የኩራት ወር ሲያልቅ፣ ኩራት የአንድ ወር በዓል ብቻ ሳይሆን የእድሜ ልክ ጉዞ እንደሆነ ከራሴ ጋር እያሰላሰልኩ አገኛለሁ። ይህ ያለፈው ወር ከጓደኞቼ ጋር ለመገናኘት ፣ ለማክበር እና እራሴን ብዙ ጥያቄ ለመጠየቅ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮልኛል።
በእውነት በደስታ እና በተስፋ የሚሞላኝ በአለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ኩራትን የሚያከብሩባቸውን የተለያዩ መንገዶች ማየቴ ነው። አምና በሳኦ ፓውሎ፣ ብራዚል በተካሄደው የኩራት ሰልፍ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል ተብሏል። ይህን እኔ እንደተአምር ነው ያየሁት። እነዚህ ሁሉ ሰዎች በአንድ ላይ ኩራትን ለማክበር ይሰባሰባሉ ብዬ መገመት ምንም አልቻልኩም። ግን እዛ መገኘት ምን ያህል ደስ የሚል ነገር እንደሆነ አስባለሁ።
በጣም የሚገርመው ሌላው 24,000 ሰዎች አምና የጆሃንስበርግ ኩራት ሰልፍን ተቀላቅለዋል! በአፍሪካ ውስጥ ያለው የኩራት ሰልፍ ወይንም በአል ብዙ ተሳታፊዎችን ሊስብ ይችላል የሚለው ለእኔ በጣም አበረታች ነው። በሁሉም የአለም ማዕዘናት ኩዊር ሰዎች እንዴት ለመብታቸው እንደሚሞገቱ ያሳያል።
መጀመሪያ ላይ፣ ስለእነዚህ ግዙፍ፣ አንጸባራቂ ኩራት በአሎች ሳነብ ወይንም ሳይ፣ “እውነተኛ” የኩራት በዓል ትልቅ እና ማራኪ መሆን እንዳለበት ከማመን ውጭ ምንም ማድረግ አልቻልኩም። ኩራት በአል ማለት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ድምቅምቅ ያሉ እና በየጎዳናዎች ላይ የሚጨፍሩ አረጌ ነበር ያሰብኩት። ግን ከዚያ በአዲስ አበባ ውስጥ ካሉ 13 ኩዊር ሰዎች ጋር ያሳለፍኩትን የኩራት በአል አስታወስኩ። ያ ለእኔም ልዩ እና ትርጉም ያለው ነበር፣ ምናልባትም ከትልልቆቹ በአላት በላይ የበለጠ። ኩራት በህዝብ ብዛት እንደማይለካ እንድገነዘብ አድርጎኛል። ኩራት ውድ ግኑኝነቶች ከLGBTQ+ ማህበረሰባችን ጋር መፍጠር እና ወደ ኋላ ሳንል ሙሉ ማንነታችን የምንሆንበት ቦታ ማግኘት ነው።
ለእኔ ትልቁ የተመርኩት ነገር ኩራት አንድ ወር ብቻ እንዳልሆነ ነው። ኩራት ማንነትን ተቀብሎ፣ ለሌሎች ኩዊር ሰዎች ቦታ የመስጠት የእለት ተእለት ልምድ ነው። ይህ የኩራት ወር ሲያልቅ፣ አዲስ ጅምር መሆኑንም እራሴን እያስታወስኩ ነው። ለማክበር እና እውነተኛ ማንነታችንን ለመኖር አንድ አመት ሙሉ አለን።