ህይወት እንደምታስቢው አይደለም። ይሄንን የምለው ነገሮች ሳታስቢያቸው ከተለያዩ ቦታዎች ስለሚከሰቱ ነው። ዱብዳ ወይ ምች በይው! ምንም ማቀድ አትችይም በቃ! አሁን አንድ ነገር አስበሽ ጭራሽ የማይገናኝ ነገር ይፈጠራል። ጥሩም መጥፎም ማለት ነው፤ ያው እንደአመጣጡ መቀበል ነው። በእኛ ሃገር “እንደፈጣሪ ፍቃድ” ብለን እንደምናልፈው ማለት ነው።

ይሄ ደግሞ እንደኩዊር ኢትዮጵያዊ ሌላ ትልቁ ተግዳሮት ነው። ከሁለት ሰኮንድ በኋላ የሚፈጠረውን ማወቅ ያዳግታል። አንዱ ጀዝባ “ግብረሰዶምን እቃወማለሁ” የሚል የስራፈት ዘመቻ ይዞ በግልሽ እና በዙሪያሽ ያለውን የኩዊር ማህበረሰብ ህይወት ምዕራፉን ይቀያይረዋል፤ ያናውጠዋል። ይሄንን ማለቴ ነው ነገሮችን ማወቅ ይከብዳል ያልኩት። መቼ ሰዎች ስለማንነትሽ እንደሚያውቁ አታውቂም። ስራ ቦታ፣ በስፖርት ማሰልጠኛ፣ በጓደኞችሽ ወይም በቤተሰብ። ከዛ ሲያውቁ ደግሞ እንደጥቁር በግ እንደሚባለው በነሱ አለም ለመካተት ሌላ ጣጣ ሌላ ትግል። ነገር ግን በቃ በራስ መጠንከር እና መግፋት ይኖርብሻል። በማንንም ልደገፍ አልፈልግም፣ ህይወት ምንም በኔ ላይ ብታመጣ በራሴ መንገድ ነው ነገሮችን መወጣት የምፈልገው።
እንደገና ነገሮች ተሳኩልኝ ስትይ ደግሞ የምትወጂውን ታጫለሽ..ሌላ ያልጠበቅሽው የህይወት ክስተት። ህይወት ልክ እንደሎሳንጀለስ ሰደድ እሳት ነው በቃ ምንም የማይገመት የማይጠበቅ ምናልባት እንደሲምሰንስ ትንሽ ፍንጭት ኖሯቸው ይሆናል 😅 ግን በቃ ህይወት እንዲህ ናት።
ትልቁ ነገር ሚዛናዊ የሆነ ህይወትን መምራት መቻል ነው። ኡኡቴ እንደው ልበለው እንጂ እኔም ይሄንን ህይወት ሚዛናዊ ለማድረግ ገና እየሞከርኩ ነው። ነገሮችን ማቀድ ይከብደኛል። “በቃ በዚህ ወር በዚህ ያህል ገንዘብ ብቻ ትንሽ ልዝናና” እልና መዝናኛው ይዞኝ ጭልጥ እኔም ካቀድኩት በላይ አጥፍቼ የብሮክ ህይወቴን አጣጥማለሁ። ችጋር ሲጠብሰኝ ነው እንደገና ተመልሼ ራሴን ለማስተካለል የምሞክረው።
ራሴን ዘወትር በመፈተሽ፣ ብዙ ከገደብ ያለፈ መዝናናት ሳዘወትር “ምን እየሰራሽ ነው?” ብዬ በመጠየቅ፣ የያዘኝ ምንድን ነው ብዬ ወደቀልቤ ደግሞ እመለሳለሁ። ይሄ ማለት ጓደኞች መቀነስ ሊሆን ይችላል፤ ህይወት ላይ የተለያየ እይታዎች ካሉን መለያየቱን እመርጣለሁ። በሌላኛው ገፅ ደግሞ ከአቅሜ በላይ በስራ ስወጠር ራሴን አረጋግቼ ፈታ ዘና በይ እላለሁ። ከምወዳቸው የኩዊር ጓደኞቼ ጋር መዝናናት ደግሞ ትልቅ የጉልበት ምንጭ ነው። በጨዋታ፣ በፍቅር፣ በሳቅ የታጀበ የምክር አገልግሎት በይው።
ብቻ ህይወት ግራ ብታጋባም፣ የሚሆነው ባይታወቅም፣ ከስህተቶቼ እየተማርኩ፣ እንደአዲስ እያቀድኩ፣ ወጥሬ እየሰራሁ፣ በብልጠት እየተዝናናሁ በዚህ ውስጥ የአዕምሮ ጤናዬን እጠብቃለሁ።