Skip to content Skip to footer

እናቴ፣ ህመምና የሚስቴ ናፍቆት

ሰው ነንና መታመም አይቀርም። እኔም ከሰሞኑ ትንሽ ጉንፋን ቢጤ ታምሜ ቤቴ ተኝቼ ነበር። ያው ከቤት እናቴ ስትደውል ድምፄ በደንብ ወፍሯል እና እንደታመምኩ ያስታውቃል። ብቻዬን እንደምኖር ነው የሚታወቀውና አጠገቤ ሰው እንደሌለ አስበው እቤት ካልመጣሽ ብለው አስጨነቁኝ። እናቴም በጣም ተጨናነቀች።

እዚ የምትንከባከበኝ ሚስት አለችኝ ከእሷ ጋር ነው የምኖረው አልል ነገር ማግባቴ አይታወቅም፤ ያውም ሴት። አንዳንዴ ቢያውቁ ብዬ እመኛለሁ ምክንያቱም ነገሮች ምን ያህል ይቀሉ ነበር። እናቴ ቤትም ሄጄ እረፍት አድርጌ እንደመምጣት የሚስቴ ናፍቆት ደግሞ እረፍት ነሳኝ። ከመታመሜ በላይ እኔን ያሳሰበኝ የምግብ ፍላጎቴን የቀነሰው ከቤቴ ከሚስቴ መራቄ ነው ይህንን ደግሞ ለቤተሰብ ማስረዳት ከባድ ነው።

ነገሮችን በግልጽ መናገር አለመቻላችን ማህበረሰባችን ትክክል ብሎ ከሚያስባቸው ያኗኗር ዘይቤዎችን ከሚከተሉ ሰዎች በላይ ፈተናችንን ያበዛዋል፤ ህይወታችንን ያከብደዋል። ራሳችንን ለመቀበል የሚወስድብንን ጊዜ እና ትግል አልፈን ደግሞ ደስተኛ ሆነን ህይወት መስርተን አግብተን ስንኖር ትልቁ ትግላችን ይጀምራል።

ህይወታችን ውስጥ ቤተሰቦቻችንን እንዴት አድርገን ቦታ መስጠት እንደምንችል ከበሽታችን ባሻገር አጠገባችን ያሉት ሰዎች ሚስት፣ እናት፣ አባት፣ እህት… እንዴት አድርገን በአንድ ቦታ ማግኘት እንደምንችል ጭንቀት ይጀምረናል። እኔ በዚች ትንሽ ህመምና ጊዜ ውስጥ የተረዳሁት እዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ኑሯችን ምን ያህል ትግል እንደሆነ ነው። ግን ደግሞ ህይወት ይቀጥላል፤ ጊዜ ጥሩ ነገር እስኪመጣ ወይ ቤተሰቦቻችን ሁሉ ነገራችንን ተቀብለው እንደማንኛውም ቀጥ ባል እና ሚስት በሁሉም ነገር ቤተሰብ ፊት መደጋገፍ እስከምንጀምር በተስፋ እንኖራለን።

Leave a Reply

Discover more from queerethiopia

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading