ንስንስ ላይ ከአዕምሮ ጤና አማካሪ ጋር ባደረግነው ቃለ መጠይቅ ላይ እየቀጠለ ካለው መገለልና ጥላቻ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ዙሪያ በጣም አስፈላጊ እና ጠቃሚ ምክርን አካፍላናለች:: ይህንን ቃለመጠይቅ በድጋሚ እያካፈልን ምንም እንኳን በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ እያለፈን ቢሆንም ተስፋ እንዳለም ደግሞ ልናስታውሳችሁ ወደድን::
ጥያቄ፡ እየተካሄደ ባለው የጥላቻ እና የመገለል ዘመቻ ውስጥ ጭንቀት እና ተስፋ መቁረጥ እየተሰማቸው ላሉ የተመሳሳይ ፇታ አፍቃሪዎች መልእክሽ ምንድነው?
የተለመደ አባባል ነው ግን ብቻችሁን አይደላችሁም ማለት እፈልጋለሁ፤ መኖራችሁን፤ መዳናችሁን የሚፈልጉና ከዛም በላይ እንድታብቡ የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች አሉ።ሁሌም ታካሚዎቼንና ጓደኞቼን `ይህን ውይይት ማድረግ ስላለብን ራሱ አዝናለሁ፤ ልንወጣቸው የሚገቡ አደጋዎች ስላሉ አዝናለሁ ግን ደግሞ ብቻችንን መጋፈጥ የለብንም፤ ችግሩን ለመወጣት የለመድናቸው ልምዶች የእናንተ ጠዕፋት አይደሉም` እላቸዋለሁ። ከባድ በመሆናቸው መርሳት እና መጋፈጥ የማንፈልጋቸው ነገሮች ውስጥ ተገደን ገብተን ሊሆን ይችላል፤ ምንም ማለት አይደለም፤ ያን ማድረጋችሁ ጥፋት አይደለም። እፍረቱ፤ የጥፋተኝነት ስሜቱ፤ መሰላቸቱ እና ንዴት የሚጠበቁ ናቸው። ምላሻችሁ ጤናማ ወይም ትክክል መሆን አለመቻሉ ምንም ማለት አይደለም። ብቻችሁን አይደላችሁም።
ጠንካራ ግንኙነት መመስረት። የተጠበቀ የደህንነት ፕላን ማውጣት፤ ማንን ነው የምታምኑት? እንዴት ነው ምላሽ የምትሰጡት? ማምለጥ ቢኖርባችሁ እንዴት ነው የምትወጡት? አስፈላጊ ከሆነ የምትደበቁበት ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ አለ? ያስቀመጣችሁት ገንዘብ አለ? ከቻላችሁ ቆጥቡ። እንዲሁም የምትተማመኑበት የምትደገፉት ሰው ይኑራችሁ። ከተለያየ አቅጣጫ ፕላን አውጡ አንዱ የአካላዊ ደህንነታችሁ ከመጠበቅ አንፃር ይሁን። ሞራል እንዲሆናችሁ የምትደውሉት ለማን ነው? እንዲያበረታታችሁ የምትደውሉት ለማን ነው? ጤናችሁን፤ ደህንነታችሁን እና መረጋጋትን ማስቀደም የማህበረሰቡ አካል እንድትሆኑ ብቻ ሳይሆን በተለይም ጊዜው ለሌሎች ከባድ በሆነበት ወቅት ጥሩ እና ድጋፍ የሚሰጥ አባል እንድትሆኑ ያግዛችሗል።