
የእናቴ ታሪክ የፅናት እና የመስዋዕትነት ነው። ገና በ13 ዓመቷ፣ ያደገችበት ህብረተሰብ እንድታገባ ስለተጫናት ትምህርትዋን መሰናበት ነበረባት። ምክንያቱም በእነዚያ ጊዜያት አያቴ የሴት ዋጋ ሚስት እና እናት በመሆን ላይ ያተኮረ እንደሆነ ያምን ነበር። ምርጫዋ አልነበረም፣ ግን የአባቷን ፍላጎት ለመታዘዝ እንደተገደደች ተሰማት። እሷ የምታውቀው ታዛዥነት ብቻ ነበር።
ነገር ግን እናቴ ቆራጥ ነች። እኛን ልጆቿን ነባራዊ ሁኔታን በሚፈታተን መልኩ የህብረተሰቡን ደንቦች ተቃወመች። እኔና እህቶቼ እንደ ወንድሞቼ ተመሳሳይ እድሎች ተሰጠን። ትምህርት ለመከታተል፣ ከትምህርት ቤት በኋላ ለመማር እና በአለባበሳችን እና በአስተያየታችን ምርጫ ራሳችንን የመግለጽ ነፃነት አግኝተናል። በእኛ በሴቶች ልጆቿና እና በቤተሰባችን ውስጥ ባሉ ወንዶች ልጆች መካከል አድሏ አልነበረም። ጠንካራ እንድሆን፣ ላማምንበት ነገር እንድቆም አስተማረችኝ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሌዝቢያን መሆን ቀላል አይደለም። በእሾህ መስክ ላይ ያለ የእግር ጫማ እንደ መሄድ ማለት ነው። ይህን የማንነቴን አንድ ክፍል ለእናቴ ለማካፈል ድፍረት አግኝቼ አላውቅም። ትርጉሙን ሙሉ በሙሉ ላትረዳው እንደምትችል እጨነቃለሁ፣ እናም በዚህ የህይወቷ ደረጃ ላይ ይህንን ነገር ላሸክማት አልፈልግም። ምናልባት ትጠራጠር ይሆናል፣ ነገር ግን በቀላሉ የምትረዳበትን መንገድ አላገኘችም። ውስጤ ግን ምንም ይሁን ምን እናቴ በክፍም በጥሩም ቀን ከጎኔ እንደምትቆም አውቃለሁ። የምትደነቅ ሴት ነች።
ስለ እናቴ በጣም የምወደው ነገር የማህበረሰቡን ጫና በእኛ ላይ ለመጫን እምቢ ማለቷ ነው። ማናችንም እንድንጋባም ሆነ ልጅ እንድንወልድ ግፊት አድርጋ አታውቅም። የውጫዊ ተፅዕኖ ሳይሰማን በራሳችን መንገድ ህይወትን የመኖር ነፃነታችንን አስከበረችልን። እንዲህ ዓይነቱ ድጋፍ እውነተኛ ማንነቴን እንዳውቅ እና ህይወቴን በእውነተኛነት እንድመራ አስችሎኛል።
በዚህ ልዩ የእናቶች ቀን፣ የሕይወቴን ገጽታ ሁሉ ከእሷ ጋር ለመካፈል እጓጓለሁ። የወደፊት ህይወቴን አብሬ ልኖር ከምፈልገው ፍቅረኛዬ ጋር ላስተዋውቃት እጓጓለሁ። ግን ሁኔታዎች ባይፈቅዱም እና መናገር ባልችልም እናቴ ልዩ ሴት መሆኗን እንድታውቅ እፈልጋለሁ። በለጋ እድሜዋ ህልሟ ቢነጠቅም ለኔ ግን አለምን ሰጠችኝ። መልካም የእናቶች ቀን ፣ እናቴ። በጣም ድንቅ ሰው ነሽ።