰቦቿ ጋ ቁርስ በልተን ጨዋታችንን አደራነው ቆይቼ “በቃ ልሂድ ብዙ ቆየሁ ” አልኩ “ለምን ? ትንሽ ቆይተን ፀሃይ ሲበርድ አብረን እንወጣለን” አለቺኝ ፣ እንደዛ ከሆነ ትንሽ ልተኛ አልኳት መኝታ ቤት አስገባችኝ ትንሽ ቆይታ መጣችና አልጋው ላይ ጋደም አለች፣ አቀፈችኝ ዝም ብዬ አየኋት “ሳሚኝ ” አልኳት። ፊቷ ፍም ሆነ ግራ ገባት ፣ ሳምኳት ዝም አለችኝ ቆይታ ግን መልሳ ሳመቺኝ ከዛ በኋላ ግን ማቆም አልፈለገችም። 

በዚህ ሁሉ ግን እኔም ራሴን አላመንኩም ፣ አልተቀበልኩም  እሷም እንደዛው። ቍስ ያለ እና ግራ ግብት ያለው ነገር ውስጥ ገባን። መለያየት አንችልም ፣ እኔን አይናገሩኝም እሷን ያሸማቅቋታል ትበሳጫለች፤ እበሳጫለሁ።  ምን እናድርግ?

ብዙ ጊዜ አብረን ማሳለፍ ጀመርን በጣም ተቀራረብን ፣ የነብስ ዓይነት ሳንገናኝ አንውልም ጊዜው አይበቃንም በዚህ መሃል እኔ ወደ ቢሮ እንደተቀየርኩ የሚገልፅ ደብዳቤ መጣልኝ እና ከስራ እንደወጣን ከሌሎች ጓደኞቻችን ጋ ተሰብስበን ሻይ እየጠጣን እንደዋዛ ቢሮ መቀየሬን ስነግራቸው እሷ ሳይታወቃት “ምን !” ብላ ጮኸች ቀለል አርጌ “የአንድ ታክሲ መንገድ እኮ ነው ብዙ አይርቅም ” አልኩ፣  እሷ ግን እያለቀሰች ጥላን ሄደች ስላላስብኩት በጣም ደነገጥኩ ሁሉም እኔ ላይ አፈጠጡ ትከሻዬን ሰብቄ ዝም አልኩ ። ጥቂት ቆይቼ  ቻው አልኩና ወደ ቤት ሄድኩ ማታ  ደወልኩላት “ተረጋጋሽ ?” አልኳት “ደህና ነኝ ይቅርታ ስላላስብኩት ነው”  አለች “ችግር የለም ብዙ አልራኩም እንደዚ እምናፍቅሽ አልመሰለኝም ነበር”  አልኳት ሳቀች ” ከባልሽ ተጣልተሽ ነው? ብሎ አጎቴ ሙድ ያዘብኝ ” አለች “ምን አልሽው ” ስላት “ያው በለው አልኩታ ” አለቺኝ። ርዕሱን ዘልዬ ሌላ ሌላ ብዙ አወራን ፍቅረኛ አላት፣  ምን ማድረግ እንዳለብኝም ስላላወኩ እንዳልገባኝ ሆንኩ ብቻ በየቀኑ ረጅም ስልክ እናወራለን፣ በቻለችው ሁሉ ምሳ ሰዓት አብረን ነን  ቀስ እያለች ገባችልኝ ፤ ወድጃታለሁ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግን አላውቅም።

ከጥቂት ጊዜ በኌላ ከፍቅረኛዋ ተለያየች እና ብዙ ጊዜ አብረን ነን ፣ ሌላ ሰው አትፈልግም ብቻዬን ነው ልታገኘኝ የምትፈልገው ውሎ እና አዳራችንን በዝርዝር  እናወራለን ቤተሰብ ሆንን እሷም ወደ እኛ ቢሮ መጣች አንድ ቢሮ ሆንን ማለት ነው ፤ እኛ ቤት እነሱ ቤት በብዛት እናድራለን ሰበብ ነው የምንፈልገው።  በዚህ መሃል እናቷ ለስራ ከሃገር ልትወጣ ስለሆነ የቤቱም ትልቅ እሷ ስለሆነች በአደራ አልፎ አልፎ እንዳያቸው ጠየቀችኝ ፤ እሺ አልኩ። 
አብረን የምናሳልፈው ጊዜ ብዙ ሆነ አይሰለቸንም ፣ ውለን አድረን መለያየት አንችልም አስተያየቷ ያሳዝነኛል ፣ አፍቃሪ ናት ግን ደግሞ ግራ ተጋባን ለግንኙነታችን ስም አልሰጠነውም። አፈቅርሻለሁ ብያት አላውቅም ፣ እሷም አትልም። ዓይኖቻችን ግን መደበቅ አልቻሉም እኛ ሳንለው ቢሮ ሁሉም ሰው አወቀው አወራው ዋና ተቃዋሚያችን ደግሞ ጓደኛችን ናት። በዚህ ሁሉ ግን እኔም ራሴን አላመንኩም ፣ አልተቀበልኩም  እሷም እንደዛው። ቅውስ ያለ እና ግራ ግብት ያለው ነገር ውስጥ ገባን። መለያየት አንችልም ፣ እኔን አይናገሩኝም እሷን ያሸማቅቋታል ትበሳጫለች፤ እበሳጫለሁ።  ምን እናድርግ?

በዚህ ደግሞ ፈጣሪዬን አሳዘንኩት ብዬ እፀልያለሁ እደነግጣለሁ።  ቤተሰቦቼ በዚህ መልኩ እንዲያዩን እና እንዲያዝኑ አልፈልግም ፤ እሷንም ማጣት ለኔ ከባድ ነው። ብቻ እማይጨበጥ ሆነብን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው እንደዚህ ያለ ነገር ውስጥ የገባሁት ፣ ብዙ ጊዜ አንድ ላይ መሆናችን ሌላ ሰው አለማስገባታችን ሃሜቱን አጦፈው ፣ ሁሉም ሰው ስለ እኛ ያወራል። እኛ ግን የለንም በራሳችን ዓለም ጠፍተናል ፤ በዚህ ሁሉ መሃል ሃሜቱ ጣራውን ሲያልፍ የሰው አስተያየት ሲቀየርብን፣ መግባባት እያቃታን ከራሳችን ተጣልተን እርስ በርስ መግባባት አቃተን እና አልፎ አልፎ አንዳንዴ ሃሜቱን ፍራቻ እሷ ከሌላ ወንድ ጋ መውጣት  መሞከር ጀመረች። ቅናቴን እና ችላ መባሌን ለመቋቋም ሞከርኩ፣ የማህበረሰቡ ግፊት እሷም የምትቋቋመው አልነበረም። በሌላ በኩል ደሞ ሁለታችንም ራሳችንን መቀበል ፈርተናል ፣ ከባድ ነበር  በቆራጥነት ኖ ማለትም  አልቻልኩም::  ምን ብዬ እንደማሳምናት የማውቀው ነገር አልነበረም ፣ ዝም ስላት ታዝናለች፣  ለምን ስላት ሃሜቱስ ትለኛለች። እንዳንዴ እየሳመቺኝ ታለቅሳለች።

ይቀጥላል …

Leave a Reply