ልጅ እያለው ዘመድ ጥያቄ ነበርኩ። ሩቅ ያሉት ዘመዶቼ ጋር በመሄድ አሳልፍ ነበር። ከሰው ጋር በጣም ተግባቢ የምባልና ከዘመድ አዝማዶች ጋር ጊዜ ማሳለፍ የሚወድ ልጅ ነበር። በጣም ነበር የምወደው!
ነገር ግን ወደኩዊር ማንነቴ ስመጣ ይሄ ነው የምለው ነገር እንኳን ባይቀየር ብዙ ነገሮች ተለወጡብኝ።

ስለማንነቴ ያፋጠጠኝም፣ የጠየቀኝም አልነበረም። ማናቸውም ክፉ ቃል አልተናገሩኝም። ማናቸውም ፊቴ ላይ በራቸውን አዘጉብኝም። ብቻ ማንነቴን ካወኩ በኋላ በእኔ እና በዘመዶቼ መሃል ክፍተቶች ተፈጠሩ። ምክንያቱም በድንገት “ምን ሊፈጠር ይችል ይሆን?”የሚለውን ነገር ማሰላሰል ጀመርኩኝ። ስለማንነት ቢያቁ እና ባይፈልጉኝስ? ከሌላ ሰው ሰምተው ቢያፋጥጡኝስ? በር ቆልፈው ለሳምንታት እንመልሳታለን በሚል በጸሎት ሊታገሉኝ ቢሞክሩስ?
ስለዚህ ወደኋላ አፈገፈኩ። መጠየቅም መጎብኘትም አቆምኩኝ። እንደበፊቱ መውደዳቸውን ቢያቆሙ ምን ሊፈጠር እንደሚችል በማሰብ ራሴን መከላከል ጀመርኩኝ።
በቅርብ በነበረ ለቅሶ ላይ ከአብዛኞቹ ጋር ተገናኘን፤ ቤታቸው ቤቴ የነበረ እዛው ነበሩ። ከመሀል አንደኛው እንደዚህ አለኝ:
“ዘመድ ሁሉን በመጠየቅ በጣም ጎበዝ ነበርሽ ምን ተፈጠረ? ማንም ሰው አሁን ያለሽበትን አያውቅም?”
ልክ እንደጠየቀኝ ዓመታት ያስቆጠረው ዝምታዬ እና መጥፋቴ ሁሉ ግጥም አለብኝ።
ምን ሆኜ ነው? ምንም እና ሁሉም ነገር። ራሴን ሆንኩኝ። ማንነቴን መደበቅ ደከመኝ። በፍርሃት፣ በጥፋተኝነት እና ወራድነት ስሜት ብዙ ታገልኩኝ። ማንነቴን በትንሹ የሚያቁ ቦታዎች ላይ ራሴን ሆኜ እንደገና መገኘት እንዴት እንደሚቻል ግራ ገባኝ። ያ አይደል የሚያሳዝነው! ፍርሃት እና ዝምታ በራሳቸው አጥር ይገነባሉ፤ ክፍተትን ይፈጥራሉ።
ነገር ግን ለቅሶ ላይ ተገኘሁ። አብሬ ታደምኩ። የምወዳቸውን ዘመዶቼን አቀፍ አብሬም አለቀስኩ። ታዲያ ምናልባት አንድ ቀን በሙሉ ማንነቴ ደግሞ እገኝ ይሆናል ብዬ ተመኘሁ።