
“ጊዜው እንዴት ይሮጣል” አላላችሁም?
የጥላቻው ዘመቻ…
ወደኃላ መለስ ብለን እናስታውሰውማ! እስቲ አንዴ ጨፍናችሁ የነበራችሁበትን ቦታ አስቡት!
ከዚህ መንደር ድራሻችንን አጥፍተን፣ ስልክ ቁጥራችንን ቀይረን፣ እንደዛ ተጫዋች እና ሰው ማግኘት የምንወድ የነበርን በራችንን ቆልፈን፣ አለባበሳችንን ይሁን ያስገምተናል ወይም ያስጠረጥረናል ያልነውን ሁሉ ለመቀየር ሞክረን፣ አንዳንዶቻችንም ተሰደን። ቀን እና ለሊት ሪፖርት አድርጉ እየተባባልን፣ የእኔንስ ፎቶ ይለቁብኝ ይሆን ስጋት እና ሰቀቀን ውስጥ ሆነን የተከፈተብን የጥላቻውን ዘመቻ ሁሉ አልፈን ይኸው አለን::
ስንቱ ተነሳብን… ከምናውቀው የማህበራዊ ሚደያ ጀለሳችን እስከ ጎረቤት… ከመንገደኛው እስከ የቤተ እምነት መሪው… ወደን ከምንከታተላቸው የዘወትር ቲክቶከሮች እስከ መንግስት ልል ነበር ለካ በህግም ምንም አይነት ከለላ የለንም::
ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን ጨፍነን ድጋሚ እንድናስብ የምፈልገው ህብረታችንን ነው:: አዋርተን የማናውቃችውን ሰዎች “እንዴት ነሽ? አለሁልሽ” መባባል ቻልን፣ አክቲቪስት ሆነን የጎረቤታችን ጠባቂ አደረጉን፣ ትንሽ ትንሽ እንፅፍ የነበርነውን ጎልተን እንድንወጣ አደረጉን፣ ቤታችን ተደብቀን የነበርነውን በአዲስ አካውንት መጥተን ትግሉን እንድንቀላቀል አደረጉን፣ በዛ ሁሉ ውስጥ ፈታ የሚያደርጉንም ድምፃች ተወለዱልን:: በማህበራዊ ሚድያ በግልፅ ሰምተናቸው የማናውቃቸው በየቤቱ ያሉ ድጋፊዎቻችን፤ በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ በኩል “አለንላችሁ አይዞን ኮራንባችሁ” አሉን:: በዚህ መሃል አረ ፍቅረኛም ያገኘ አለ፤ ከትውውቅ ከመተማመን ትግል ላይ ፍቅርን የተቀዳጁ አሉ:: መልካም ጓደኝነት ያፈሩም እንዲሁ።
በፊት አይተን ከምናውቀው ጥላቻ የጠነከረ እና አስፈሪ ማለት ቢቻልም አለፈ:: “ሁሉም ያልፋል” ሲባል ቀላል ይመስላል ግን ያለን ተስፋ እሱ ነው! እዩት ያስጨነቀን አልፎ ህይወት ቀጠለ:: ምንም ጥላቻ የለም ማለት ሳይሆን ትላንት የነበረው የውስጥ ፍርሃት እና ሽብር ግን አይኖርም:: አንድ ወደፊት ተራምደናላ! ህብረታችን አለሁሎት አለሁልሽ መባባላችን አበርትቶናላ!
የማናልፈው አይኖርም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ህብረት ጥላቻን ይሰብራል።
ትግሉ ይቀጥላል።