
“ካንሰር አሁን ላይ በጣም በዛ” ወይም “እየተስፋፋ ነው” የሚል የተለመደ አባባል አለ። ነገር ግን ካንሰር በእርግጥ እየተስፋፋ ነው ወይንስ በተሻለ የምርመራ ቁሶች ኖረው ሆስፒታሎች በመጨረሻ ካንሰርን መለየት መቻላቸው ነው? ቀደም ባሉት ጊዜያት ሰዎች በሆስፒታል አልጋዎች ላይ ግራ እና ቀኝ ይሞታሉ። ቤተሰቦች የሕክምና ምክንያቶቹን ሳያውቁ የሚወዷቸውን አጥተዋል። ዛሬ ነገሮች የተለዩ ናቸው። ሰዎች ስለ ሞት መንስኤ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን ለመከላከል የተወሰኑ ምርመራዎችን እንዲወስዱ ምክር ይሰጣቸዋል። ሕመሞችን ለመለየት እና በተቻለ መጠን ሰዎችን በሕይወት ለማቆየት የሚረዱ የተለያዩ የህክምና መሣሪያዎች አሉ።
ከዛ ደግሞ በተመሳሳይ “የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስፋፋ ነው።” ግን እየተስፋፋ ነው ወይንስ ኩዊር ሰዎች የራሳቸውን ታሪክ መፃፍ፣ የተለያዩ መረጃዎችን ማግኘት እና ከሰፊው ኩዊር ማህበረሰብ ጋር መገናኘት ችለው ነው? ኩዊር ሰዎች አሁን እኛ በፊት ባልነበረን መንገድ የበይነመረብ መዳረሻ አላቸው። አሁን ላይ ኩዊር የሆነ ነገር በኢንተርኔት ለመፈለግ አደጋ ላይ ሊጥልብን ወደሚችለው የኢንተርኔት ካፌ መሄድ አይጠበቅብንም። ቴሌ ሁላችንንም አገናኝቶናል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ ራቅ ካሉ አካባቢዎች ሳይቀር ቲክቶከር ማግኘት ይችላል።
የኩዊር ኢትዮጵያውያን ነፃ መውጣት በእጃችን መዳፍ ላይ ነው። በአልጋችን ላይ ሆነን የጥላቻ ንግግርን እንቃወማለን። ያለ ይቅርታ በመስመር ላይ በመገኘታችን ጥቃትን እንቃወማለን። ለማንበብ፣ ለመማር፣ ራሳችንን ለማስታረቅ እና ከተጫነብን ጥላቻ ለመፈወስ (ጠብቆ) ብዙ አማራጭ አለ። ሰዎች በራሳቸው ቋንቋ ቢያንስ በአንድ ወይም በሁለት የአከባቢ ቋንቋዎች ፅሁፎችን እያገኙ ነው። በመላው አገሪቱ እና አህጉር በኢንተርኔት አማካኝነት እየተገናኘን ነው። ደህንነቱን የተጠበቀ አማራጭ የዲጂታል ዓለምን ለራሳችን እየገነባን ነው።
ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ ነበርን። ምንም እንኳን ያለማቋረጥ የሰይጣን ስራ እየተባልን እና እየተጠቃን ቢሆንም፣ መኖራችንን እንደቀጠልን አለን። በበለጠ መታየነት እና ተደራሽነት፣ በራሳችን መንገድ ነፃ መሆናችንን እንቀጥላለን። እየተስፋፋን አይደለም። የተቃራኒ ፆታ አፍቃሪው ዓለም መደበቅ (ጠብቆ) እንዳላስፈለገው ሁሉ እኛም እንዲሁ እምቢ እያልን ነው።