Skip to content Skip to footer

ዘመቻ: ፍርሃት፣ እንክብካቤ እና ትምህርት

የጥላቻው ዘመቻ ሰሞን የነበረው ስሜት 
<<ግብረሰዶምን እቃወማለሁ>> የሚለው የመጀመሪያው ቪድዮ ታኅሳስ 05/04/2015 ሲለቀቅ ለምን እንደሆነ አላውቅም ስልኬ ላይ አስቀርቼው ነበር፤ ስክሪን ሻት ያደረኩት እስካሁን አለ። ቪድዮ መጀመሪያ ላይ አስቆኛል ነገር ግን የሰዎችን ምላሽ ሳይ በጣም ደነገጥኩ። የሰዎች ምላሽ በጣም የሚያሳቅቅ ነበር “እንግደላቸው እና እናስወግዳቸው” የሚሉት ምላሾችን እያየሁ ብዙ ጥያቄዎች በሃሳቤ እንደጎርፍ ተመላለሱብኝ። የእነሱን ቃል ለመጠቀም ያህል “ኃጢያቴን” እንኳን በግልፅ አላወጅኩም፤ ወሲባዊ ማንነቴም ማንንም አይጎዳም። 

ልቤ በማላውቀው የዜማ አጣጣል ሮጠ፤ ሰውነቴ ዝግንን አለው። ስልኬ ከእጄ ሾልኮ ሲወጣ ራሱ መያዝ አልቻልኩም። ድንጋጤውን መቋቋም አልቻልኩም።

መጀመሪያ ላይ ብዙም ግድ አልሰጠኝም ነበር … በማግስቱ ጠዋት ረሳሁት። ሆኖም ፦ ከአንድ ወር ገደማ በፊት በማህበራዊ ሚዲያ በተለይ በቲክቶክ በኩል የጥላቻ ማዕበል ተከፈተ። የተለቀቀውን የፓርቲ ቪድዩ እና የጥቃት ጥሪውን ሳይ በልቤ ውስጥ ጥልቅ የሆነ ፍርሃት ነበር የተሰማኝ። ለመግለፅ የሚከብድ ግራ መጋባት እና ትንፋሽ እጥረት ነበር የተሰማኝ፤ ልክ አየር ከክፍል ውስጥ የተመጠጠ አይነት ስሜት። ልቤ በማላውቀው የዜማ አጣጣል ሮጠ፤ ሰውነቴ ዝግንን አለው። ስልኬ ከእጄ ሾልኮ ሲወጣ ራሱ መያዝ አልቻልኩም። ድንጋጤውን መቋቋም አልቻልኩም። ቪድዮ ላይ የተለቀቁትን ሁሉ አቅፌ ባፅናናቸው ተመኘሁ።

ጥላቻን በሚነዙት ላይ ዓመፅ ነበር ያሰኘኝ፥ በፍቅር እና በመረዳት እያንዳንዱ ሰው የተለያየ ማንነት መኖሩ ፍፁም ትክክል እና ተቀባይነት ያለው መሆኑን እንዲገነዘቡ ለማድረግ ከፍተኛ ተነሳሽነት አደረብኝ።

ፓርቲ ቪድዮ ከመለቀቁ አንድ ቀን በፊት ለጓደኛዬ ስለወሲባዊ ማንነቴ ነግሪያት ነበር ፤ በጣም ነበር የደገፈችኝ። እንዳጋጣሚ ሆኖም በቡድን ሆነው ጌ ይሆናል ብለው የጠረጠሩትን ትንሽ ልጅ ሲደበድቡ ያለውን ቪድዮ እሷ ነበረች ያሳየችኝ። የዛ ምስል ተፅዕኖ ከጭንቅላቴ ላወጣው የማልችለው ክብደት ነበረው። የዓለም ሁሉ ሀዘን በልቤ የፈሰሰ ያህል ነው የተሰማኝ:: በቻልኩት ሁሉ ልጁን ለማግኘት ዝግጁ ነበርኩ ምክንያቱም የሱ ስቃይ የተለያየ ስሜትን ነበር የቀሰቀሰብኝ፥ ፍቅር፣ ርህራሄ፣ ንዴት እና ጥላቻ። ጥላቻን በሚነዙት ላይ ዓመፅ ነበር ያሰኘኝ፥ በፍቅር እና በመረዳት እያንዳንዱ ሰው የተለያየ ማንነት መኖሩ ፍፁም ትክክል እና ተቀባይነት ያለው መሆኑን እንዲገነዘቡ ለማድረግ ከፍተኛ ተነሳሽነት አደረብኝ። ያንን ወጣት ልጅ በቅርብ ለመያዝ፣ ለማረጋጋት እና ፍርሃቱን ከፊቱ ላጠፋለት ተመኘሁ።  ወንድሜ ይሄንን ፅሁፍ በአጋጣሚ እያነበብክ ከሆነ እጅግ የተወደድክ እንደሆንክ እንድታውቅ እፈልጋለሁ። መላው የኩዊር ማህበረሰብ ከጎንህ ነው።

ራሴን የተንከባከብኩበት መንገድ
በጎዳና ወጥቼ በጨቋኞቻችን ላይ የማመፅ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ ሆኖም ይህን ማድረግ ለሞት እንደሚዳርገኝ አውቃለሁ። ከህይወት በላይ ምንም የለም፤ ለዚህም ነው ማንነቴን በመደበቅ በቃላቶች ድምፄን በማሰማት ለዓላማችን መታገልን የመረጥኩት። ከዚህ የጥላቻ ዘመቻ በፊት ማህበራዊ ሚድያን ረስቼው ነበር:: ወደሁለት ወር ገደማ ፌስቡክ ላይ አልገባሁም ነበር:: ይህ ከተፈጠረ በኋላ ግን ኢንተርኔት ዳታዬ ሁሌም ክፍት ነው።

ባለፈው ወር ቲክቶክ እና ፌስቡክ በማቀያየር ሙሉ ጊዜዬን ማህበራዊ ሚድያ ላይ ነበርኩ። በዚህ ነገር ላይ በጣም ከመጠመዴ ምንም ነገር እንዳያመልጠኝ በሚል አንዳንዴ ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ምሳ መውጣቱን እዘል ነበር። የየሰዓቱ መረጃ እንዲኖረኝ እና ወቅታዊ ሆኜ እያንዳንዱን የጥላቻ መልዕክት ሪፖርት ለማድረግ እፈልግ ነበር።

ይህ (ኩዊር) ማህበረሰብ የእኔ ዓለም እና መሸሸጊያ ሆኗል። በእኛ ላይ የተነጣጠረው ጥላቻ ድምፃችንን አንድ አድርጎ ከመቼውም በላይ አቀራርቦናል::

ይህ (ኩዊር) ማህበረሰብ የእኔ ዓለም እና መሸሸጊያ ሆኗል። በእኛ ላይ የተነጣጠረው ጥላቻ ድምፃችንን አንድ አድርጎ ከመቼውም በላይ አቀራርቦናል:: በማህበረሰባችን ውስጥ እንዲህ አይነት ፍቅር እና ትብብር አይቼ አላውቅም። አንዳንድ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ጥላቻን ተቃውመው ሲናገሩ ማየት የኔን ቆራጥነት ከማጠናከር ባለፈ ለዓለም መኖራችንን አሳይቷል። ከዚህም ባለፈ <<ዜጋ ፖሊስ>> ላይ እነዚህን ቪድዮዎች ሪፖርት ለማድረግ ያደረግነው እንቅስቃሴ አዎንታዊ ውጤቶችን አምጥቷል፤ ብዙ የጥላቻ መልዕክቶች ከማህበራዊ ሚዲያው አስጠፍተናል። የኤደን ሳሙኤል ማበረታቻ እና ከዚህ የጥላቻ ዘመቻ ጋር የተያያዘ ማንኛውንም ነገር ለመቅረፍ የወሰደችው ፍጣን እርምጃ እና ጥረት ለብዙዎቻችን ምቹ ቀጠናን ፈጥሯል። ለእኔ ዋና የብርታት ምንጭ ነበርሽ እና ጥረቴ በቂ ባይመስልም ትግሉን እንድቀጥል አነሳስተሽኛል። እነዚህ ጥቂት ነገሮች የአዕምሮ ጤናዬን እና ደህንነቴን እንድጠብቅ ረድተውኛል።

ለኩዊር ማህበረሰብ ያለኝ መልዕክት
ለኩዊር ማህበረሰብ ወገኖቼ፥ ያለፈው ወር ለሁላችንም ከባድ ነበር:: በእነዚህ የፈተና ጊዜያት ሁላችንም ደክሞናል። በዙሪያችን ከአቅም በላይ የሆነ የፍርሃት ስሜት እና ማመንታት ወይም እርግጠኛ ያለመሆን ነገር ነበር። የእነሱ የጥላቻ ቪድዮ ሰለባ የምንሆነው መቼ ይሆን ፣ ቀጣዩስ እኔ እሆን ይሆን ብለን አስበን ነበር። ነገር ግን በዚህ ሁሉ ሁከት ውስጥ ተሳስበን አንድ ሆነን ቆምን። በቻልነው ሁሉ የእርዳታ እጃችንን እየሰጠን እርስ በእርስ ተደጋገፍን።

ከዚህ የጨለማ ጊዜ ያገኘነውን እነዚህን ውብ ባህሪያት አጥብቀን እንያዝ።

ከዚህ የጨለማ ጊዜ ያገኘነውን እነዚህን ውብ ባህሪያት አጥብቀን እንያዝ። ለወደፊቱ እጅግ ጥንቃቄ እናድርግ:: የግል መረጃዋቻችሁን ለማንም አታሳውቁ። አላስፈላጊ አደጋ ላይ የሚጥልን ነገር በተቻለ መጠን እናስወግድ። የእናንተ ህይወት ዋጋ ለእኛ አለው እና የእናንተ መኖር ማህበረሰባችንን ያለለፅገዋል። ከቀስተ ደመናችን አንዱን እንኳን ማጣት አንፈልግም። እንኖራለን፣ አንድነታችንን እና ትግላችንን እንቀጥላለን።

Leave a Reply

Discover more from queerethiopia

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading