ክፍል ሦስት: “የሆነ ቀን ፍራሽ ላይ ጋደም ብለን ሞቅ ያለ ጨዋታ ይዘናል…  እኔ እና እሷ አንድ ጋቢ ለሁለት ለብሰናል”

(ክፍል ሦስት)

ይህ የሦስት ተከታታይ ፁሑፍ የመጨረሻ ክፍል ነው።

እንደተወዛገብን እናቷ ከሄደችበት ተመለሰች።  በይ በዚህ ዕድሜ ነው ማግባት ያለብሽ የሚለው ምክሯ የዕለት ዕለት ጉትጎታ ሆነባት። በዚህ ጊዜ ጭንቀት ውስጥ ገባች ፤ መቋቋም የምትችለው ስላልነበረ ለሳምንት ያህል ታማ ከቤት ሳትወጣ ከረመች።  በጊዜ ሂደት በወሬ መሃል “ማግባት አለብኝ አይደል?” ትለኛለች። እኔ ደግሞ በኔ ምክንያት እንድትጨነቅ አልፈልግም፣  እንደ ሰው ነፃ ናት የምትፈልገውን የማድረግ ሙሉ መብት አላት ፤ የምትፈልገውን ታውቃለች። እኔ ልወዳት እንጂ ጭንቀት ልሆንባት አልፈልግም ፣ አንቄ ልይዛትም አልችልም ምን እንደምላት ይጨንቀኝ ነበር እና ከጊዜ በኋላ…. አ…ገ…ባ..ች ።  

ስለእኔ ሁሉንም ማወቅ ትፈልጋለች ፣ አጠገቤ መሆኛ ሰበብ ትፈልጋለች።  እኔ ተመልሰን እንድንገናኝ አልፈልግም፣  የልጆች እናት ሆናለች እሷ ዛሬም ከኔ ምን እንደምትፈልግ እምታውቅ አልመሰለኝም።


የሰርጓ ዕለት ሁሉም አልቆ ጨብ ብዬ ወደ ቤት እየሄድኩ ፣ መኪና ውስጥ ከኛ ጋ የነበረች ባልደረባችን ከቁጥጥሬ ውጭ ሆኖ እምባዬ ሲፈስ ማየቷን ነግራት ፣ እንዳዘነች ነገረችኝ። እዛ የተገኘሁት ህይወቷን ላለመረበሽ ሲበጠረቅ የከረመ የቢሮ ሃሜተኛ ሁላ ድራማ ሊያይ ጓጉቶ ስለነበረ ህመሜን ዋጥ አድርጌው በደስታ ፈገግ ብዬ ታደምኩ። እውነት ነው ፣ ደስታዋ ደስታዬ ነበረ ግን ህመሙ ችላ የሚሉት አልነበረም። ባሏ ባልደረባችን ነበረ እና በዙሪያችን ያለውን ነገር ያወሩት ስለነበር የሆነ አይነት ድራማ ለማየት ሳይጠራ የመጣው ሰውም ትንሽ አልነበረም። ስለዚህ ደስተኛ መሆኔ የገረመውም እዛው ሲያንሾከሹክ ነበር ፤ ብቻ ሁሉንም ልችለው ሞክሬያለው ዝም ለማለት ምንም እንዳልተፈጠረ ለመሆን ከጊዜ በኋላ ግን ማገገም አቅቶኝ እምነግረውም ሰው ባለመኖሩ በቃ ልፈነዳ ልቀውስ ሁላ መስሎኝ ነበር ፤ ደህና አልነበርኩም። ራሴን አይዞህ ብዬ ወስኜ እራቅኳት።  አሁንም በስራ አጋጣሚ ስንገናኝ  ሁሌ ልታወራኝ ትፈልጋለች። እኔን ለማግኘት ምንም ሰበብ ትፈልጋለች ፤ በአይኖቿ ዛሬም  እስክርቅ ትሸኘኛለች።  ስለእኔ ሁሉንም ማወቅ ትፈልጋለች ፣ አጠገቤ መሆኛ ሰበብ ትፈልጋለች።  እኔ ተመልሰን እንድንገናኝ አልፈልግም፣  የልጆች እናት ሆናለች እሷ ዛሬም ከኔ ምን እንደምትፈልግ እምታውቅ አልመሰለኝም። ሲያማት እንደምናፍቃት ታወራኛለች ፣ ግን አንድም ቀን ምን ያህል እንደተፋቀርን አውርተነው አናውቅም። አናሳዝንም?

 
እኔ ራሴን ተረድቼዋለሁ፣ ተቀብዬዋለው ፣ የማንንም ይሁንታ አልለምንም። ራሴን እወደዋለሁ ፣ ያሳለፍኩት ነገር ግን እስካሁን ያመኛል ይሄን ነገር ለማንም አውርቼው አላውቅም። ከቤተሰቦቼ እህቴ የምትጠራጠር ይመስለኛል ፣ በግልፅ አላወራንም እሚደግፈኝ እንደሌለ ግን ተረድቻለሁ ፤ እኔ ግን እኔ ነኝ። እስኪ እህትነታችሁን አሳዩኝ እውነት ሃሳቤን የሚረዳ አንድም ሰው አጠገቤ የለም::

 

Leave a Reply